በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

ከመጋባታችን በፊት አብረን ብንኖርስ?

ከመጋባታችን በፊት አብረን ብንኖርስ?

 በርካታ ጥንዶች ከመጋባታቸው በፊት አብረው ይኖራሉ። አንዳንዶች እንዲህ የሚያደርጉት የሚጣጣሙ መሆናቸውን ለመፈተን እንዲሁም የሰመረ ትዳር የመመሥረት ዕድላቸውን ለማሳደግ ነው። ይሁንና ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር የጥበብ እርምጃ ነው?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

  •    መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራል። ለምሳሌ ‘ከፆታ ብልግና ራቁ’ የሚል መመሪያ ይሰጣል። (1 ተሰሎንቄ 4:3፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህም ወደፊት ለመጋባት በማሰብ አብረው በሚኖሩ ጥንዶች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት ይጨምራል። a የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት፣ ጥንዶች ከጋብቻ ውጭ ከሚመጣ እርግዝና እንዲሁም ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር ከሚያስከትላቸው ሌሎች መዘዞች እንዲጠበቁ ያደርጋል።

  •    የጋብቻ ዝግጅትን ያቋቋመው አምላክ ነው። ይህን ዝግጅት ባቋቋመበት ወቅት እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 2:24) የጋብቻ ቃል ኪዳን ፍቅር የሰፈነበትና ዘላቂ የሆነ ቤተሰብ ለመገንባት የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መሠረት ነው።

 አብሮ መኖር ለትዳር ያዘጋጃል?

 አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸዋል። ጥንዶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብረው መሥራታቸውና አንዳቸው የሌላውን ባሕርይ በቅርበት ማየታቸው ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆንላቸው ያስባሉ። ይሁንና የሰመረ ትዳር ለመመሥረት የሚረዳው ዋነኛ ቁልፍ ቃል ኪዳንን ማክበር ነው።

 ጥንዶች በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጊዜ ተጣብቀው ለመኖር የሚረዳቸው ምንድን ነው? ሁለቱም ሰዎች በፈለጉት ሰዓት ግንኙነታቸውን ሊያቋርጡ የሚችሉበት “የሙከራ ጊዜ” ማዘጋጀት ለዚህ አይረዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ሰዎች ቃል ኪዳናቸውን የሚያከብሩ እንዲሁም ችግሮችን ለመፍታት በጋራ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ግንኙነታቸው ይጠናከራል።

 ዋናው ነጥብ፦ ከጋብቻ በፊት አብረው የሚኖሩ ጥንዶች የሚለማመዱት ትዳርን ሳይሆን መለያየትን ሊሆን ይችላል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”​—ገላትያ 6:7

 አብሮ መኖር ለኢኮኖሚ ይጠቅማል?

 አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸዋል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከአሥር አዋቂዎች መካከል አራቱ አብረው መኖር የጀመሩት ገንዘብ ለመቆጠብ እንዲረዳቸው ብለው ነው። ይሁንና ለተወሰነ ጊዜ አብረው ከኖሩ በኋላም ብዙዎቹ ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ ያልሆኑበት ዋነኛ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።

 ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር በተለይ በሴቶች ላይ ሌሎች መዘዞችም ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ከወሰኑ ብዙውን ጊዜ ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት የሚወድቀው በሴቶች ላይ ነው።

 ዋናው ነጥብ፦ ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር የሚያስከትለው መዘዝ፣ አገኛለሁ ብለው ከሚያስቡት ከማንኛውም ጥቅም በእጅጉ ይበልጣል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”​—ኢሳይያስ 48:17

 አብሮ መኖር የማይሆን ሰው ከማግባት ያድናል?

 አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸዋል። ይሁንና ፋይቲንግ ፎር ዩር ሜሬጅ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ከጋብቻ በፊት አብረው የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች፣ አብረው መኖራቸው ግንኙነታቸውን ማቋረጥ ይበልጥ እንዲከብዳቸው እንደሚያደርግ አይገነዘቡም።” ለምን? አብረው መኖር የጀመሩ አንዳንድ ጥንዶች ጨርሶ እንደማይጣጣሙ ያስተውሉ ይሆናል። ሆኖም አብረው የሚያሳድጉት የቤት እንስሳ በመኖሩ፣ ቤታቸውን በጋራ በመግዛታቸው፣ ያልተጠበቀ እርግዝና በመከሰቱ ወይም በሌሎች አስገዳጅ ምክንያቶች የተነሳ ግንኙነታቸውን ማቋረጥ ይከብዳቸዋል። b መጽሐፉ እንደሚገልጸው “ከትዳር በፊት ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ሊወስኑ ይችሉ የነበሩ ሰዎች ሁኔታውን ላለማወሳሰብ ሲሉ ብቻ ትዳር ለመመሥረት ይገደዳሉ።”

 ዋናው ነጥብ፦ አብራችሁ መኖራችሁ ጥሩ ውሳኔ እንድታደርጉ ከመርዳት ይልቅ ከማይሆናችሁ ሰው ጋር ያላችሁን ግንኙነት ማቋረጥ ከባድ እንዲሆንባችሁ ሊያደርግ ይችላል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”​—ምሳሌ 22:3

 የተሻለ አማራጭ ይኖር ይሆን?

 ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር ከሚያስከትላቸው መዘዞች መዳንና የሰመረ ትዳር የመመሥረት ዕድላችሁን መጨመር ትችላላችሁ። እንዴት? ከትዳር ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መሥፈርት በመከተል ነው። እንደ ባልና ሚስት አብራችሁ መኖር ከመጀመራችሁ በፊት ለትዳር ያሰባችሁትን ሰው ጊዜ ወስዳችሁ በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በፆታ መሳሳብ ላይ ተመሥርታችሁ የትዳር አጋር ከመምረጥ ይልቅ ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ መሥፈርትና እምነት ያለው ሰው መምረጣችሁ በእጅጉ የተሻለ ነው።

 የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስደሳችና ዘላቂ ትዳር ለመገንባት የሚያስችል መሠረት እንድትጥሉ ይረዳችኋል። c ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ የሚረዱ መመሪያዎችን ይዟል፦

 እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.org ላይ የሚገኘውን “ትዳር እና ቤተሰብ” የሚለውን ክፍል ተመልከቱ።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም ለማስተማር . . . ይጠቅማሉ።”​—2 ጢሞቴዎስ 3:16

b ፋሚሊ ሪሌሽንስ በሚለው መጽሔት ላይ ከወጣው በስኮት ስታንሊ፣ በጋሊና ክላይን ሮድስ እና በሃዋርድ ማርክማን ከተዘጋጀው “ስላይዲንግ ቨርስስ ዲሳይዲንግ፦ ኢነርሻ ኤንድ ዘ ፕሪማሪታል ኮሃቢቴሽን ኢፌክት” ከሚለው ርዕስ የተወሰደ።

c በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ በመምረጥ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ለየትኞቹ ባሕርያት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል።