በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታላቂቱ ባቢሎን ማን ናት?

ታላቂቱ ባቢሎን ማን ናት?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸችው ታላቂቱ ባቢሎን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች በቡድን ደረጃ ታመለክታለች። a (ራእይ 14:8፤ 17:5፤ 18:21) እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች በተወሰነ ደረጃ በመካከላቸው ልዩነት ቢኖርም ሁሉም፣ ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ እንዲርቁ አድርገዋል።—ዘዳግም 4:35

የታላቂቱ ባቢሎንን ማንነት ለማወቅ የሚያስችሉ አገላለጾች

  1.   ታላቂቱ ባቢሎን ምሳሌያዊ ናት። መጽሐፍ ቅዱስ “አንዲት ሴት” እና “ታላቂቱ አመንዝራ” ብሎ የሚጠራት ከመሆኑም ሌላ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል “ሚስጥራዊ” ስም እንዳላት ይገልጻል። (ራእይ 17:1, 3, 5) የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው “በምልክቶች” እንደ መሆኑ መጠን ታላቂቱ ባቢሎን የሚለው ስያሜም ቃል በቃል አንዲትን ሴት ሊያመለክት እንደማይችል ግልጽ ነው። (ራእይ 1:1) በተጨማሪም ‘በብዙ ውኃዎች ላይ እንደተቀመጠች’ እና እነዚህ ውኃዎች ደግሞ “ወገኖችን፣ ብዙ ሕዝብን፣ ብሔራትንና ቋንቋዎችን” እንደሚያመለክቱ ተገልጿል። (ራእይ 17:1, 15) መቼም አንዲት ሴት እንዲህ ልታደርግ እንደማትችል የታወቀ ነው።

  2.   ታላቂቱ ባቢሎን ዓለም አቀፍ ድርጅትን የምትወክል ናት። ‘በምድር ነገሥታት ላይ መንግሥት ያላት ታላቂቱ ከተማ’ ተብላ ተጠርታለች። (ራእይ 17:18) ይህ አገላለጽ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳላትና በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ እንደምታሳድር የሚያሳይ ነው።

  3.   ታላቂቱ ባቢሎን የሃይማኖት ድርጅት እንጂ የፖለቲካ ወይም የንግድ ድርጅት አይደለችም። የጥንቷ ባቢሎን ሃይማኖታዊ በሆኑ ድርጊቶች የተሞላች ከተማ ስትሆን በውስጧ በሚፈጸመው ‘ድግምትና ጥንቆላ’ ትታወቅ ነበር። (ኢሳይያስ 47:1, 12, 13፤ ኤርምያስ 50:1, 2, 38) እንዲያውም በዚህች ከተማ ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በቀጥታ የሚቃወም ሃይማኖታዊ ተግባር ይፈጸም ነበር። (ዘፍጥረት 10:8, 9፤ 11:2-4, 8) የባቢሎን መሪዎች ራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ ለይሖዋም ሆነ ለእሱ አምልኮ ንቀት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ኢሳይያስ 14:4, 13, 14፤ ዳንኤል 5:2-4, 23) በተመሳሳይም ታላቂቱ ባቢሎን ‘በመናፍስታዊ ድርጊቶቿ’ ትታወቃለች። ይህም ሃይማኖታዊ ድርጅት መሆኗን ያሳያል።—ራእይ 18:23

     ታላቂቱ ባቢሎን የፖለቲካ ድርጅት ልትሆን አትችልም፤ ምክንያቱም እሷ ስትጠፋ ‘የምድር ነገሥታት’ እንዳለቀሱ ተገልጿል። (ራእይ 17:1, 2፤ 18:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የምድር ነጋዴዎችን’ ከእሷ ለይቶ ስለሚጠቅስ የንግድ ድርጅት ልትሆን አትችልም።—ራእይ 18:11, 15

  4. የባቢሎን ንጉሥ የናቦኒደስ ሐውልት ሲን፣ ሻማሽና ኢሽታር ከሚባሉት ሦስት ጣምራ አማልክት ጋር

      ታላቂቱ ባቢሎን የሚለው ስያሜ ለሐሰት ሃይማኖቶች ተስማሚ መጠሪያ ነው። የሐሰት ሃይማኖት፣ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ከማስተማር ይልቅ ሌሎች አማልክትን እንዲያመልኩ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ድርጊት “መንፈሳዊ ምንዝር” በማለት ይጠራዋል። (ዘሌዋውያን 20:6፤ ዘፀአት 34:15, 16) አምላክ ሥላሴ ነው እና ነፍስ አትሞትም እንደሚሉት ያሉ እምነቶች እንዲሁም ምስሎችን ለአምልኮ እንደመጠቀም ያሉ ልማዶች የመጡት ከጥንቷ ባቢሎን ሲሆን በሐሰት ሃይማኖት ውስጥም ተስፋፍተው ይገኛሉ። በተጨማሪም እነዚህ ሃይማኖቶች አምልኳቸውንና ለዓለም ያላቸውን ፍቅር ጎን ለጎን ለማስኬድ ይሞክራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው የክህደት ድርጊት መንፈሳዊ ምንዝር እንደሆነ ይናገራል።—ያዕቆብ 4:4

     መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎን “ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ” እንደለበሰች እንዲሁም “በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች” እዳጌጠች ይናገራል፤ ይህም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ያላቸውን ሀብትና ይህ ሀብታቸው እንዲታይላቸው የሚያደርጉትን ጥረት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (ራእይ 17:4) ታላቂቱ ባቢሎን “የምድር አስጸያፊ ነገሮች” ማለትም አምላክን የማያስከብሩ ትምህርቶችና ድርጊቶች ምንጭ ናት። (ራእይ 17:5) የሐሰት ሃይማኖት አባላት በሙሉ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚደግፉ ‘ወገኖች፣ ብዙ ሕዝብ፣ ብሔራትና ቋንቋዎች’ ናቸው።—ራእይ 17:15

 ታላቂቱ ባቢሎን ‘በምድር ላይ ለታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም’ ተጠያቂ ናት። (ራእይ 18:24) የሐሰት ሃይማኖቶች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ጦርነትን ሲቆሰቁሱና ሽብርተኝነትን ሲያባብሱ ኖረዋል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋም ለሰዎች አላስተማሩም። (1 ዮሐንስ 4:8) ይህም በዓለም ላይ ለተከሰተው ለአብዛኛው ደም መፋሰስ አስተዋጽኦ አድርጓል። በመሆኑም አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ራሳቸውን ከሐሰት ሃይማኖት በመለየት “ከእሷ ውጡ” የሚለውን ትእዛዝ መፈጸም አለባቸው።—ራእይ 18:4፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-17