በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

2 ጢሞቴዎስ 1:7—‘አምላክ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም’

2 ጢሞቴዎስ 1:7—‘አምላክ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም’

 “አምላክ የኃይል፣ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።”—2 ጢሞቴዎስ 1:7 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።”—2 ጢሞቴዎስ 1:7 የ1954 ትርጉም

የ2 ጢሞቴዎስ 1:7 ትርጉም

 አምላክ ሰዎች ትክክለኛውን ነገር የማድረግ ድፍረት እንዲኖራቸው ሊረዳቸው ይችላል። እሱ ማንም ሰው ጤናማ ባልሆነ “ፍርሃት” ተሸንፎ እሱን የሚያስደስት ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዲል አይፈልግም።

 በዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ ፍርሃታችንን እንድናሸንፍ ለመርዳት ሲል የሚሰጠን ሦስት ነገሮች ተገልጸዋል።

 “ኃይል።” ክርስቲያኖች ብዙ አስፈሪ ጠላቶችና አደገኛ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም አምላክን በድፍረት ማገልገል ችለዋል። በፍርሃት ተሸንፈው ወደኋላ አላፈገፈጉም። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) እንዲህ ያለ ድፍረት ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ የረዳቸው ምን እንደሆነ ሲገልጽ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) አምላክ አገልጋዮቹ ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት እንዲችሉ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7

 “ፍቅር።” አንድ ክርስቲያን ለአምላክ ያለው ጥልቅ ፍቅር ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ድፍረት ይሰጠዋል። በተጨማሪም ለሰዎች ያለው ፍቅር ተቃውሞ ወይም ራሱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር እያለም ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት እንዲያስቀድም ያነሳሳዋል።—ዮሐንስ 13:34፤ 15:13

 “ጤናማ አእምሮ።” በጥቅሉ ሲታይ ‘ጤናማ አእምሮ’ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አንድ ክርስቲያን ያለውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ለማመልከት ነው። ይህ ሰው እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ ነው። ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ከባድ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ጊዜም እንኳ ተረጋግቶና ሚዛናዊ ሆኖ ማሰብ ይችላል። ሌሎች ስለ እሱ ካላቸው አመለካከት የበለጠ ቦታ የሚሰጠው ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና እንደሆነ ይገነዘባል፤ በመሆኑም የአምላክን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ውሳኔ ያደርጋል።

የ2 ጢሞቴዎስ 1:7 አውድ

 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን ሁለተኛ ጢሞቴዎስን የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን ይህን ደብዳቤ የጻፈው ውድ ጓደኛውና የሥራ ባልደረባው ለሆነው ለጢሞቴዎስ ነው። በዚህ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን በአገልግሎት በትጋት መካፈሉን እንዲቀጥል አበረታቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:1, 2) ጢሞቴዎስ ዓይናፋርና ቁጥብ የነበረ ይመስላል፤ ይህ ባሕርይ ደግሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ጋር በተያያዘ ሙሉ አቅሙን እንዳይጠቀም እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:12) ጳውሎስ ግን ጢሞቴዎስን ስጦታ ማለትም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ልዩ የአገልግሎት መብት እንደተሰጠው አስታውሶታል። የጉባኤ የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነቱን ሲወጣ፣ ምሥራቹን ሲሰብክና በእምነቱ ምክንያት ፈታኝ ሁኔታዎችን ሲቋቋም መፍራት እንደሌለበት ጢሞቴዎስን አሳስቦታል።—2 ጢሞቴዎስ 1:6-8

 ይህ ደብዳቤ መጀመሪያ የተጻፈው ለጢሞቴዎስ ቢሆንም ሐሳቡ በዛሬው ጊዜ ይሖዋን የሚያገለግሉትን በሙሉ ያበረታታል። የአምላክ አገልጋዮች ማንኛውም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው አምላክ እሱን በተሳካ መንገድ ማገልገል እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ማረጋገጫ ይሰጣል።