በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከልብስ ማጠቢያ ማሽን ሥር የተቀመጡ ማስታወሻዎች

ከልብስ ማጠቢያ ማሽን ሥር የተቀመጡ ማስታወሻዎች

 ዘሪና ሩሲያ ውስጥ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ እምነቷን ለሁለት ሴት ልጆቿ ለማስተማር ስትል በማዕከላዊ አውሮፓ ወደሚገኘው የትውልድ አገሯ ተመለሰች። በነበረባት የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ከወላጆቿ፣ ከወንድሟና ከባለቤቱ ጋር ትኖር ነበር። ወላጆቿ መጽሐፍ ቅዱስን ለልጆቿ እንዳታስተምር ከለከሏት። ልጆቿንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከእናታቸው ጋር እንዳይነጋገሩ አዘዋቸው ነበር።

 ዘሪና ልጆቿን ስለ ይሖዋ ማስተማር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ታስብ ጀመር። (ምሳሌ 1:8) እንዲሁም ጥበብና አመራር እንዲሰጣት ወደ ይሖዋ አጥብቃ ትጸልይ ነበር። ከዚያም ከጸሎቷ ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድ ስትል ከልጆቿ ጋር በእግር እየተንሸራሸረች ድንቅ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ትነግራቸው ነበር። እንዲህ ማድረጓ ልጆቿ ስለ ፈጣሪ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው አደረገ።

 ቀጥሎም ዘሪና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? a የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ልጆቿን ይበልጥ ለማስተማር የሚያስችል ዘዴ ቀየሰች። በመጽሐፉ ላይ የሚገኙትን አንቀጾችና ጥያቄዎች ወረቀት ላይ ትገለብጥ ነበር። ከዚያም ልጆቿ ሐሳቡ ይበልጥ እንዲገባቸው ለመርዳት ተጨማሪ ሐሳቦችን ትጽፋለች። ቀጥሎም ወረቀቶቹን ከእርሳስ ጋር አድርጋ መታጠቢያ ቤት ውስጥ በሚገኘው የልብስ ማጠቢያ ማሽን ሥር ትደብቃቸዋለች። ልጆቿ መታጠቢያ ቤት ሲገቡ አንቀጾቹን አንብበው የጥያቄዎቹን መልስ ይጽፋሉ።

 ዘሪና ይህን ዘዴ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ሁለት ምዕራፎችን አስጠናቻቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን እሷና ልጆቿ ለብቻቸው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻቸ። በመሆኑም ልጆቿን ያለምንም ተቃውሞ ማስተማር ቻለች። ጥቅምት 2016 ሁለቱም ልጆቿ ተጠመቁ፤ እናታቸው እነሱን በመንፈሳዊ ለመመገብ ስትል ጥበብና ብልሃት በመጠቀሟ ደስተኞች ናቸው።

a አሁን በስፋት የምንጠቀመው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ነው።