በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለአንድ ሰው የተጀመረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለብዙዎች ተረፈ

ለአንድ ሰው የተጀመረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለብዙዎች ተረፈ

 ማርታ በጓቴማላ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ናት፤ ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመናገር ስትል ኬክቺ የተባለውን ቋንቋ እየተማረች ነው። አንድ ቀን ከሆስፒታል የሚወጣ አንድ ሰው አየች። ሰውየው በተራራማ አካባቢ ካለ የኬክቺ መንደር የመጣ እንደሆነ ጠረጠረች፤ በዚህ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙም አልሰበኩም። ማርታ ወደ ሰውየው ቀርባ በተሰባበረ የኬክቺ ቋንቋ አነጋገረችው።

 ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ለሰውየው ግብዣ አቀረበችለት። ሰውየው ግብዣውን በደስታ ቢቀበልም ለጥናቱ የሚከፍለው ገንዘብ እንደሌለው ነገራት። ማርታም የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምሩት ያለክፍያ እንደሆነ ነገረችው። በተጨማሪም በስልክ ማጥናት እንደሚችል እንዲሁም መላው ቤተሰቡ በጥናቱ መካፈል እንደሚችል ገለጸችለት። ሰውየውም በዚህ ተስማማ። ሰውየው ስፓንኛ መናገርና ማንበብ ስለሚችል ማርታ በስፓንኛ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠችው። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በኬክቺ ቋንቋ ሰጠችው። በቀጣዩ ሳምንት ላይ ሰውየው፣ ባለቤቱና ሁለት ልጆቻቸው ከማርታ ጋር በስልክ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። የሚያጠኑት በሳምንት ሁለት ጊዜ ነበር። ማርታ እንዲህ ብላለች፦ “ኬክቺ በደንብ ስለማልችል የምናጠናው በስፓንኛ ነበር፤ ሰውየው የምናጠናውን ለባለቤቱ ይተረጉምላታል። ልጆቹ ስፓንኛ ይገባቸዋል።”

 ሰውየው የአንድ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና የተማራቸውን ነገሮች ለምዕመናኑ ማስተማር ጀመረ። ምዕመናኑም በሚያስተምራቸው ነገር ስለተደሰቱ ይህን አዲስ ትምህርት ያገኘው ከየት እንደሆነ ጠየቁት። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠና እንደሆነ ሲነግራቸው እነሱም አንድ በአንድ በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ 15 ያህል ሰዎች በየሳምንቱ ከማርታ ጋር በስልክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይሰበሰቡ ጀመር። በኋላ ላይ ደግሞ ሁሉም ሰው ውይይቱን መስማት እንዲችል ስልኩ አጠገብ ማይክሮፎን አስቀመጡ።

 ማርታ ስለ ጥናቱ ለጉባኤዋ ሽማግሌዎች ስትነግራቸው አንደኛው የጉባኤ ሽማግሌ ተማሪዎቹን ለመጠየቅ ወደ መንደራቸው ሄደ። ከዚያም ሽማግሌው፣ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች a በሌላ መንደር ውስጥ በሚሰጠው የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ ጋበዛቸው፤ ወደ ቦታው ለመድረስ በመኪና ለአንድ ሰዓት ያህል ከሄዱ በኋላ በእግራቸው ለሁለት ሰዓት ያህል መጓዝ ነበረባቸው። ተማሪዎቹ ወደዚያ ለመሄድ የተስማሙ ሲሆን ከመካከላቸው 17ቱ በስብሰባው ላይ ተገኙ።

 ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቹና አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተማሪዎቹ ወዳሉበት መንደር ሄደው አራት ቀን አሳለፉ። በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ፣ jw.org ላይ የወጡ በኬክቺ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቪዲዮዎችን ይመለከቱ ነበር፤ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የተባለውን ብሮሹር ያጠናሉ። ከሰዓት በኋላ ደግሞ JW ብሮድካስቲንግ ላይ የወጡ የተለያዩ ቪዲዮዎችን ያያሉ። በተጨማሪም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እያንዳንዳቸውን በግለሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናቸው ሰው እንዲኖር ዝግጅት አደረገ።

 በእነዚያ አራት ቀናት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮቹ በአቅራቢያው ባሉ የኬክቺ መንደሮች የሰበኩ ከመሆኑም ሌላ ሰዎቹን በአንድ ልዩ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋበዟቸው። በስብሰባው ላይ ለተገኙት 47 ሰዎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት እንደሚችሉ ነገሯቸው። አሥራ አንድ ቤተሰቦች ግብዣውን ተቀበሉ።

 ከጥቂት ወራት በኋላ የጉባኤ ሽማግሌዎቹ፣ መጀመሪያ ማጥናት የጀመረው ሰው በሚኖርበት መንደር በየሳምንቱ ስብሰባ እንዲካሄድ ዝግጅት አደረጉ። በአሁኑ ወቅት 40 የሚያህሉ ሰዎች በስብሰባው ላይ አዘውትረው ይገኛሉ። የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዚያ መንደር በተከበረበት ወቅት 91 ሰዎች በበዓሉ ላይ መገኘታቸው ወንድሞችን አስደስቷቸዋል።

 ማርታ ይህ ሁሉ የጀመረበትን መንገድ እና አሁን የደረሰበትን ደረጃ ስታስብ እንዲህ ትላለች፦ “ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ፣ ማድረግ የምችለው ነገር ውስን እንደሆነ ይሰማኛል። ሆኖም አምላክ ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቀምብን ይችላል። የእነዚያን ሰዎች ልብ ተመልክቶ ወደ ሕዝቡ ስቧቸዋል። ይሖዋ እንደሚወዳቸው ጥርጥር የለውም።”

a የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚባለው ወደ 20 ገደማ ጉባኤዎችን ያቀፈ ወረዳን እንዲጎበኝ የሚሾም የይሖዋ ምሥክር ነው።