በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

ሥራን ሥራ ቦታ መተው

ሥራን ሥራ ቦታ መተው

 በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን አሠሪያችሁ፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁ ወይም ደንበኞቻችሁ ቀንም ሆነ ሌሊት በማንኛውም ሰዓት ሊያገኟችሁ ይፈልጉ ይሆናል። ይህም ሥራችሁንና ሌሎች እንቅስቃሴዎቻችሁን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ ማለትም ትዳራችሁን ጨምሮ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገባቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠት ከባድ እንዲሆንባችሁ ሊያደርግ ይችላል።

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

  •   ቴክኖሎጂ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ልታሳልፉ የሚገባችሁን ጊዜ በሥራ እንድታሳልፉ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ከሥራ ሰዓት ውጭ የሚመጡ የስልክ ጥሪዎችን፣ ኢሜይሎችን ወይም የጽሑፍ መልእክቶችን ወዲያውኑ መመለስ እንዳለባችሁ ይሰማችሁ ይሆናል።

     “ድሮ ድሮ ከሥራ በኋላ ቤት ተመልሶ ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የተለመደ ነገር ነበር፤ አሁን ግን ይህ የማይቻል ነገር ሆኗል። ምክንያቱም ከሥራ ጋር የተያያዙ ኢሜይሎችና የስልክ ጥሪዎች ቤት ድረስ ተከትለውን ስለሚመጡ ትዳራችን ችላ ሊባል ይችላል።”—ጀኔት

  •   ሥራችሁንና የቤተሰብ ሕይወታችሁን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስኬድ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ አለባችሁ። ዕቅድ ካላወጣችሁ ሥራችሁ ለትዳር ጓደኛችሁ የመደባችሁትን ጊዜ መሻማቱ አይቀርም።

     “አብዛኛውን ጊዜ ችላ የምትሉት የመጀመሪያው ሰው የትዳር ጓደኛችሁ ነው። ምክንያቱም ‘እሱ እንኳ ይገባዋል ስለዚህ ይቅር ይለኛል፤ ሥራዬን ስጨርስ አብሬው ጊዜ አሳልፋለሁ’ ብላችሁ ታስባላችሁ።”—ሆሊ

 ሥራችሁንና ሌሎች እንቅስቃሴዎቻችሁን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስኬድ የሚረዱ ምክሮች

  •   ለትዳራችሁ ቅድሚያ ስጡ። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ይላል። (ማቴዎስ 19:6) ማንም ሰው ከትዳር ጓደኛችሁ ‘እንዲለያያችሁ’ የማትፈቅዱ ከሆነ ሥራችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ እንዲለያያችሁ ለምን ትፈቅዳላችሁ?

     “አንዳንድ ደንበኞች ገንዘብ ስለሚከፍሏችሁ ብቻ በፈለጓችሁ ጊዜ ሁሉ ሊያገኟችሁ እንደሚገባ ይሰማቸዋል። ሆኖም ለትዳሬ ቅድሚያ መስጠት እንዳለብኝ ስለማውቅ ሥራ በማልሠራባቸው ቀናት ሊያገኙኝ እንደማይችሉ ሥራ ስገባ ግን ጥያቄያቸውን እንደማስተናግድ እነግራቸዋለሁ።”—ማርክ

     ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ የማደርጋቸው ነገሮች ትዳሬን ከሥራዬ እንደማስበልጥ ይጠቁማሉ?

  •   አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አይሆንም በሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2) ልካችሁን ማወቃችሁ አንዳንድ ሥራዎችን ላለመቀበል ወይም ለሌሎች ሰዎች ለመስጠት እንድትወስኑ ሊያደርጋችሁ ይችላል።

     “የቧንቧ ሠራተኛ ነኝ፤ አንዳንድ ጊዜ ደንበኞቼ በአስቸኳይ እንድደርስላቸው ይፈልጋሉ። እነሱ በፈለጉበት ጊዜ ልሠራላቸው እንደማልችል ከተሰማኝ ሌላ ሰው እጠቁማቸዋለሁ።”—ክሪስቶፈር

     ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬ ችላ እንደተባለ ወይም እንደተባለች ከተሰማት ወይም ከተሰማው የተሰጠኝን ተጨማሪ ሥራ ለመተው ፈቃደኛ ነኝ? የትዳር ጓደኛዬስ እንዲህ ይሰማዋል ወይም ይሰማታል?

  •   አብራችሁ የምትሆኑበት ጊዜ መድቡ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1) ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ የምትሆኑበት ጊዜ መመደብ ወይም ማመቻቸት የሚያስፈልጋችሁ በተለይ የሥራ ጫና በሚበዛባችሁ ወቅት ነው።

     “በአብዛኛው የሥራ ጫና በጣም ሲበዛብን ተነጋግረን የሆነ ሰዓት እንመድባለን፤ የተለየ ነገር ለማድረግ ሳይሆን ራት ለመብላት ወይም ባሕር ዳርቻ ለመንሸራሸር ሊሆን ይችላል፤ ብቻ የመደብነውን ሰዓት ምንም ነገር ሳይረብሸን አብረን ጊዜ ማሳለፍ እንፈልጋለን።”—ዴቦራ

     ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ለትዳር ጓደኛዬ ያልተከፋፈለ ትኩረት የምሰጥበት ጊዜ እመድባለሁ? የትዳር ጓደኛዬስ እንዲህ ይሰማዋል ወይም ይሰማታል?’

  •   የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችሁን አጥፉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚደወሉላችሁ ስልኮች ወይም የሚላኩላችሁ መልእክቶች ትኩረታችሁን እንዳይከፋፍሉት አልፎ አልፎ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችሁን ማጥፋት ትችሉ ይሆን?

     “በተወሰነ ሰዓት ላይ ሥራዬን ለማቆም ጥረት እያደረግኩ ነው። ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ምንም ዓይነት መልእክት እንዳይደርሰኝ ስልኬን አጠፋለሁ።”—ጄረሚ

     ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘አለቃዬ ወይም ደንበኞቼ ሊፈልጉኝ ይችላሉ ብዬ በማሰብ ስልኬን ሁሌም ክፍት ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል? የትዳር ጓደኛዬስ እንዲህ ይሰማዋል ወይም ይሰማታል?’

  •    ምክንያታዊ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። (ፊልጵስዩስ 4:5) አንዳንድ ጊዜ አብራችሁ ለማሳለፍ ባሰባችሁበት ሰዓት ላይ የሥራ ጉዳይ ጣልቃ ሊገባባችሁ እንደሚችል አይካድም። ለምሳሌ ያህል፣ የትዳር ጓደኛችሁ የሥራ ጸባይ ከሥራ ሰዓት ውጪ እንዲጠራ ወይም እንድትጠራ የሚያስገድድ ሊሆን ይችላል። ከትዳር ጓደኛችሁ በምትጠብቁት ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁኑ።

     “ባለቤቴ አነስተኛ የሆነ ንግድ አለው፤ አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ሰዓት ውጪ አስቸኳይ ጉዳይ አጋጥሞት ሥራ ለመግባት ይገደዳል። ይህ የሚያበሳጨኝ ጊዜ አለ፤ ግን አብረን ጊዜ የምናሳልፍበት ብዙ አጋጣሚ ስላለን በዚያ እንደሚካካስ ይሰማኛል።”—ቤቨርሊ

     ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬን የሥራ ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት ከእሱ ወይም ከእሷ በምጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ለመሆን እሞክራለሁ? የትዳር ጓደኛዬስ እንዲህ ይሰማዋል ወይም ይሰማታል?’

 ውይይት ለማድረግ የሚረዱ ጥያቄዎች

 መጀመሪያ፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በየግላችሁ ለመመለስ ሞክሩ፤ ከዚያም በሰጣችሁት መልስ ላይ አብራችሁ ተወያዩ።

  •   የትዳር ጓደኛችሁ ሥራችሁን ወደ ቤት ይዛችሁ በመምጣታችሁ ቅር እንደተሰኘ ተናግሮ ያውቃል? ከሆነ እናንተስ በዚህ ሐሳብ ትስማማላችሁ?

  •   ሥራችሁንና ሌሎች እንቅስቃሴዎቻችሁን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማስኬድ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባችሁ የሚሰማችሁ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ነው?

  •   የትዳር ጓደኛችሁ ሥራውን “በሥራው ቦታው” ትቶ ለመምጣት እንደሚቸገር ተሰምቷችሁ ያውቃል? ከሆነ የትኞቹን አጋጣሚዎች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ትችላላችሁ?

  •   የትዳር ጓደኛችሁ ሥራውንና ሌሎች እንቅስቃሴዎቹን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማስኬድ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ይሰማችኋል? ከሆነ በየትኞቹ አቅጣጫዎች?