በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን የቤቴል ሕንጻዎች እንድትጎበኝ ጋብዘንሃል

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን የቤቴል ሕንጻዎች እንድትጎበኝ ጋብዘንሃል

ከቫኑዋቱ የመጡ አንድ ባልና ሚስት በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከጎበኙ በኋላ “ቤቴልን መጎብኘታችን ዕድሜ ልካችንን የማንረሳው ልዩ ትዝታ ጥሎብን አልፏል” ብለዋል። በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤቴልን የሚጎበኙ ሲሆን እነሱም የእነዚህን ባልና ሚስት ስሜት ይጋራሉ።

አንተስ በዩናይትድ ስቴትስ ያለውን ቤቴል ጎብኝተሃል? ካልጎበኘህ እንዲህ እንድታደርግ እንጋብዝሃለን።

በዋነኞቹ ሦስት የቤቴል ሕንጻዎች ውስጥ ምን ሥራዎች ይከናወናሉ?

ዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት። ሦስት ዐውደ ርዕዮችን ያለአስጎብኚ የማየት አጋጣሚ ታገኛለህ። አንደኛው “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም” የሚል ርዕስ አለው፤ ይህ ዐውደ ርዕይ በቀላሉ የማይገኙ መጽሐፍ ቅዱሶችን እንዲሁም የአምላክ ስም ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሳይጠፋ ሊቆይ የቻለው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። “ለይሖዋ ስም የሚሆን ሕዝብ” የተባለው ዐውደ ርዕይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳለፉትን ታሪክ የሚያስቃኝ ነው። “የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት​—በተግባር የተደገፈ እምነት” የተባለው ዐውደ ርዕይ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ የሚሰበሰቡት፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች የሚናገሩት እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ፍቅር የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ከዚህም በተጨማሪ በተመደበልህ አስጎብኚ አማካኝነት የቢሮዎችና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃውን እንዲሁም የዎርዊክን ግቢ በ20-ደቂቃ ውስጥ መጎብኘት ትችላለህ።

ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል። በዚህ ማዕከል ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ለምሳሌ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤትን እንዲሁም ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀውን ትምህርት ቤት በተመደበልህ አስጎብኚ አማካኝነት መጎብኘት ትችላለህ። በተጨማሪም የሥዕልና የኦዲዮ/ቪዲዮ ክፍሎችን ጨምሮ በዚያ ባሉ የተለያዩ ቢሮዎች ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን የሚያሳዩ ትዕይንቶችንና ቪዲዮዎችን ማየት ትችላለህ።

በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ የሚገኙት የጽሑፍ ማተሚያና መላኪያ ሕንፃዎች። መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚታተሙት፣ የሚጠረዙት እንዲሁም በዮናይትድ ስቴትስ፣ በካሪቢያንና በሌሎች አካባቢዎች ወደሚገኙ ጉባኤዎች የሚላኩት እንዴት እንደሆነ በተመደበልህ አስጎብኚ አማካኝነት መጎብኘት ትችላለህ።

የጉብኝት ቀጠሮ ማስያዝ የምችለው እንዴት ነው?

ለጉዞ መዘጋጀት ከመጀመርህ በፊት እባክህ “ቢሮዎቻችንን ጎብኝ“ ወደሚለው ገጽ ሄደህ የጉብኝት ቀጠሮ አስገባ። በዚህ ገጽ ላይ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ስለሚገኙት የቤቴል ሕንፃዎች እንዲሁም ስለሚገኙበት አድራሻና ጉብኝቱ ስለሚወስደው ጊዜ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

አስጎብኚዎቹ እነማን ናቸው?

አስጎብኚዎቹ በቤቴል በሚገኙ የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ውስጥ የሚያገለግሉት ቤቴላውያን ናቸው። በዚህ ረገድ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የማስተማር ሥራ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይሰማቸዋል። ጉብኝቱን በበርካታ ቋንቋዎች ማካሄድ ይቻላል።

ጉብኝቱ ምን ያህል ያስከፍላል?

ጉብኝቱ የሚካሄደው ያለክፍያ ነው።

እነዚህን ቦታዎች ለመጎብኘት የግድ የይሖዋ ምሥክር መሆን ያስፈልጋል?

በፍጹም። እንዲያውም አብዛኞቹ ጎብኚዎች የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች እነዚህን ቦታዎች መጎብኘታቸው የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ እያከናወኑ ስላሉት ሥራ ይበልጥ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።

ከሕንድ የመጣች አንዲት የእስልምና እምነት ተከታይ ፓተርሰንን ጎብኝታ ነበር። ከጉብኝቱ በኋላ “እኔም የዚህ ድርጅት አባል መሆን እፈልጋለሁ። በአክብሮት ስለያዛችሁኝ እጅግ አመሰግናለሁ” ብላለች።

ልጆች መጎብኘት ይችላሉ?

እንዴታ! ልጆች እንዲህ ያለ ጉብኝት ማድረጋቸው በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል። ጆን የተባለ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ አንድ ጎብኚ እንዲህ ብሏል፦ “አብረውን የጎበኙት ልጆች ወደ ቤት ከተመለስን በኋላም በጉብኝታቸው ወቅት ስላዩአቸው ነገሮች ማውራታቸውን አላቆሙም። ከጉብኝቱ በፊት ቤቴል ማገልገል ሲባል ምን እንደሆነ በውል የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ አሁን ግን ቤቴል ገብተው ለማገልገል ግብ አውጥተዋል።”

በሌሎች አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መጎብኘት ይቻላል?

አዎ፣ በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችንም መጎብኘት ይቻላል። ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የሚገኙበትን አድራሻ ለማወቅ ከቢሮዎቻችንና ከጉብኝት ጋር የተያያዘ መረጃ የሚገኝበትን ገጽ ተመልከት። የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መጥተህ እንድትጎበኝ በአክብሮት ጋብዘንሃል።