በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋችንን ለሰዎች መናገር—ፓሪስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋችንን ለሰዎች መናገር—ፓሪስ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP21) ከኅዳር 30 እስከ ታኅሣሥ 12, 2015 በፓሪስ፣ ፈረንሳይ ተካሂዶ ነበር፤ ከ195 አገሮች የተውጣጡ ልዑካን የሰው ልጆች በአየር ንብረት ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ መቀነስ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመወያየት በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ነበር። የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን፣ ሳይንቲስቶችን፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችንና ነጋዴዎችን ጨምሮ ወደ 38,000 የሚጠጉ ሰዎች በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተዋል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በአቅራቢያው የሚገኝን መረጃ መስጫ ጣቢያ በመጎብኘት ስለ አየር ንብረት ለውጥ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በኮንፈረንሱ ባይካፈሉም የአየር ንብረት መለወጡ ያሳስባቸዋል። በፓሪስ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወደፊት ፕላኔታችን ከብክለት ነፃ እንደምትሆን የሚናገረውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ ለሰዎች ለማካፈል ሲሉ በልዩ ዘመቻ ተካፍለዋል።

አንዲት የይሖዋ ምሥክር የሕዝብ መጓጓዣ በምትጠቀምበት ወቅት የፔሩን ባሕላዊ ልብስ ከለበሰ የፔሩ ተወላጅ ጋር ተገናኘች። ሰውየው ውብ በሆነ ተራራ ላይ የሚኖርና ጥሩ ጤንነት ያለው ቢሆንም የፕላኔታችን የወደፊት ተስፋ እንደሚያሳስበው ገለጸ። በተነገረው አስደሳች ተስፋ ልቡ የተነካ ሲሆን www.isa4310.com ወደተባለው ድረ ገጻችን የሚወስደውን የአድራሻ ካርድ በደስታ ተቀብሏል።

ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በባቡር ሲጓዙ ከአንድ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስት ጋር ይገናኛሉ። ይህ ግለሰብ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሯቸው አዳዲስ ሕንፃዎችን ሲገነቡ የሕንፃዎቹ ንድፍም ሆነ አሠራር አካባቢን የማይጎዳ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉና ለዚህም ግሪን ቢልዲንግ ኢኒሼቲቭ ከተባለው ድርጅት ሁለት ጊዜ ከፍተኛውን የግሪን ግሎብ ሽልማት እንደተቀበሉ ሲሰማ ተገረመ። ይህ ሰውም ቢሆን የተሰጠውን የአድራሻ ካርድ በደስታ ተቀብሏል።

ብዙዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች አካባቢውን ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ስለተገረሙ ድረ ገጻችንን ለመጎብኘት ቃል ገብተዋል። ከካናዳ የመጣች አንዲት ልዑክ የይሖዋ ምሥክሮች በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ አዲሱን ዋና መሥሪያ ቤታቸውን ሲገነቡ በአካባቢው ያሉት ኢስተርን ብሉበርድ የተባሉ ወፎች ከመኖሪያቸው እንዳይፈናቀሉ ለመከላከል ያደረጉትን ጥረት ስትሰማ እንዲህ ብላለች፦ “የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ከመሆኔ በፊት የወፎች ጥናት ባለሙያ ነበርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች ለዱር እንስሳት ጥበቃ ይህን ያህል ትኩረት እንደሚሰጡ አላውቅም ነበር። ከዚህ በኋላ ጽሑፎቻችሁን በማንበብ እንዲሁም ድረ ገጻችሁን በመጎብኘት ስለ እናንተ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አደርጋለሁ!”