በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኒው ዮርክ ሲቲ ለአሜሪካ ሕንዶች የተዘጋጀ ዓውደ ርዕይ

በኒው ዮርክ ሲቲ ለአሜሪካ ሕንዶች የተዘጋጀ ዓውደ ርዕይ

በርካታ ሰዎች፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የአሜሪካ ሕንዶች በብዛት የሚኖሩት ለእነሱ በተከለሉት የአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ብቻ ይመስላቸዋል። እንደ እውነታው ከሆነ ግን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የዚህ ጎሳ ተወላጆች የሚኖሩት በከተማዎች ውስጥ ነው። ከዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች መካከል ትልቋ የሆነችው ኒው ዮርክ ከሰኔ 5-7, 2015 “ጌትዌይ ቱ ኔሽንስ” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የአሜሪካ ሕንዶች ክብረ በዓልና ፓውዋው (የአሜሪካ ሕንዶች ባሕላዊ ዝግጅት) አስተናግዳለች። a በኒው ዮርክ የሚገኙ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ዝግጅት መደረጉን ሲሰሙ ወዲያውኑ የዝግጅቱ ተካፋይ ለመሆን እቅድ አወጡ። ለምን?

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ይተረጉማሉ፤ ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ደግሞ እንደ ሆፒ፣ ሞሆክ፣ ብላክፉት፣ ናቫሆ፣ ኦዳዋ፣ ዳኮታና ፕሌንስ ክሪ ያሉ በርካታ የአሜሪካ ሕንዶች ቋንቋዎች ይገኙበታል። በመሆኑም “ጌትዌይ ቱ ኔሽንስ” የሚል ስያሜ በተሰጠው ዓውደ ርዕይ ላይ ቀልብ የሚስቡ ጠረጴዛዎችንና ጋሪዎችን በመጠቀም በፈጣሪ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ! የሚለውን ትራክት ጨምሮ በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የተለያዩ ጽሑፎችን ለእይታ አቅርበዋል!

ድረ ገጻችንም ከላይ በተጠቀሱት ቋንቋዎች የተዘጋጁ የኦዲዮ ቪዲዮ ፕሮግራሞችን ይዟል። “ጌትዌይ ቱ ኔሽንስ” በተባለው ዝግጅት ላይ የተካፈሉ የይሖዋ ምሥክሮች የማወቅ ፍላጎት ላላቸው በርካታ ጎብኚዎች የተለያዩ የኦዲዮ ቪዲዮ ፕሮግራሞችን አጫውተውላቸዋል፤ ከይሖዋ ምሥክሮች በተቃራኒ ሌሎቹ ቦታዎች ላይ ለእይታ የቀረቡት ነገሮችም ሆኑ የተሰቀሉት ማስታወቂያዎች የተዘጋጁት በእንግሊዝኛ ወይም በስፓንኛ ብቻ መሆኑን ጎብኚዎቹ ማስተዋል ችለዋል።

በዓውደ ርዕዩ ላይ የተገኙትን በርካታ ሰዎች ያስገረማቸው በተለያዩ የአሜሪካ ሕንድ ቋንቋዎች ለመተርጎም የምናደርገው ጥረት ብቻ ሳይሆን በከተማም ሆነ በገጠር ያሉትን እነዚህን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር የምናደርገው ጥረት ነው። በዚህ ዝግጅት ላይ የተሳተፈ አንድ ሰው ስለምናከናውነው ሥራ ካወቀ በኋላ በዚያ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች “መጥታችሁ እንድትጠይቁኝና መጽሐፍ ቅዱስን እንድታስጠኑኝ እፈልጋለሁ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስተምሩት ጠይቋል።

የአሜሪካ ሕንድ ተወላጅ የሆኑ መስማት የተሳናቸው አንድ ባልና ሚስት ጽሑፎቻችን ወደተደረደሩበት ቦታ መጡ፤ ሆኖም በዚያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የምልክት ቋንቋ ስለማይችሉ ሊያነጋግሯቸው አልቻሉም። ይሁንና በዚያኑ ሰዓት ምልክት ቋንቋ የተማረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር መጣች። ከእነዚህ ባልና ሚስት ጋር ለ30 ደቂቃ ያህል ከተወያየች በኋላ በአካባቢያቸው የይሖዋ ምሥክሮች በምልክት ቋንቋ የክልል ስብሰባ የሚያደርጉት መቼና የት እንደሆነ ነገረቻቸው።

ለሦስት ቀን በቆየው በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር በተደረገው ጥረት ከ50 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች የተካፈሉ ሲሆን ጎብኚዎች ከ150 በላይ ጽሑፎችን ወስደዋል።

a ዊልያም ፓወርስ የተባሉ አንትሮፖሎጂስት በአሁኑ ጊዜ ያለው የፓውዋው ባሕላዊ ዝግጅት ምን ገጽታ እንዳለው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ሃይማኖታዊ ያልሆነ ፕሮግራም የቡድን ጭፈራን ለማጀብ አንድ ላይ ሆኖ መዝፈንን ያካትታል፤ በጭፈራው ላይ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ይካፈላሉ።”—ኤትኖሚዩዚኮሎጂ፣ መስከረም 1968፣ ገጽ 354