በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሦስት ማዕዘን ምልክት

ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሦስት ማዕዘን ምልክት

 በፈረንሳይ የምትኖረው ሞድ የምትሠራው በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን በዚያም አካል ጉዳተኛ ለሆኑ ልጆች እገዛ ታደርጋለች። ከጥቂት ጊዜ በፊት በአንድ ክፍል ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ናዚዎች ስላደረሱት እልቂትና ስለ ማጎሪያ ካምፖች እየተማሩ ነበር። በካምፑ ውስጥ የታሰሩ እስረኞች በደንብ ልብሳቸው ላይ ቀለም ያለው ጨርቅ ይሰፋላቸው ነበር። የጨርቁ ቅርጽና ቀለም ግለሰቡ የታሰረበትን ምክንያት ያሳያል።

 አስተማሪው ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሦስት ማዕዘን ምልክት ስለሚያደርጉት እስረኞች ሲናገር “ይሄ ግብረ ሰዶማውያን የሚያደርጉት ምልክት መሰለኝ” አለ። ክፍለ ጊዜው ካለቀ በኋላ ሞድ ወደ አስተማሪው ሄዳ ናዚዎች ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሦስት ማዕዘን ምልክት የሚሰጡት ለይሖዋ ምሥክሮች እንደነበረ ነገረችው። a ከዚያም ስለዚህ ጉዳይ የሚናገር ጽሑፍ ልታመጣለት እንደምትችል ገለጸችለት። አስተማሪውም በሐሳቧ ተስማማ፤ እንዲያውም ሞድ ስለዚህ ጉዳይ ለተማሪዎቹ ገለጻ እንድትሰጥ ጠየቃት።

 በሌላ ጊዜ ደግሞ አንዲት አስተማሪ ይህንኑ ትምህርት ስታስተምር እስረኞቹ የሚያደርጓቸውን ምልክቶች የሚያሳይ ሰንጠረዥ ተጠቅማ ነበር። ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሦስት ማዕዘን ምልክት የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ በሰንጠረዡ ላይ በትክክል ተገልጿል። የትምህርት ክፍለ ጊዜው ሲያበቃ ሞድ ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ አንዳንድ መረጃዎች ልታካፍላት እንደምትችል ለአስተማሪዋ ነገረቻት። አስተማሪዋ መረጃዎቹን ከተቀበለች በኋላ ሞድ ለተማሪዎቹ ማብራሪያ እንድትሰጥ ዝግጅት አደረገች።

ሞድ የተጠቀመችባቸውን ጽሑፎችና ቪዲዮ በእጇ ይዛ

 ሞድ ለመጀመሪያው ክፍል ተማሪዎች የ15 ደቂቃ ገለጻ ለመስጠት ተዘጋጅታ ነበር፤ ሆኖም የምታቀርብበት ሰዓት ሲደርስ “ሙሉውን ሰዓት መጠቀም ትችያለሽ” ተባለች። ሞድ በመጀመሪያ ናዚዎች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስላደረሱት ስደት የሚገልጽ ጥናታዊ ፊልም አሳየች። ፊልሙ ናዚዎች 800 የይሖዋ ምሥክር ልጆችን ከወላጆቻቸው ነጥቀው እንደወሰዱ ሲገልጽ ሞድ ፊልሙን አቆመችና ከእነዚህ ልጆች መካከል የሦስቱን የሕይወት ታሪክ አነበበች። ሞድ ፊልሙ ካለቀ በኋላ፣ ጌርሃርት ሽታይናከር የተባለ አንድ የ19 ዓመት ኦስትሪያዊ የይሖዋ ምሥክር በ1940 በናዚዎች ከመገደሉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ለወላጆቹ የጻፈውን የስንብት ደብዳቤ በማንበብ ደመደመች። b

 ሞድ ለሁለተኛው ክፍልም ተመሳሳይ ማብራሪያ ሰጠች። ሞድ ያሳየችው ድፍረት ሁለቱም አስተማሪዎች በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ስለደረሰው እልቂት ሲያስተምሩ የይሖዋ ምሥክሮችን መጥቀስ እንዳይረሱ ምክንያት ሆኗል።

a በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቢበልፎርሸር (የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች) በመባል የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች ናዚዎችን ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ታስረው ነበር።

b ጌርሃርት ሽታይናከር ሞት የተፈረደበት፣ የጀርመን ወታደር ለመሆን ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው። የጻፈው የስንብት ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ “ገና ልጅ ነኝ። ልጸና የምችለው ጌታ ካበረታኝ ብቻ ነው፤ የምለምነውም ይህንኑ ነው።” በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ላይ ጌርሃርት ተገደለ። በመቃብሩ ላይ ያለው ጽሑፍ “አምላክን ለማስከበር ሲል ሞቷል” ይላል።