በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የቃል ኪዳኑ ታቦት ምንድን ነው?

የቃል ኪዳኑ ታቦት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የቃል ኪዳኑ ታቦት የጥንት እስራኤላውያን አምላክ በሰጠው መመሪያና ንድፍ መሠረት የሠሩት የሣጥን ቅርጽ ያለው ቅዱስ ዕቃ ነበር። “ምሥክሩ” ማለትም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ የተጻፉት አሥርቱ ትእዛዛት የሚቀመጡት በዚህ ታቦት ውስጥ ነበር።—ዘፀአት 25:8-10, 16፤ 31:18

  •   አሠራሩ። ታቦቱ ርዝመቱ 2.5 ክንድ፣ ወርዱ 1.5 ክንድ እንዲሁም ከፍታው 1.5 ክንድ (111 x 67 x 67 ሳንቲ ሜትር) ነበር። ታቦቱ የተሠራው ከግራር እንጨት ነው፤ ውስጡም ሆነ ውጩ በወርቅ የተለበጠ ሲሆን ጠርዙ ጌጥ ነበረው። መክደኛው ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሠራ ሲሆን ጫፍና ጫፉ ላይ የተሠሩ ሁለት የወርቅ ኪሩቦች ነበሩት። የኪሩቦቹ ፊት ወደ መክደኛው ያጎነበሰ ሲሆን ክንፎቻቸው ደግሞ ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን ይከልሉ ነበር። ታቦቱ ከእግሮቹ በላይ አራት የወርቅ ቀለበቶች ነበሩት። ከግራር እንጨት ተሠርተው በወርቅ የተለበጡ መሎጊያዎች በቀለበቶቹ ውስጥ በመግባት ታቦቱን ለመሸከም ያገለግሉ ነበር።—ዘፀአት 25:10-21፤ 37:6-9

  •   የሚቀመጥበት ቦታ። ታቦቱ በመጀመሪያ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ባለው ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይቀመጥ ነበር፤ የማደሪያ ድንኳኑ የተሠራው ታቦቱ በተሠራበት ወቅት ሲሆን የአምልኮ ቦታ ሆኖ የሚያገለግል ተንቀሳቃሽ ድንኳን ነበር። ቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ካህናቱና ሕዝቡ እንዳያዩት ሲባል በመጋረጃ ይከለል ነበር። (ዘፀአት 40:3, 21) እዚህ ክፍል ውስጥ ገብቶ ታቦቱን ማየት የሚችለው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ሲሆን እሱም ወደዚያ የሚገባው በዓመት አንድ ጊዜ ማለትም በስርየት ቀን ብቻ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:2፤ ዕብራውያን 9:7) በኋላ ደግሞ ታቦቱ ሰለሞን በሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን ተወሰደ።—1 ነገሥት 6:14, 19

  •   ዓላማው። ታቦቱ እስራኤላውያንን አምላክ በሲና ተራራ ከእነሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ወይም ስምምነት የሚያስታውሷቸውን ቅዱስ ዕቃዎችን ለማስቀመጥ ያገለግል ነበር። በተጨማሪም በስርየት ቀን በሚኖረው ዝግጅት ላይ ቁልፍ ሚና ይጫወት ነበር።—ዘሌዋውያን 16:3, 13-17

  •   በውስጡ የሚቀመጡ ነገሮች። በታቦቱ ውስጥ በመጀመሪያ የተቀመጡት አሥርቱ ትእዛዛት የተቀረጸባቸው የድንጋይ ጽላቶች ነበሩ። (ዘፀአት 40:20) መና የያዘው የወርቅ ማሰሮ እና “ያቆጠቆጠችው የአሮን በትር” ደግሞ በኋላ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገዋል። (ዕብራውያን 9:4፤ ዘፀአት 16:33, 34፤ ዘኁልቁ 17:10) ከጊዜ በኋላ ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲወሰድ ማሰሮውና በትሩ በታቦቱ ውስጥ አልነበሩም፤ በሆነ ወቅት ላይ ከታቦቱ ውስጥ እንዲወጡ ሳይደረግ አይቀርም።—1 ነገሥት 8:9

  •   የሚጓጓዝበት መንገድ። ሌዋውያኑ ከግራር እንጨት በተሠሩት መሎጊያዎች በመጠቀም ታቦቱን በትከሻቸው ላይ ይሸከሙ ነበር። (ዘኁልቁ 7:9፤ 1 ዜና መዋዕል 15:15) መሎጊያዎቹ ሁልጊዜም የሚቀመጡት ከታቦቱ ጋር ተያይዘው ስለሆነ ሌዋውያኑ ታቦቱን ፈጽሞ አይነኩም ነበር። (ዘፀአት 25:12-16) ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየው ‘የሚከልለው መጋረጃ’ ታቦቱ በሚጓጓዝበት ጊዜ ታቦቱን ለመሸፈን ያገለግል ነበር።—ዘኁልቁ 4:5, 6 a

  •   የሚወክለው ነገር። ታቦቱ ከአምላክ መገኘት ጋር ተዛማጅነት ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ በቅድስተ ቅዱሳኑና እስራኤላውያን በሚሰፍሩባቸው ቦታዎች በታቦቱ ላይ ደመናው መታየቱ ይሖዋ አብሯቸው እንዳለና በረከቱ እንዳልተለያቸው ያመለክት ነበር። (ዘሌዋውያን 16:2፤ ዘኁልቁ 10:33-36) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ከኪሩቤል በላይ በዙፋን” እንደተቀመጠ ይናገራል፤ እዚህ ላይ “ከኪሩቤል በላይ” ሲል በታቦቱ መክደኛ ላይ ያሉትን ኪሩቦች ማመልከቱ ነው። (1 ሳሙኤል 4:4፤ መዝሙር 80:1) ስለሆነም እነዚህ ኪሩቦች የይሖዋ ‘ሠረገላ ምስል’ ወይም ምሳሌ ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 28:18) ንጉሥ ዳዊት ታቦቱ ወደ ጽዮን ከተወሰደ በኋላ ይሖዋ ‘በጽዮን እንደሚኖር’ የተናገረው ታቦቱ ከሚወክለው ነገር አንጻር ነበር።—መዝሙር 9:11

  •   የተጠራባቸው መንገዶች። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሣጥን ቅርጽ ያለው ቅዱስ ዕቃ ለማመልከት የተለያዩ መጠሪያዎችን ተጠቅሟል፤ ከእነዚህም መካከል ‘የምሥክሩ ታቦት፣’ ‘የቃል ኪዳኑ ታቦት፣’ ‘የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት’ እንዲሁም ‘የይሖዋ ብርታት ታቦት’ የሚሉት ይገኙበታል።—ዘኁልቁ 7:89፤ ኢያሱ 3:6, 13፤ 2 ዜና መዋዕል 6:41

     የታቦቱ መክደኛ “የስርየት መክደኛ” ተብሎ ይጠራ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:11) ይህ ስያሜ መክደኛው በስርየት ቀን የሚሰጠውን ልዩ አገልግሎት የሚያመለክት ነው፤ የእስራኤል ሊቀ ካህናት በስርየት ቀን መሥዋዕት የሚደረጉትን እንስሳት ደም ወደ መክደኛውና በመክደኛው ፊት ይረጭ ነበር። ሊቀ ክህናቱ እንዲህ በማድረግ ‘የራሱን፣ የቤቱንና የመላውን የእስራኤል ጉባኤ’ ኃጢአት ያስተሰርያል ወይም ይሸፍናል።—ዘሌዋውያን 16:14-17

የቃል ኪዳኑ ታቦት አሁንም አለ?

 ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከታቦቱ ጋር ዝምድና ያለው ቃል ኪዳን በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ በተመሠረተ “አዲስ ቃል ኪዳን” ስለተተካ ታቦቱ አስፈላጊ መሆኑ እንደቀረ ይናገራል። (ኤርምያስ 31:31-33፤ ዕብራውያን 8:13፤ 12:24) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የቃል ኪዳኑ ታቦት የማያስፈልግበት ጊዜ እንደሚመጣና የአምላክ ሕዝቦች ታቦቱ ባለመኖሩ ምንም እንደጎደላቸው እንደማይሰማቸው በትንቢት ተናግሯል።—ኤርምያስ 3:16

 ሐዋርያው ዮሐንስ አዲሱ ቃል ኪዳን ከተቋቋመ በኋላ ባየው አንድ ራእይ ላይ የቃል ኪዳኑ ታቦት በሰማይ ታይቶ ነበር። (ራእይ 11:15, 19) ይህ ምሳሌያዊ ታቦት የአምላክን መገኘትና አምላክ አዲሱን ቃል ኪዳን እንደባረከው የሚያሳይ ነው።

ታቦቱ የተለየ ኃይል ነበረው?

 አልነበረውም። ታቦቱ መኖሩ በራሱ ሁሉ ነገር እንዲቃና ያደርጋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ከጋይ ሰዎች ጋር ሲዋጉ ታቦቱን ይዘው የነበረ ቢሆንም አንድ እስራኤላዊ በፈጸመው ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ምክንያት በጦርነት ተሸንፈዋል። (ኢያሱ 7:1-6) ከጊዜ በኋላም ከፍልስጤማውያን ጋር ሲዋጉ የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ጦር ሜዳው ይዘውት የሄዱ ቢሆንም በፍልስጤማውያን ተሸንፈዋል። ድል የተመቱት እስራኤላውያኑ ካህናት ሆፍኒ እና ፊንሃስ በሚፈጸሙት መጥፎ ድርጊት ምክንያት ነበር። (1 ሳሙኤል 2:12፤ 4:1-11) ፍልስጤማውያን በዚያ ጦርነት ታቦቱን ማርከው ወሰዱ፤ ሆኖም ታቦቱን ወደ እስራኤል እስኪመልሱ ድረስ አምላክ በመቅሰፍት መታቸው።—1 ሳሙኤል 5:11–6:5

የቃል ኪዳኑ ታቦት ታሪክ

ዓመት (ዓ.ዓ.)

ክንውን

1513

ባስልኤልና ረዳቶቹ እስራኤላውያን መዋጮ ያደረጓቸውን ዕቃዎች በመጠቀም ታቦቱን ሠሩ።—ዘፀአት 25:1, 2፤ 37:1

1512

ሙሴ ታቦቱና የማደሪያ ድንኳኑ ለይሖዋ አገልግሎት እንዲቀደሱ አደረገ፤ የክህነት ሥርዓቱም ጀመረ።።—ዘፀአት 40:1-3, 9, 20, 21

1512—ከ1070 በኋላ

ወደተለያዩ ቦታዎች ተወሰደ።—ኢያሱ 18:1፤ መሳፍንት 20:26, 27፤ 1 ሳሙኤል 1:24፤ 3:3፤ 6:11-14፤ 7:1, 2

ከ1070 በኋላ

ንጉሥ ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው።—2 ሳሙኤል 6:12

1026

በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የሰለሞን ቤተ መቅደስ ተወሰደ።—1 ነገሥት 8:1, 6

642

ንጉሥ ኢዮስያስ ወደ ቤተ መቅደሱ መልሶ አመጣው።—2 ዜና መዋዕል 35:3 b

ከ607 በፊት

ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ እንደነበር ግልጽ ነው። በ607 ዓ.ዓ. ቤተ መቅደሱ በፈራረሰበት ወቅት ከቤተ መቅደሱ ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት ዕቃዎች ዝርዝር ውስጥ አይገኝም፤ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት ዕቃዎች ዝርዝር ውስጥም ቢሆን አልተጠቀሰም።—2 ነገሥት 25:18፤ ዕዝራ 2:1

63

ሮማዊው ጄኔራል ፖምፒ ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን በተመለከተበት ወቅት ታቦቱ እንደሌለ ተናግሯል። c

a እስራኤላውያን ታቦቱን ከማጓጓዝና ከመሸፈን ጋር በተያያዘ የአምላክን ሕግ ችላ በማለታቸው አስከፊ መዘዝ ደርሶባቸው ነበር።—1 ሳሙኤል 6:19፤ 2 ሳሙኤል 6:2-7

b መጽሐፍ ቅዱስ ታቦቱ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ የነበረው መቼ፣ ለምን ወይም በማን እንደሆነ አይናገርም።

c በታሲተስ የተዘጋጀውን ዘ ሂስትሪስ፣ ጥራዝ 5 አንቀጽ 9 ተመልከት።