በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

ፖርኖግራፊ ትዳራችሁን ሊያናጋው ይችላል

ፖርኖግራፊ ትዳራችሁን ሊያናጋው ይችላል

 ባለቤቱ ሚስጥሩን አወቀችበት። አጥብቆ ይቅርታ ጠየቃት። እንደሚያቆም ቃል ገባላት፤ ደግሞም ለተወሰነ ጊዜ አቆመ። ከዚያ ግን አገረሸበት። አሁንም ታሪክ ራሱን ደገመ።

 አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞሃል? ከሆነ የፖርኖግራፊ ሱስህ ባለቤትህን የሚጎዳት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህን ሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሸነፍ የምትችለው እንዴት እንደሆነ መማር ይኖርብሃል። a

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

 ፖርኖግራፊ ትዳርን ሊያናጋ ይችላል። በባለትዳሮች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር እንዲሁም ሚስትየዋ ባሏን ማመን እንዲከብዳት ሊያደርግ ይችላል። b

 ፖርኖግራፊ የሚመለከት ባል ያላት ሴት የሚከተሉት ስሜቶች ሊፈጠሩባት ይችላሉ፦

  •   መከዳት። ሣራ የተባለች አንዲት ባለትዳር “ባለቤቴ በተደጋጋሚ ምንዝር የፈጸመ ያህል ሆኖ ተሰማኝ” ብላለች።

  •   ለራስ አክብሮት ማጣት። አንዲት ባለትዳር የባሏ የፖርኖግራፊ ሱስ ‘አስቀያሚ እንደሆነች እንዲሰማትና እንድትሸማቀቅ’ እንዳደረጋት ተናግራለች።

  •   አለመተማመን። ሄለን የተባለች አንዲት ባለትዳር “ባለቤቴ የሚያደርገውን እያንዳንዱን ነገር በጥርጣሬ ዓይን ነው የማየው” ብላለች።

  •   ጭንቀት። ካትሪን የተባለች አንዲት ባለትዳር “ስለ ባለቤቴ የፖርኖግራፊ ሱስ መብሰልሰሌ መላ ሕይወቴን ተቆጣጠረው” ብላለች።

 ሊታሰብበት የሚገባው ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባል ሚስቱን መውደድ እንዳለበት ይናገራል። (ኤፌሶን 5:25) ታዲያ አንድ ባል፣ ሚስቱ ከላይ የተጠቀሱት ስሜቶች እንዲሰሟት ካደረገ በእርግጥ ይወዳታል ሊባል ይችላል?

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

 የፖርኖግራፊ ሱስን ማሸነፍ ቀላል አይደለም። ስቴሲ የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የሲጋራ፣ የማሪዋና እና የአልኮል ሱሱን ማሸነፍ ችሏል። የፖርኖግራፊ ሱሱ ግን አሁንም ድረስ ያታግለዋል።”

 የአንተም ሁኔታ እንደዚህ ከሆነ የሚከተሉት ምክሮች ይህን ሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማሸነፍ ይረዱሃል።

  •   ፖርኖግራፊ መጥፎ የሆነው ለምን እንደሆነ ተረዳ። ፖርኖግራፊ ሰዎች የራስ ወዳድነት ምኞታቸውን ለማርካት እንዲነሳሱ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ለደስተኛ ትዳር ቁልፍ የሆኑትን ፍቅርን፣ መተማመንን እና ታማኝነትን ይሸረሽራል። በተጨማሪም ፖርኖግራፊ መመልከት የትዳር ዝግጅትን ላቋቋመው ለይሖዋ አምላክ አክብሮት የጎደለው ድርጊት ነው።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ጋብቻ ክቡር ይሁን።’—ዕብራውያን 13:4

  •   ለድርጊትህ ኃላፊነት ውሰድ። ‘ሚስቴ ይበልጥ ፍቅር ብታሳየኝ ኖሮ ፖርኖግራፊ አያስፈልገኝም ነበር’ አትበል። ተጠያቂነቱን ወደ ሚስትህ ማዞር በፍጹም አግባብ አይደለም። እንዲሁም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ፣ ሚስትህ ቅር ባሰኘችህ ቁጥር ወደዚህ ሱስ እንድትመለስ ሰበብ ይፈጥራል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።”—ያዕቆብ 1:14

  •   ከሚስትህ ጋር በግልጽና በሐቀኝነት ተነጋገር። ኬቨን የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ሲያጋጥመኝ ማየቴን መቀጠሌን ወይም ፈተናውን ማሸነፌን ለሚስቴ በየቀኑ እነግራታለሁ። በዚህ መልኩ በየቀኑ መነጋገራችን በመካከላችን ምንም ዓይነት ሚስጥር እንዳይኖር አድርጓል።”

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

  •   ምንጊዜም ንቁ ሁን። ሱሱን እንዳሸነፍከው ከተሰማህ ከበርካታ ዓመታት በኋላም ሊያገረሽብህ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኬቨን እንዲህ ብሏል፦ “የፖርኖግራፊ ሱሴ ለአሥር ዓመት ያህል ሳያገረሽብኝ ስለቆየ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንዳሸነፍኩት ተሰምቶኝ ነበር። ለካስ ሱሱ አመቺ ጊዜ ሲያገኝ ብቅ ለማለት ተደብቆ እያደባ ነበር።”

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።”—1 ቆሮንቶስ 10:12

  •   ለማየት ስትፈተን ታገሥ። ፖርኖግራፊ የማየት ምኞት እንዳያድርብህ መከላከል ባትችልም እንኳ ምኞቱን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም መምረጥ ትችላለህ። ምኞቱ ማለፉ አይቀርም፤ በተለይም ሐሳብህ በሌሎች ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ከቻልክ ምኞቱ ቶሎ ብሎ ሊያልፍልህ ይችላል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል በመቆጣጠር እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። ይህም . . . ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።”—1 ተሰሎንቄ 4:4, 5

  •   ልማዱ እንዲያገረሽብህ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ራቅ። ዊልፓወር ኢዝ ኖት ኢነፍ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ ስትገባ ክብሪት እንደለኮስክ ሊቆጠር ይችላል። ትንሽ ነዳጅ ካገኘ . . . እሳቱ ይቀጣጠላል።”

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ማንኛውም ክፉ ነገር በእኔ ላይ አይሠልጥን።”—መዝሙር 119:133

  •   ተስፋ አትቁረጥ። ሚስትህ መልሳ እምነት እስክትጥልብህ ረጅም ጊዜ፣ ምናልባትም ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ሆኖም ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የሚስትህን አመኔታ መልሰህ ማትረፍ ትችላለህ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅር ታጋሽ . . . ነው።”—1 ቆሮንቶስ 13:4

a ይህ ርዕስ በዋነኝነት የሚናገረው ስለ ባሎች ቢሆንም በውስጡ ያሉት ሐሳቦች ፖርኖግራፊ ለሚመለከቱ ሚስቶችም ይሠራሉ።

b አንዳንድ ባለትዳሮች፣ አብረው ፖርኖግራፊ ማየታቸው ጥምረታቸውን እንደሚያጠናክርላቸው ይገልጻሉ። ሆኖም እንዲህ ያለው ልማድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ይጋጫል።—ምሳሌ 5:15-20፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4, 5፤ ገላትያ 5:22, 23