በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መዳን ምንድን ነው?

መዳን ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “መዳን” የሚለውን ቃል ከአደጋ ወይም ከጥፋት በሕይወት መትረፍን ለማመልከት የሠሩበት ጊዜ አለ። (ዘፀአት 14:13, 14፤ የሐዋርያት ሥራ 27:20) አብዛኛውን ጊዜ ግን ይህ ቃል የሚያመለክተው ከኃጢአት መዳንን ነው። (ማቴዎስ 1:21) ሞት የኃጢአት ውጤት በመሆኑ ከኃጢአት የዳኑ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል።—ዮሐንስ 3:16, 17 a

መዳን የሚገኘው እንዴት ነው?

 ለመዳን በኢየሱስ ማመን እንዲሁም ይህን እምነት በተግባር ማሳየት ማለትም ትእዛዛቱን መጠበቅ ያስፈልጋል።—የሐዋርያት ሥራ 4:10, 12፤ ሮም 10:9, 10፤ ዕብራውያን 5:9

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነታችን ሕያው እንደሆነ የሚታየው በሥራችን ማለትም በታዛዥነታችን እንደሆነ ይናገራል። (ያዕቆብ 2:24, 26) እንዲህ ሲባል ግን የምንድነው በሥራችን ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምንድነው በአምላክ “ጸጋ” ነው።—ኤፌሶን 2:8, 9

አንድ ሰው የመዳን ተስፋውን ሊያጣ ይችላል?

 አዎ። ከመስመጥ የተረፈ ሰው መልሶ ውኃው ውስጥ ሊወድቅ ወይም ዘሎ ሊገባ እንደሚችል ሁሉ ከኃጢአት የዳነ ሆኖም በእምነት መመላለሱን ያቆመ ሰውም የመዳን ተስፋውን ሊያጣ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ መዳን ያገኙ ክርስቲያኖች ለእምነት ‘ብርቱ ተጋድሎ እንዲያደርጉ’ የሚያሳስበው ለዚህ ነው። (ይሁዳ 3) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መዳን ላገኙ ክርስቲያኖች “የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል።—ፊልጵስዩስ 2:12

አዳኛችን አምላክ ነው ወይስ ኢየሱስ?

 መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛው የመዳን ምንጭ አምላክ እንደሆነ ይናገራል፤ በመሆኑም በተደጋጋሚ ጊዜ “አዳኝ” በማለት ይጠራዋል። (1 ሳሙኤል 10:19፤ ኢሳይያስ 43:11፤ ቲቶ 2:10፤ ይሁዳ 25) በተጨማሪም አምላክ የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ለማዳን የተለያዩ ሰዎችን የተጠቀመ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች “አዳኝ” ብሎ ጠርቷቸዋል። (ነህምያ 9:27፤ መሳፍንት 3:9, 15፤ 2 ነገሥት 13:5) b አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከኃጢአት የምንድንበት ዝግጅት ስላደረገ ኢየሱስም ቢሆን “አዳኝ” ተብሎ ተጠርቷል።—የሐዋርያት ሥራ 5:31፤ ቲቶ 1:4 c

ሁሉም ሰው ይድናል?

 ሁሉም ሰው አይድንም፤ የማይድኑ ሰዎችም አሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:9) ኢየሱስ “የሚድኑት ጥቂቶች ናቸው?” የሚል ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ “በጠባቡ በር ለመግባት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ፤ እላችኋለሁ፦ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይችሉም” በማለት መልስ ሰጥቷል።—ሉቃስ 13:23, 24

ሰዎች ስለ መዳን ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አንደኛ ቆሮንቶስ 15:22 “ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ” ስለሚል የሰው ልጆች በሙሉ ይድናሉ።

 እውነታው፦ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ የሚናገረው ስለ ትንሣኤ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:12, 13, 20, 21, 35) ስለዚህ “ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ” የሚለው አገላለጽ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ሁሉ ይህን በረከት የሚያገኙት በክርስቶስ በኩል እንደሆነ የሚያመለክት ነው።—ዮሐንስ 11:25

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ቲቶ 2:11 አምላክ ‘ሰዎችን ሁሉ እንደሚያድን’ ስለሚናገር መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰዎች እንደሚድኑ ያስተምራል።—የ1954 ትርጉም

 እውነታው፦ በዚህ ጥቅስ ላይ “ሁሉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ሁሉም ዓይነት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። d በመሆኑም ቲቶ 2:11 ላይ ያለው ሐሳብ አምላክ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” ሰዎችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለማዳን ዝግጅት እንዳደረገ የሚጠቁም ነው።—ራእይ 7:9, 10

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:9 አምላክ ‘ማንም እንዲጠፋ እንደማይፈልግ’ ስለሚናገር መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰዎች እንደሚድኑ ያስተምራል።

 እውነታው፦ አምላክ ሰዎች እንዲድኑ ይፈልጋል፤ ሆኖም ለመዳን ያደረገውን ዝግጅት እንዲቀበል ማንንም ሰው አያስገድድም። አምላክ በሚያመጣው “የፍርድ ቀን”፣ ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ይጠፋሉ።’—2 ጴጥሮስ 3:7

a መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው ከኃጢአትና ከሞት የሚድንበት ጊዜ ገና ቢሆንም ግለሰቡ ‘እንደዳነ’ አድርጎ የሚገልጽበት ጊዜ አለ።—ኤፌሶን 2:5፤ ሮም 13:11

b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “አዳኝ” በሚለው ቃል ፋንታ “ታዳጊ”፣ “ነፃ አውጪ”፣ “ጀግና” እና “መሪ” እንደሚሉት ያሉ ቃላትን ተጠቅመዋል። ሆኖም በመጀመሪያው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ውስጥ፣ አዳኝ ስለሆኑ ሰዎች በሚናገርበት ቦታ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል ስለ ይሖዋ አምላክ አዳኝነት በሚናገሩ ሌሎች ጥቅሶች ላይ ከገባው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።—መዝሙር 7:10

c ኢየሱስ የሚለው ስም የሆሹዋ ከሚለው የዕብራይስጥ ስም የመጣ ሲሆን “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

d ቫይንስ ኮምፕሊት ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የሚለውን መጽሐፍ ተመልከት። በማቴዎስ 5:11 ላይ ሰዎች በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ‘ክፉውን ሁሉ በውሸት እንደሚያስወሩባቸው’ የሚገልጽ ዘገባ እናገኛለን፤ እዚህ ላይም ቢሆን “ሁሉ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ሁሉንም ዓይነት” የሚለውን ሐሳብ ያስተላልፋል።—ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ቨርዥን