በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ሮም 12:12—“በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ”

ሮም 12:12—“በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ”

 “በተስፋው ደስ ይበላችሁ። መከራን በጽናት ተቋቋሙ። ሳትታክቱ ጸልዩ።”—ሮም 12:12 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።”—ሮም 12:12 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የሮም 12:12 ትርጉም

 በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖችን ሦስት ነገሮች እንዲያደርጉ አበረታቷል፤ እነዚህ ሦስት ነገሮች፣ ክርስቲያኖች ስደትንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን በታማኝነት እንዲቋቋሙ ይረዷቸዋል።

 “በተስፋው ደስ ይበላችሁ።” ክርስቲያኖች አስደናቂ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፤ አንዳንዶቹ በሰማይ፣ አብዛኞቹ ደግሞ ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (መዝሙር 37:29፤ ዮሐንስ 3:16፤ ራእይ 14:1-4፤ 21:3, 4) ይህ ተስፋቸው ሲፈጸም የአምላክ መንግሥት a የሰው ልጆችን እያስጨነቁ ያሉ ችግሮችን ሁሉ ሲያስወግድ ያያሉ። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ፈተና ውስጥ እያሉም እንኳ መደሰት ይችላሉ፤ ምክንያቱም ተስፋቸው አስተማማኝ እንደሆነና መጽናታቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያስገኝላቸው እርግጠኞች ናቸው።—ማቴዎስ 5:11, 12፤ ሮም 5:3-5

 “መከራን በጽናት ተቋቋሙ።” መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መጽናት” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ግስ ብዙውን ጊዜ እንዲህ የሚል ፍቺ ይሰጠዋል፦ “ከመሸሽ ይልቅ መጋፈጥ፣ ችሎ መኖር፣ ካሉበት ንቅንቅ አለማለት።” የክርስቶስ ተከታዮች ‘የዓለም b ክፍል ስላልሆኑ’ ስደት እንደሚደርስባቸው ይጠብቃሉ፤ ጽናት የሚያስፈልጋቸው ለዚህ ነው። (ዮሐንስ 15:18-20፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12) አንድ ክርስቲያን በፈተና ውስጥም አምላክን በታማኝነት በማገልገል ሲጸና አምላክ ወሮታውን በመክፈል እንደሚክሰው ያለው እምነት ይጠናከራል። (ማቴዎስ 24:13) ይህ የእርግጠኝነት ስሜት ደግሞ ፈተናዎችን በትዕግሥትና በደስታ እንዲወጣ ይረዳዋል።—ቆላስይስ 1:11

 “ሳትታክቱ ጸልዩ።” ክርስቲያኖች አዘውትረው እንዲጸልዩ በተደጋጋሚ ተበረታተዋል፤ ለአምላክ ምንጊዜም ታማኝ መሆን የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ነው። (ሉቃስ 11:9፤ 18:1) ምንጊዜም አምላክ እንዲመራቸው ይለምኑታል፤ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ በእሱ ይታመናሉ። (ቆላስይስ 4:2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) አምላክን እስከታዘዙትና እሱን ለማስደሰት የሚችሉትን ሁሉ እስካደረጉ ድረስ አምላክ ልመናቸውን እንደሚሰማቸው እርግጠኞች ናቸው። (1 ዮሐንስ 3:22፤ 5:14) ደግሞም ሳይታክቱ መጸለያቸውን ከቀጠሉ አምላክ ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም የሚረዳ ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ያውቃሉ።—ፊልጵስዩስ 4:13

የሮም 12:12 አውድ

 ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በ56 ዓ.ም. ነው። በዚህ ደብዳቤ ምዕራፍ 12 ላይ ለዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚጠቅሟቸው ምክሮች ሰጥቷቸዋል፤ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዴት እንደሚያዳብሩ፣ ከእምነት አጋሮቻቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ እንዲሁም ስደት ሲደርስባቸው እንዴት ሰላማዊ መሆን እንደሚችሉ ነግሯቸዋል። (ሮም 12:9-21) ይህ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ወቅታዊ ምክር ነበር፤ ምክንያቱም ከባድ ተቃውሞ ከፊታቸው ይጠብቃቸው ነበር።

 ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም በ64 ዓ.ም. ሮም ውስጥ የተነሳ የእሳት አደጋ ከተማዋን አወደማት። እሳቱን ያስነሳው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ እንደሆነ የሚገልጽ ወሬ ተዛመተ። የሮም ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ታሲተስ እንደገለጸው ኔሮ ራሱን ነፃ ለማውጣት ጥፋቱን በክርስቲያኖች ላይ አላከከ። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ይህን ተከትሎ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ የስደት ዘመቻ ተነሳ። ጳውሎስ ስደትን በጽናት ስለ መቋቋም አስቀድሞ የሰጣቸው ምክር ያን የፈተና ጊዜ እምነታቸውንና ክብራቸውን ጠብቀው እንዲያልፉት ረድቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:9) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ ትልቅ ትምህርት ያገኛሉ።

 የሮም መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a የአምላክ መንግሥት፣ አምላክ በሰማይ ያቋቋመው መስተዳድር ነው፤ ይህ መስተዳድር የአምላክ ፈቃድ ምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል። ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ከፈለግህ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዓለም” የሚለው ቃል ከአምላክ የራቁ ሰዎችን ያመለክታል።