የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ሉቃስ 2:14—“ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን”
“በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች ሰላም ይሁን።”—ሉቃስ 2:14 አዲስ ዓለም ትርጉም
“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”—ሉቃስ 2:14 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የሉቃስ 2:14 ትርጉም
እነዚህ የውዳሴ ቃላት መላእክት ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት የተናገሯቸው ናቸው፤ በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ የአምላክን ሞገስና ሰላም እንደሚያገኙ ይጠቁማሉ።
“በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን።” መላእክት ይህን ሲናገሩ፣ ክብር ሁሉ ሊሰጠው የሚገባው አምላክ እንደሆነ ማጉላታቸው ነው። ይህ መግለጫ የሚጠቁመን ሌላው ነገር ደግሞ የኢየሱስ መወለድና ምድር ላይ ያከናወነው አገልግሎት ራሱ፣ ለይሖዋ a አምላክ ትልቅ ክብር የሚያመጣ መሆኑን ነው። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ላስተማረው ትምህርት ምንጊዜም እውቅና የሚሰጠው ለአምላክ ነበር፤ “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16-18) ኢየሱስ ተአምር ሲፈጽም የተመለከቱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ‘አምላክን ያመሰግኑ’ ነበር። (ሉቃስ 5:18, 24-26፤ ዮሐንስ 5:19) የኢየሱስ ሞትም እንኳ ለአምላክ ክብር አምጥቷል። ምድር ጻድቅና ሰላም ወዳድ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ አምላክ ያወጣው ታላቅ ዓላማ እንዲፈጸም መንገድ የከፈተው የኢየሱስ ሞት ነው።—ዘፍጥረት 1:28
“በምድርም . . . ሰላም።” እዚህ ላይ የተገለጸው ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም። አንድ ሰው የይሖዋን ሞገስ ሲያገኝ የሚኖረውን ሰላምና ውስጣዊ መረጋጋትም ይጨምራል። ለኢየሱስ ምስጋና ይግባውና የሰው ልጆች ከአምላክ ጋር እንዲህ ዓይነት ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር ችለዋል። (ያዕቆብ 4:8) ወደፊት ደግሞ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ምድርን ሲገዛ በመላው ምድር ላይ ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል።—መዝሙር 37:11፤ ሉቃስ 1:32, 33
“አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች።” ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው በአምላክና እሱ በላከው በኢየሱስ ከልብ በማመናቸው የእሱን ሞገስ ወይም በጎ ፈቃድ ያገኙ ሰዎችን ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደሚያስቀምጡት አምላክ ይህን ሞገሱን የሚያሳየው ክፉ ደግ ሳይል ለሁሉም የሰው ልጆች አይደለም። ጥንታዊና ተአማኒ የሆኑ የግሪክኛ ቅጂዎች ጥቅሱ በአዲሱ ዓለም ትርጉም እና በሌሎች መሰል ዘመናዊ ትርጉሞች ላይ የተቀመጠበትን መንገድ ይደግፋሉ። ሰላም የሚያገኙት አምላክ ሞገስ የሚያሳያቸው ሰዎች ናቸው።—“ ሉቃስ 2:14 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች” የሚለውን ተመልከት።
የሉቃስ 2:14 አውድ
ሉቃስ ምዕራፍ 2 የኢየሱስን የልጅነት ሕይወት ይተርካል። ኢየሱስ እንደተወለደ አንድ መልአክ “ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ [ለሚያድሩ] እረኞች” ተገለጠ። b (ሉቃስ 2:4-8) መልአኩ ለእረኞቹ “ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች” ይዞላቸው እንደመጣ ነገራቸው፤ “በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋልና፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው” አላቸው። (ሉቃስ 2:9-11) እረኞቹ ሕፃኑን የት እንደሚያገኙት ተነገራቸው፤ ከዚያም እጅግ ብዙ መላእክት አምላክን ሲያወድሱ ተመለከቱ። እረኞቹ ቤተልሔም ሲደርሱ ማርያምና ዮሴፍን ከሕፃኑ ኢየሱስ ጋር አገኟቸው። (ሉቃስ 2:12-16) ያጋጠማቸውን አስደናቂ ነገር ተረኩላቸው፤ ከዚያም ስላዩትና ስለሰሙት ነገር ሁሉ “አምላክን እያከበሩና እያወደሱ” ወደ መንጎቻቸው ተመለሱ።—ሉቃስ 2:17-20
ሉቃስ 2:14 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች
“ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት! እግዚአብሔር በጸጋው ላደላቸው ሁሉ በምድር ላይ ሰላም ይሁን።”—ሉቃስ 2:14 ሕያው ቃል
“በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!”—ሉቃስ 2:14 የ1980 ትርጉም
የሉቃስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b እረኞቹ ሌሊት ውጭ እንዳደሩ የሚገልጸው ዘገባ በራሱ እነዚህ ክንውኖች የተፈጸሙት በክረምት ወቅት እንዳልሆነ ይጠቁማል፤ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።