በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 5

ከዘመዶቻችሁ ጋር በሰላም መኖር የምትችሉት እንዴት ነው?

ከዘመዶቻችሁ ጋር በሰላም መኖር የምትችሉት እንዴት ነው?

“ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12

ትዳር ውስጥ ስትገባ አዲስ ቤተሰብ ትመሠርታለህ። ወላጆችህን ምንጊዜም የምትወዳቸውና የምታከብራቸው ቢሆንም ካገባህ በኋላ ግን በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ የምትበልጥብህ የትዳር ጓደኛህ ናት። የሁለታችሁም ወላጆችም ሆነ ሌሎች ዘመዶች ይህን ሐቅ መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አዲሱን ቤተሰባችሁን ለማጠናከር ስትጥሩ ከሁለታችሁም ወላጆችና ዘመዶች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራችሁ በማድረግ ረገድ ሚዛናችሁን መጠበቅ እንድትችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ሊረዷችሁ ይችላሉ።

1 ለዘመዶቻችሁ ተገቢ አመለካከት ይኑራችሁ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አባትህንና እናትህን አክብር።” (ኤፌሶን 6:2) ትልቅ ሰው ብትሆንም ምንጊዜም ወላጆችህን ማክበር ያስፈልግሃል። የትዳር ጓደኛህም ለወላጆቿ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልጋት መዘንጋት የለብህም። “ፍቅር አይቀናም።” በመሆኑም የትዳር ጓደኛህ ከወላጆቿ ጋር በመቀራረቧ ልትሰጋ አይገባም።—1 ቆሮንቶስ 13:4፤ ገላትያ 5:26

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • “ቤተሰቦችሽ ሁልጊዜ ይንቁኛል” ወይም “እናትህ እኔ የማደርገው ነገር ሁሉ በፍጹም አያስደስታትም” እንደሚሉት ያሉ አነጋገሮችን ከመጠቀም ተቆጠቡ

  • ነገሮችን በትዳር ጓደኛችሁ ቦታ ሆናችሁ ለማየት ሞክሩ

2 አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ ሁኑ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 2:24) ትዳር ከመሠረታችሁም በኋላ ወላጆቻችሁ እናንተን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል፤ በመሆኑም ከሚገባው በላይ በትዳራችሁ ውስጥ ለመግባት ይሞክሩ ይሆናል።

በዚህ ረገድ ገደብ ማበጀትና ይህንንም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለወላጆቻችሁ ማሳወቁ የእናንተ ኃላፊነት ነው። ወላጆቻችሁን የሚያስከፋ ነገር ሳትናገሩ ጉዳዩን በግልጽና በማያሻማ መንገድ ልታሳውቋቸው ትችላላችሁ። (ምሳሌ 15:1) ትሕትና፣ ገርነትና ትዕግሥት ከወላጆቻችሁም ሆነ ከሌሎች ዘመዶቻችሁ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራችሁና “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል” እንድትኖሩ ይረዷችኋል።—ኤፌሶን 4:2

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ዘመዶቻችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ከሚገባው በላይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ ከተሰማህ ጉዳዩን ተረጋግታችሁ ባላችሁበት ሰዓት ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተወያዩበት

  • እነዚህን ጉዳዮች እንዴት መፍታት እንደምትችሉ ተወያይታችሁ ወስኑ