በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ሁልጊዜ የሚያገሉኝ ለምንድን ነው?

ሰዎች ሁልጊዜ የሚያገሉኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ሰዎች ሁልጊዜ የሚያገሉኝ ለምንድን ነው?

“ቅዳሜና እሁድ ከእኔ በስተቀር በመላው ዓለም የሚገኝ ሰው ሁሉ እየተዝናና እንዳለ ይሰማኛል።”—ረኔ

“ወጣቶች አንድ ላይ ተገናኝተው ጊዜ ያሳልፋሉ፤ እኔን ግን አይጠሩኝም!”—ጄረሚ

ቀኑ ደስ የሚል ነው፤ አንተ ግን ልታደርገው ያሰብከው ነገር የለም። ከአንተ በስተቀር ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉት ነገር አላቸው። ጓደኞችህ ሁሉ ወጣ ብለው እየተዝናኑ ነው። ዛሬም አንተን አልጠሩህም!

በአንድ ዝግጅት ላይ አለመጠራት ሊያሳዝን ይችላል፤ ከዚህ የከፋው ግን በዝግጅቱ ላይ አለመጠራትህ የሚያስተላልፈው መልእክት ነው። ምናልባት ራስህን እንዲህ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል:- ‘አንድ ችግር ቢኖርብኝ ነው፤ ሰዎች አብሬያቸው እንድሆን የማይፈልጉት ለምንድን ነው?’

ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?

ከሰዎች ጋር ለመቀራረብም ሆነ በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። እውነት ነው፣ እኛ ሰዎች ማኅበራዊ ኑሮ ስለምንወድ ከሌሎች ጋር ሆነን የምናደርገው ነገር ያስደስተናል። ይሖዋ፣ ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊት አዳምን አስመልክቶ ሲናገር “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ለሰው ሰው ያስፈልገዋል፤ ይህ የሰው ተፈጥሮ ነው። ሰዎች ሲያገሉን በጣም የምንጎዳው በዚህ ምክንያት ነው።

በተለይ ደግሞ ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ካገለሉህ አሊያም ጓደኞችህ እንዲሆኑ የምትፈልጋቸውን ሰዎች እንደማትመጥናቸው እንዲሰማህ የሚያደርግ ነገር ከተፈጸመብህ ሁኔታው ይበልጥ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንብህ ይችላል። ማሪ የተባለች ወጣት እንዲህ ትላለች:- “ትልልቅ ነገሮችን የሚያከናውኑ ፈጽሞ የማይነጣጠሉ ወጣቶች አሉ፤ ይሁንና ነገረ ሥራቸው ‘ከእኛ ጋር ለመሆን ሁኔታሽ አይመጥንም’ የሚል አስተሳሰብ እንዳላቸው ያሳያል።” ሌሎች አብረሃቸው እንድትሆን እንደማይፈልጉ ስትረዳ የመገለልና የብቸኝነት ስሜት ይሰማሃል።

አንዳንድ ጊዜ በሰዎች መካከል ሆነህም እንኳ እንደተገለልህ ሊሰማህ ይችላል። ኒኮል እንዲህ ብላለች:- “ነገሩ ያልተለመደ ቢሆንም በአንድ ግብዣ ላይ ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት ተሰምቶኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ይህ የሆነው በብዙ ሰዎች መካከል ብገኝም ከአንዳቸውም ጋር የቅርብ ጓደኝነት እንዳለኝ ስላልተሰማኝ ይመስለኛል።” አንዳንዶች በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ ሳይቀር ብቸኝነት ይሰማቸዋል። ሜጋን የተባለች አንዲት ወጣት “ከእኔ በስተቀር ሁሉም እርስ በርሱ የሚተዋወቅ ይመስላል!” በማለት ተናግራለች። ማሪያ የተባለች ወጣትም በተመሳሳይ “በብዙ ጓደኞቼ መካከል ሆኜ ጓደኛ ያጣሁ ያህል ነው” ስትል ስሜቷን ገልጻለች።

የብቸኝነት ስሜት የማይሰማው ሰው የለም፤ ታዋቂ ወይም ደስተኛ የሚመስሉ ሰዎች እንኳ ከዚህ ስሜት ነጻ አይደሉም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 14:13) አንድ ሰው የሚሰማው የብቸኝነት ስሜት ኃይለኛና ቀጣይነት ያለው ከሆነ ውሎ አድሮ ጉዳት ላይ ሊጥለው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል” ይላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህንን ጥቅስ “ሐዘን ቅስምህን ሊሰብር ይችላል” በማለት ተርጉሞታል። (ምሳሌ 15:13 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ሰዎች እንዳገለሉህ ተሰምቶህ ቅስምህ ተሰብሮ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ብቸኝነትን መዋጋት

የብቸኝነትን ስሜት ለመዋጋት የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር:-

በጠንካራ ጎኖችህ ላይ አተኩር። (2 ቆሮንቶስ 11:6) ‘ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ያሉህን አንዳንድ ተሰጥኦዎች ወይም ግሩም ባሕርያት ቆም ብለህ አስብና ከታች ጻፋቸው።

․․․․․

እንደተገለልክ ሆኖ ሲሰማህ ከላይ እንደዘረዘርካቸው ያሉ ጠንካራ ጎኖችህን አስታውስ። ድክመቶች እንዳሉህ ብሎም እነዚህን ድክመቶች ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርብህ እሙን ነው። ቢሆንም በስህተቶችህ ላይ ከልክ በላይ ላለማተኮር ጥረት አድርግ። ከዚህ ይልቅ ራስህን ስህተቶቹን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አንድ ግለሰብ አድርገህ ተመልከት። ሁሉንም ባይሆንም አንዳንድ ነገሮችን በትክክለኛው መንገድ እያከናወንክ ይሆናል። በእነዚህ ነገሮች ላይ አተኩር!

ፍቅርህን አስፋ። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13) ቅድሚያውን ወስደህ ከሰዎች ጋር ተዋወቅ። ይህ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። የ19 ዓመቷ ሊዝ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ሰዎች ሰብሰብ ብለው ሲታዩ ሊያስፈሩ ይችላሉ፤ ይሁንና ከእነርሱ መካከል አንዱን ቀርበህ ‘ታዲያስ’ ብትለው ሳትቸገር ከእነርሱ ጋር ተቀላቀልክ ማለት ነው።” (“ጭውውት ለመጀመር የሚረዱ ሐሳቦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ስለ መገለል ስንነጋገር አንተም አረጋውያንን ጨምሮ ማንንም እንዳታገል ጥንቃቄ አድርግ። ኮሪ የተባለች በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ወጣት እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “የ10 ወይም የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዕድሜ በጣም የምትበልጠኝ አንዲት ጓደኛ ነበረችኝ። የዕድሜ ልዩነት ቢኖረንም በጣም እንቀራረብ ነበር።”

በጉባኤህ ውስጥ ይበልጥ ልትተዋወቃቸው ስለምትፈልጋቸው ሁለት ትልልቅ ሰዎች አስብ።

․․․․․

በቀጣዩ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ከላይ ከጠቀስካቸው ሰዎች መካከል አንዱን ቀርበህ ለምን አታናግረውም። ይህ ሰው እውነትን እንዴት እንደሰማ ጠይቀው። “ከመላው የወንድማማች ማኅበር” ጋር ይበልጥ በተቀራረብህ ቁጥር ይሰማህ የነበረው የመገለልና የብቸኝነት ስሜት እየቀነሰ መምጣቱ አይቀርም።—1 ጴጥሮስ 2:17 NW

ስሜትህን ለትልቅ ሰው አካፍል። (ምሳሌ 17:17) ጭንቀቶችህን ለወላጆችህ ወይም ለሌላ ሰው ማካፈልህ የሚሰማህን የብቸኝነት ስሜት ለመቀነስ ይረዳሃል። አንዲት የ16 ዓመት ልጅ ይህን ተገንዝባለች። መጀመሪያ ላይ በመገለሏ ምክንያት በጣም ትጨነቅ ነበር። እንዲህ ትላለች:- “የመገለል ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገው ምን እንደሆነ ለማወቅ ደግሜ ደጋግሜ አስብበታለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ስለ ሁኔታው ለእናቴ አማክራትና ችግሩን እንዴት መቋቋም እንደምችል ምክር ትሰጠኛለች። ለሌሎች ማወያየት በእርግጥ ይረዳል!”

ስለሚሰማህ የብቸኝነት ስሜት ለሌላ ሰው ማወያየት ብትፈልግ ማንን ቀርበህ ማነጋገር ትችላለህ?

․․․․․

ስለ ሌሎች አስብ። (1 ቆሮንቶስ 10:24) መጽሐፍ ቅዱስ “ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” በማለት ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 2:4) እንደተገለልክ ሲሰማህ በቀላሉ እንደምትጨነቅ ወይም እንደምታዝን ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከምትዋጥ ይልቅ አንድን የተቸገረ ሰው ለመርዳት ለምን አንድ ነገር አታደርግም? ምናልባትም እንዲህ ማድረግህ አዳዲስ ጓደኞችን እንድታፈራ ይረዳህ ይሆናል!

ከቤተሰብህ ወይም ከጉባኤህ አባላት መካከል ሊሆን ይችላል የአንተ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ይኖር እንደሆነ እስቲ አስብ። የዚህን ሰው ስም ከዚህ በታች ጻፍና እንዴት ልትረዳው እንደምትችል አስብ።

․․․․․

ስለ ሌሎች ሰዎች ማሰብና በአንዳንድ ነገሮች እነርሱን መርዳት ስትጀምር የሚሰማህ የብቸኝነት ስሜት በእጅጉ ይቀንሳል። ይህ ደግሞ በአመለካከትህና በባሕርይህ ይበልጥ እንድትተማመን ስለሚያስችልህ በሌሎች ዘንድ በቀላሉ የምትቀረብ እንድትሆን ያደርግሃል። ምሳሌ 11:25 “ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” በማለት ይናገራል።

መራጭ ሁን። (ምሳሌ 13:20) ችግር ውስጥ ሊከቱህ የሚችሉ ብዙ ጓደኞች ከሚኖሩህ ይልቅ ስለ አንተ የሚያስቡ ጥቂት ጓደኞች ቢኖሩህ የተሻለ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የወጣቱን የሳሙኤልን ሁኔታ ተመልከት። ሳሙኤል በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግልበት ወቅት ብቸኝነት ተሰምቶት መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ከሥራ ባልደረቦቹ መካከል አንዳንዶቹ ይኸውም አፍኒን እና ፊንሐስ የሊቀ ካህናቱ ልጆች ቢሆኑም እንኳ ሥራቸው መጥፎ ስለሆነ ለጓደኝነት የሚመረጡ አልነበሩም። ሳሙኤል ከእነርሱ ጋር መግጠሙ መንፈሳዊ አደጋ ያስከትልበታል። እርሱ ደግሞ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲያጋጥመው አልፈለገም! መጽሐፍ ቅዱስ “ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ” ይላል። (1 ሳሙኤል 2:26) እዚህ ላይ በሰው ፊት ያለው ማንን ነው? አፍኒንን እና ፊንሐስን እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም እነርሱ ሳሙኤል መልካም በማድረጉ ምክንያት አግለውት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ሳሙኤል የነበሩት ግሩም ባሕርያት ለአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከፍተኛ ግምት በሚሰጡ ሰዎች ዘንድ እንዲወደድ አድርገውታል። ለአንተም የሚያስፈልጉህ ይሖዋን የሚወድዱ ጓደኞች ናቸው!

አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። (ምሳሌ 15:15) በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት ይሰማዋል። ታዲያ ምን ሊረዳህ ይችላል? በአፍራሽ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በሕይወትህ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አድርግ። በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥምህን እያንዳንዱን ሁኔታ መቆጣጠር እንደማትችል እሙን ነው፤ ይሁንና አንዳንድ ነገሮች ሲያጋጥሙህ የምትወስደውን እርምጃ መቆጣጠር እንደምትችል አስታውስ።

የብቸኝነት ስሜት ሲሰማህ አንድም ሁኔታውን ለማስተካከል ካልሆነም ደግሞ ቢያንስ ለሁኔታው ያለህን አመለካከት ለመለወጥ አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎችን ውሰድ። ይሖዋ አፈጣጠርህን ስለሚያውቅ የሚያስፈልጉህን ነገሮችና እነዚህን ነገሮች በተሻለ መንገድ ማሟላት የሚቻልበትን መንገድ እንደሚያውቅ ምንጊዜም አትርሳ። ዘወትር ስለሚሰማህ የብቸኝነት ስሜት ወደ ይሖዋ ጸልይ። ‘እርሱ ደግፎ እንደሚይዝህ’ እርግጠኛ ሁን።—መዝሙር 55:22

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው ቋሚ አምድ ሥር የወጡ ሌሎች ርዕሶችንም ማግኘት ይቻላል

ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ሰዎች እንዳገለሉኝ ከተሰማኝ ምን አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ እችላለሁ?

▪ በአፍራሽ አስተሳሰቦች ከመዋጥ ይልቅ ራሴን በሚዛናዊነት እንድመለከት የሚረዱኝ ምን ጥቅሶች አሉ?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጭውውት ለመጀመር የሚረዱ ሐሳቦች

ፈገግ በል። የሚታይብህ የፍቅር ስሜት ሌሎች ከአንተ ጋር ጭውውት እንዲጀምሩ ይጋብዛቸዋል።

ራስህን አስተዋውቅ። ስምህንና ከየት እንደመጣህ ተናገር።

ጥያቄዎችን ጠይቅ። በግለሰቡ የግል ጉዳይ ውስጥ ሳትገባ ስለ ማንነቱ ለማወቅ የሚያስችሉህን ተገቢ ጥያቄዎች ጠይቅ።

አዳምጥ። ቀጥሎ ምን እላለሁ ብለህ አታስብ። በቅድሚያ አዳምጥ። ቀጥሎ የምትጠይቀው ጥያቄ ወይም የምትናገረው ሐሳብ ራሱ ይመጣልሃል።

ዘና በል! ጭውውት አዲስ ጓደኝነት ለመመሥረት በሩን ይከፍታል። በመሆኑም አጋጣሚውን ተጠቀምበት!