ምዕራፍ 22
“የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”
ጳውሎስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቆርጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ
በሐዋርያት ሥራ 21:1-17 ላይ የተመሠረተ
1-4. ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዘው ለምንድን ነው? እዚያስ ምን ይጠብቀዋል?
ጳውሎስና ሉቃስ ከሚሊጢን በሚነሳው መርከብ ላይ ቆመዋል፤ ስንብቱ በጣም ከባድ ነበር። ከሚወዷቸው የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር የተለያዩት በግድ ነው! አሁን ሁለቱ ሚስዮናውያን ጉዞ ሊጀምሩ ነው። ለጉዞ የሚያስፈልጓቸውን በርካታ ነገሮች ሸክፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ በይሁዳ ላሉ ችግረኛ ክርስቲያኖች የተሰባሰበውን ገንዘብ ይዘዋል፤ ይህን ስጦታ በማስረከብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቸኩለዋል።
2 ነፋሱ የመርከቡን ሸራዎች ወጠራቸው፤ መርከቡም በጫጫታ የተሞላውን ወደብ ተሰናብቶ መንቀሳቀስ ጀመረ። እነዚህ ሁለት ሰዎችና ሰባቱ የጉዞ ጓደኞቻቸው፣ ዓይናቸው ከባሕሩ ዳርቻ አልተነቀለም፤ በሐዘን የተዋጡት ወንድሞቻቸው አሁንም እዚያው ናቸው። (ሥራ 20:4, 14, 15) መርከቡ ርቆ ወዳጆቻቸው ከዓይናቸው እስኪሰወሩ ድረስ መንገደኞቹ እጃቸውን ማውለብለባቸውን አላቆሙም።
3 ጳውሎስ ለሦስት ዓመት ያህል በኤፌሶን ካሉ ሽማግሌዎች ጋር በቅርብ ሲሠራ ቆይቷል። አሁን ግን የመንፈስ ቅዱስን አመራር በመከተል ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ነው። በዚያ ምን እንደሚጠብቀው በተወሰነ መጠን ያውቃል። ቀደም ሲል እነዚህን ሽማግሌዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እዚያ ምን እንደሚደርስብኝ ባላውቅም መንፈስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው፤ እርግጥ ነው፣ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ በደረስኩበት ከተማ ሁሉ በተደጋጋሚ ያሳስበኛል።” (ሥራ 20:22, 23) ጳውሎስ አደጋ ቢደቀንበትም ‘መንፈስ ግድ ብሎታል’፤ ሐዋርያው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ መንፈስ የሰጠውን መመሪያ ለመከተል የውዴታ ግዴታ ተሰምቶታል። ጳውሎስ መከራ እንዲደርስበት ባይፈልግም በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ነው።
4 አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን፣ በሕይወታችን ውስጥ ከምንም ነገር በላይ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም ቃል ገብተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን የታማኝነት ምሳሌ በመመርመር የምናገኘው ትምህርት አለ።
‘የቆጵሮስን ደሴት’ አልፈው ሄዱ (የሐዋርያት ሥራ 21:1-3)
5. ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ወደ ጢሮስ የተጓዙት እንዴት ነው?
5 ጳውሎስና ጓደኞቹ የተሳፈሩበት መርከብ በዚያው ቀን ቆስ ደረሰ፤ ‘የተጓዘው በቀጥታ’ ነው። ተስማሚ ነፋስ ስለነበረ በዚያ እየተነዱ በፍጥነት መጓዝ ችለው ነበር። (ሥራ 21:1) መርከቡ ቆስ ላይ መልሕቁን ጥሎ ያደረ ይመስላል፤ በማግስቱ ወደ ሮድስ ከዚያም ወደ ጳጥራ ጉዞውን ቀጠለ። በትንሿ እስያ ደቡባዊ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ጳጥራ ሲደርሱ ወንድሞች በአንድ ትልቅ የዕቃ ማጓጓዣ መርከብ ተሳፍረው በፊንቄ ወደምትገኘው ጢሮስ አመሩ። በጉዟቸው ላይ ‘የቆጵሮስን ደሴት በስተ ግራ ትተው’ አለፉ። (ሥራ 21:3) የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሉቃስ ይህን ጉዳይ ለይቶ የጠቀሰው ለምንድን ነው?
6. (ሀ) ጳውሎስ ቆጵሮስን ማየቱ ሊያበረታታው የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ያህል እንደባረከህና እንደረዳህ ማሰብህ ምን መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ያደርግሃል?
6 ምናልባት ጳውሎስ ደሴቷን እያሳያቸው በዚያ ያጋጠሙትን ነገሮች ነግሯቸው ሊሆን ይችላል። ከዘጠኝ ዓመት በፊት በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ከበርናባስና ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር ወደዚህች ደሴት ሄዶ ነበር፤ በዚያ ሲያገለግሉ ኤልማስ የተባለ ጠንቋይ የስብከቱን ሥራ ለመቃወም ሞክሮ ነበር። (ሥራ 13:4-12) ጳውሎስ ደሴቲቱን ሲያይ በዚያ ያሳለፈው ትዝታ ወደ አእምሮው መጥቶ ይሆናል፤ ያን ጊዜ መለስ ብሎ ማሰቡ ሳያበረታታው አይቀርም፤ ከፊቱ ለሚጠብቀው ነገርም አጠናክሮት ሊሆን ይችላል። እኛም አምላክ ምን ያህል እንደባረከንና ፈተናዎችን በጽናት እንድንወጣ እንደረዳን መለስ ብለን ማሰባችን ይጠቅመናል። እንዲህ ማድረጋችን የዳዊት ዓይነት ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል፤ ዳዊት “የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል” በማለት ጽፏል።—መዝ. 34:19
የሐዋርያት ሥራ 21:4-9)
‘ደቀ መዛሙርቱን ፈልገን አገኘናቸው’ (7. መንገደኞቹ ጢሮስ ሲደርሱ ምን አደረጉ?
7 ጳውሎስ ከክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያለውን ጠቀሜታ ያውቃል፤ ስለዚህ በእምነት ከሚዛመዱት ሰዎች ጋር ለመገናኘት ጓጉቶ ነበር። ጢሮስ በደረሱ ጊዜ ‘ደቀ መዛሙርቱን ፈልገው እንዳገኟቸው’ ሉቃስ ጽፏል። (ሥራ 21:4) እነዚህ መንገደኞች በጢሮስ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው እንዳሉ ስለሚያውቁ ፈልገው አገኟቸው፤ ያረፉትም እነሱ ጋ ሳይሆን አይቀርም። እውነትን ማወቅ ከሚያስገኛቸው ታላላቅ በረከቶች አንዱ፣ የትም ብንሄድ በደስታ የሚቀበሉን የእምነት ባልንጀሮች ማግኘታችን ነው። አምላክን የሚወዱና እውነተኛውን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎች በመላው ዓለም ወዳጆች አሏቸው።
8. በሐዋርያት ሥራ 21:4 ላይ ያለውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል?
8 መንገደኞቹ በጢሮስ ሰባት ቀናት አሳለፉ፤ በዚያ ስለሆነው ነገር ሉቃስ የጻፈው ዘገባ ላይ ላዩን ሲታይ ግራ ሊያጋባ ይችላል፤ ሉቃስ “[በጢሮስ ያሉት ወንድሞች] በመንፈስ ተመርተው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ደጋግመው ነገሩት” ብሏል። (ሥራ 21:4) ይሖዋ፣ ሐሳቡን ለውጦ ይሆን? ቀድሞውንም ቢሆን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የመራው እሱ ነው፤ ታዲያ አሁን እንዳይሄድ መመሪያ እየሰጠው ነው? አይደለም። መንፈስ የጠቆመው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም እንግልት እንደሚደርስበት ነው፤ ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ አላለውም። መንፈስ ቅዱስ ለጢሮስ ወንድሞች ያሳወቃቸው ነገር አለ፤ ከዚህ በመነሳት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ችግር እንደሚያጋጥመው የተገነዘቡ ይመስላል። በመሆኑም ለጳውሎስ ደህንነት ስላሳሰባቸው ወደዚያ እንዳይሄድ ጎተጎቱት። ጳውሎስን ከአደጋ ለማዳን መፈለጋቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ጳውሎስ ግን የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ስለቆረጠ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዙን ቀጠለ።—ሥራ 21:12
9, 10. (ሀ) ጳውሎስ በጢሮስ ያሉ ወንድሞች ያሳሰባቸውን ጉዳይ ሲገልጹ ሲሰማ የትኛው ተመሳሳይ ሁኔታ ትዝ ሳይለው አልቀረም? (ለ) በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚታየው አመለካከት ምንድን ነው? ይህስ ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ የሚለየው እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ የወንድሞችን ልመና ሲሰማ፣ ኢየሱስ የገጠመውን ነገር ሳያስታውስ አይቀርም፤ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ፣ ብዙ መከራ እንደሚደርስበትና እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ጴጥሮስ በስሜታዊነት “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” ብሎት ነበር። ኢየሱስ ግን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” ብሎታል። (ማቴ. 16:21-23) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸምና ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለመስጠት ቆርጦ ነበር። ጳውሎስም የሚሰማው እንዲሁ ነው። ልክ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁሉ የጢሮስ ወንድሞችም ጳውሎስን የለመኑት በአሳቢነት እንደሆነ አያጠያይቅም፤ ይሁን እንጂ የአምላክን ፈቃድ አልተገነዘቡም ነበር።
10 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በራሳቸው ላይ መጨከን ወይም ምንም ዓይነት መሥዋዕት መክፈል አይፈልጉም። በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች የሚመርጡት፣ ለራሳቸው የሚመቻቸውና ከአባላቱ ብዙ የማይጠብቅ ሃይማኖት መከተል ነው። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ከዚህ ፍጹም የተለየ አመለካከት እንዲኖረን አበረታቷል። ደቀ መዛሙርቱን “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 16:24) ኢየሱስን መከተል ትክክለኛና የጥበብ ጎዳና ነው፤ ቀላሉ ጎዳና ነው ማለት ግን አይደለም።
11. በጢሮስ ያሉ ደቀ መዛሙርት ለጳውሎስ ያላቸውን ፍቅርና ድጋፍ የገለጹት እንዴት ነው?
11 ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ፣ ሉቃስና አብረዋቸው ያሉት ሌሎች ወንድሞች ጉዟቸውን የሚቀጥሉበት ጊዜ ደረሰ። ከጢሮስ ሲነሱ ስለነበረው ሁኔታ የሚገልጸው ዘገባ ስሜት የሚነካ ነው። የጢሮስ ወንድሞች ለጳውሎስ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና በአገልግሎቱ እንዲጸና ለማበረታታት ያላቸውን ፍላጎት በግልጽ አሳይተዋል። በዚያ የነበሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ጳውሎስንና ጓደኞቹን እስከ ባሕሩ ዳርቻ ድረስ ሸኟቸው። ሁሉም አንድ ላይ ተንበርክከው ከጸለዩ በኋላ ተሰነባበቱ። ከዚያም ጳውሎስ፣ ሉቃስና አብረዋቸው የሚጓዙት ወንድሞች ሌላ መርከብ ተሳፍረው ወደ ጴጤሌማይስ ተጓዙ፤ እዚያም ከወንድሞች ጋር አንድ ቀን ዋሉ።—ሥራ 21:5-7
12, 13. (ሀ) ፊልጶስ ምን የአገልግሎት ታሪክ አስመዝግቧል? (ለ) ፊልጶስ ዛሬ ላሉ ክርስቲያን አባቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?
12 በመቀጠል ጳውሎስና አብረውት የሚጓዙት ወንድሞች ወደ ቂሳርያ ማምራታቸውን ሉቃስ ዘግቧል። እዚያ ሲደርሱም “ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት [ገቡ]።” a (ሥራ 21:8) ፊልጶስን በማግኘታቸው እጅግ ተደስተው መሆን አለበት። ፊልጶስ ከ20 ዓመት ገደማ በፊት የክርስቲያን ጉባኤ ጨቅላ በነበረበት ወቅት ምግብ በማከፋፈሉ ሥራ እንዲረዳ በሐዋርያት ተሹሞ ነበር። ፊልጶስ ለብዙ ዓመታት በቅንዓት ባከናወነው የስብከት ሥራ መልካም ስም አትርፏል። ደቀ መዛሙርቱ በስደት የተነሳ ወደተለያዩ ቦታዎች ሲበታተኑ ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ በዚያ መስበክ እንደጀመረ አስታውስ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሰበከለት ከመሆኑም ሌላ አጥምቆታል። (ሥራ 6:2-6፤ 8:4-13, 26-38) በእርግጥም አገልግሎቱን በታማኝነት በመወጣት ረገድ ብዙ ታሪክ አስመዝግቧል!
13 ፊልጶስ ለአገልግሎት ያለው ቅንዓት አልቀዘቀዘም። መኖሪያውን በቂሳርያ ያደረገው ፊልጶስ አሁንም በስብከቱ ሥራ በትጋት እየተሳተፈ ነው፤ ሉቃስ “ወንጌላዊው” ብሎ የጠራው መሆኑ ይህን ያሳያል። በተጨማሪም ትንቢት የሚናገሩ አራት ሴቶች ልጆች አፍርቷል፤ ይህም ልጆቹ የአባታቸውን ፈለግ እንደተከተሉ ያሳያል። b (ሥራ 21:9) በመሆኑም ፊልጶስ የቤተሰቡን መንፈሳዊነት ለመገንባት ብዙ ጥረት አድርጎ መሆን አለበት። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን አባቶች የፊልጶስን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው፤ በአገልግሎት ግንባር ቀደም በመሆን ልጆቻቸው የወንጌላዊነቱን ሥራ እንዲወዱት መርዳት ይችላሉ።
14. ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን መጎብኘቱ ምን በጎ ውጤት አስገኝቶ መሆን አለበት? ዛሬስ ምን ተመሳሳይ አጋጣሚዎች አሉ?
14 ጳውሎስ በደረሰበት ቦታ ሁሉ የእምነት ባልንጀሮቹን ለማግኘት ጥረት ያደርጋል፤ ከዚያም አብሯቸው ጊዜ ያሳልፋል። በየቦታው የሚያገኛቸው ወንድሞችም ይህን ሚስዮናዊና የጉዞ ባልደረቦቹን በእንግድነት ለመቀበል እንደሚጓጉ ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ጉብኝት ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ እንዳስቻላቸው ምንም ጥያቄ የለውም። (ሮም 1:11, 12) ዛሬም ቢሆን እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች አሉ። ቤትህ ትንሽ ቢሆንም እንኳ የወረዳ የበላይ ተመልካቹንና ሚስቱን በእንግድነት መቀበልህ ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል።—ሮም 12:13
“ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ” (የሐዋርያት ሥራ 21:10-14)
15, 16. አጋቦስ ያመጣው መልእክት ምንድን ነው? ወንድሞች መልእክቱን ሲሰሙ ምን ተሰማቸው?
15 ጳውሎስ ፊልጶስ ቤት እያለ፣ አጋቦስ የሚባል ሌላ የተከበረ እንግዳ መጣ። በፊልጶስ ቤት የተሰበሰቡት ሰዎች አጋቦስ ነቢይ መሆኑን ያውቃሉ፤ ደግሞም በቀላውዴዎስ ዘመን ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት ተንብዮ ነበር። (ሥራ 11:27, 28) ሰዎቹ አጋቦስ የመጣበት ምክንያት ጥያቄ ፈጥሮባቸው ይሆናል፤ ‘ምን መልእክት ይዞ ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ሁሉም በትኩረት እየተመለከቱት ሳለ የጳውሎስን ቀበቶ ወሰደ፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቀበቶ ገንዘብና ሌሎች ነገሮች ለመያዝ የሚያገለግል ወገብ ላይ የሚታሰር ረጅም መቀነት ነው። አጋቦስ በቀበቶው የራሱን እግሮችና እጆች አሰረ። ከዚያም ይህን አስደንጋጭ መልእክት ተናገረ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን ቀበቶ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’”—ሥራ 21:11
16 ትንቢቱ፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ የማይቀር መሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም በዚያ የሚገኙት አይሁዳውያን ‘ለአሕዛብ አሳልፈው’ እንደሚሰጡት ይጠቁማል። ይህ ትንቢት በዚያ የነበሩትን ሁሉ ረበሻቸው። ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘እያለቀሳችሁ ልቤን ለምን ታባባላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ’ ሲል መለሰ።”—ሥራ 21:12, 13
17, 18. ጳውሎስ ከአቋሙ ፍንክች እንደማይል ያሳየው እንዴት ነው? የወንድሞችስ ምላሽ ምን ነበር?
17 እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሉቃስን ጨምሮ ወንድሞች፣ ጳውሎስ ጉዞውን እንዳይቀጥል እየለመኑት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ያለቅሳሉ። ጳውሎስ፣ የወንድሞቹን ፍቅርና ስስት ሲያይ “ልቤን ለምን ታባባላችሁ?” አላቸው፤ አንዳንድ ትርጉሞች “ልቤን እየሰበራችሁት ነው” በማለት አስቀምጠውታል። ያም ቢሆን ጳውሎስ ከአቋሙ ፍንክች አላለም፤ በጢሮስም ሆነ እዚህ ያገኛቸው ወንድሞች ለቅሶና ልመና ልቡን እንዲከፍለው አልፈቀደም። ይልቁንም ጉዞውን መቀጠል ያለበት ለምን እንደሆነ አስረዳቸው። ድፍረቱና ቆራጥነቱ እጅግ ይደንቃል! ከእሱ በፊት ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ ጳውሎስም ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቆርጦ ተነስቷል። (ዕብ 12:2) ጳውሎስ ሰማዕት የመሆን ፍላጎት የለውም፤ ሆኖም ይህ የማይቀር ከሆነ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ ሆኖ መሞቱን እንደ ክብር ይቆጥረዋል።
18 የወንድሞች ምላሽ ምን ነበር? በአጭሩ፣ ሐሳቡን አክብረውለታል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እሱን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ ‘እንግዲህ የይሖዋ ፈቃድ ይሁን’ ብለን ዝም አልን።” (ሥራ 21:14) ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለማሳመን የጣሩት ወንድሞች ሐሳባቸውን እንዲቀበል አላስገደዱትም። የጳውሎስን ሐሳብ ሰምተው እሱ ባለው ተስማሙ፤ ነገሩ ቢከብዳቸውም የይሖዋን ፈቃድ መቀበል እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። ጳውሎስ የጀመረው ጎዳና የኋላ ኋላ ለሞት ሊዳርገው ይችላል። ወዳጆቹ ሁኔታውን ለመቀበል የሚያቀሉለት ይህን እንዳያደርግ ለማግባባት ጥረት ማድረጋቸውን ካቆሙ ነው።
19. ጳውሎስ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
19 ጳውሎስ ካጋጠመው ሁኔታ የምናገኘው ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ አምላክን ለማገልገል ሲሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ክርስቲያኖች የያዙትን ጎዳና እንዲተዉ ለማግባባት ፈጽሞ መሞከር የለብንም። የሞትና የሕይወት ጉዳይ በሆኑ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮችም ይህን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ ብዙ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን ለማገልገል ሩቅ ወደሆነ አካባቢ ሲሄዱ ሁኔታው እንደሚከብዳቸው የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን እነሱን ተስፋ ላለማስቆረጥ ይጠነቀቃሉ። በእንግሊዝ የምትኖረው ፊሊስ አንድ ልጇ ሚስዮናዊት ሆና ለማገልገል ወደ አፍሪካ ስትሄድ ምን እንደተሰማት አትረሳውም። እንዲህ ብላለች፦ “ስሜቴ እጅግ ተረብሾ ነበር። ከእኔ በጣም ርቃ እንደምትሄድ መቀበል ከበደኝ። በአንድ በኩል አዘንኩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኩራት ተሰማኝ። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ጸለይኩ። ሆኖም ውሳኔውን ለእሷ ተውኩት፤ ሐሳቧን ለማስቀየር አልሞከርኩም። ደግሞም እኮ ያስተማርኳት የአምላክን መንግሥት እንድታስቀድም ነው! ላለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ አገሮች አገልግላለች፤ በታማኝነት በመጽናቷም ይሖዋን በየቀኑ አመሰግነዋለሁ።” የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማበረታታት በእርግጥም ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው!
የሐዋርያት ሥራ 21:15-17)
“ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን” (20, 21. ጳውሎስ ከወንድሞች ጋር የመሆን ፍላጎት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው? ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መሆን የፈለገውስ ለምንድን ነው?
20 አስፈላጊው ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ጳውሎስ ጉዞውን ቀጠለ፤ አንዳንድ የቂሳርያ ወንድሞችም አብረውት ናቸው፤ እነዚህ ታማኝ ወንድሞች በዚህ መንገድ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም ባደረጉት ጉዞ በደረሱበት ሁሉ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። በጢሮስ ደቀ መዛሙርቱን አግኝተው ከእነሱ ጋር ለሰባት ቀናት ቆይተዋል። በጴጤሌማይስ እህቶችንና ወንድሞችን ሰላም ካሉ በኋላ አብረዋቸው ውለዋል። በቂሳርያ በፊልጶስ ቤት ለበርካታ ቀናት ተቀምጠዋል። ቀጥሎ ደግሞ በቂሳርያ ያሉ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ጳውሎስንና ጓደኞቹን እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ሸኟቸው፤ እዚያ ሲደርሱም ከቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ በሆነው በምናሶን ቤት አረፉ። ሉቃስ እንደዘገበው በኢየሩሳሌም “ወንድሞች በደስታ [ተቀበሏቸው]።”—ሥራ 21:17
21 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መሆን ያስደስተው ነበር። ዛሬ ወንድሞቻችን የብርታት ምንጭ እንደሚሆኑን ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስም ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ጋር ጊዜ ሲያሳልፍ ይበረታታል። ይህ ማበረታቻ፣ ጳውሎስ ሊገድሉት የሚፈልጉ ኃይለኛ ተቃዋሚዎቹን ለመጋፈጥ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሰጠው ምንም አያጠያይቅም።
a “ ቂሳርያ—የሮም ግዛት የሆነው የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b “ ሴቶች፣ ክርስቲያን አገልጋዮች መሆን ይችላሉ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።