በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆች እና ዘመናዊ ስልኮች—ክፍል 2፦ ልጆች ዘመናዊ ስልክን በጥበብ እንዲጠቀሙ ማስተማር

ልጆች እና ዘመናዊ ስልኮች—ክፍል 2፦ ልጆች ዘመናዊ ስልክን በጥበብ እንዲጠቀሙ ማስተማር

ዘመናዊ ስልክ እንደ ቢላ ነው፤ እንደ አጠቃቀማችን ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን ይችላል። ልጆቻችሁ በዚህ አደገኛ መሣሪያ ሲጠቀሙ አስተዋይ እንዲሆኑ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ለምሳሌ ልጃችሁ ስልኩ ላይ ምን ያህል ሰዓት እንዲያሳልፍ ልትፈቅዱለት ይገባል? a

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

  • ዘመናዊ ስልኮች ለአደጋ ያጋልጣሉ። “ልጆች እና ዘመናዊ ስልኮች—ክፍል 1፦ ልጄ ዘመናዊ ስልክ ሊኖረው ይገባል?” በሚለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ጥሩም ይሁኑ መጥፎ ኢንተርኔት ላይ ያሉ ነገሮችን በሙሉ በዘመናዊ ስልክ አማካኝነት ማግኘት ይቻላል።

    “ዘመናዊ ስልክ ልጆቻችንን ለብዙ ዓይነት አደገኛ ሰዎችና ሐሳቦች ሊያጋልጣቸው እንደሚችል በቀላሉ ልንዘነጋ እንችላለን።”—ብሬንዳ

  • ልጆች ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ወጣቶች ከትንሽነታቸው አንስቶ ለቴክኖሎጂ የተጋለጡ ናቸው፤ አብዛኞቹ አዋቂዎች ግን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የጀመሩት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርቡ ነው። ይህ ሲባል ግን ወላጆች ስለ ቴክኖሎጂ ምንም አያውቁም ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ልጆች ስልካቸውን መቼና እንዴት እንደሚጠቀሙበት ለመወሰን ከወላጆቻቸው የተሻለ ብቃት አላቸው ማለት አይደለም።

    እርግጥ ልጆቻችሁ በስልክ አጠቃቀም ረገድ ከእናንተ ይበልጥ ቀልጣፋ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም ቅልጥፍናና ብስለት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርባችኋል። ስለ ቴክኖሎጂ ብዙ የሚያውቁ ልጆችም እንኳ ዘመናዊ ስልካቸውን በጥበብ ለመጠቀም የወላጆቻቸው ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል።

    “ለልጃችሁ ሥልጠና ሳትሰጡ ዘመናዊ ስልክ ብትሰጡት የመንጃ ፈቃድ ሥልጠና ሳያገኝ የመኪና ቁልፍ ሰጥታችሁ፣ የሹፌር ወንበር ላይ አስቀምጣችሁት፣ ሞተር አስነስታችሁ ‘ተጠንቅቀህ ንዳ’ ከማለት አይተናነስም።”—ሴት

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • የልጃችሁ ስልክ ያሉትን ገጽታዎች እወቁ። አንዳንድ ስልኮች ልጃችሁ ስልኩን በጥበብ እንዲጠቀም ሊረዱት የሚችሉ ገጽታዎች አሏቸው፤ ከእነዚህ ገጽታዎች ጋር በሚገባ ተዋወቁ። ለምሳሌ፦

    ስልኩ ልጁ ረጅም ሰዓት እንዳይጠቀምበት የሚገድብ ለወላጆች የተዘጋጀ መቆጣጠሪያ አለው?

    ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን የሚያግደው መቆጣጠሪያ የታሰበውን አገልግሎት የማይሰጥበት ጊዜ እንዳለ ታውቃላችሁ?

    ስለ ልጃችሁ ስልክ በደንብ ማወቃችሁ ልጃችሁ ስልኩን በጥበብ እንዲጠቀም ለመርዳት ያስችላችኋል።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰውም በእውቀት ኃይሉን ይጨምራል።”—ምሳሌ 24:5

  • ገደብ አብጁ። ለልጃችሁ ምን እንደምትፈቅዱለትና ምን እንደምትከለክሉት ወስኑ። ለምሳሌ፦

    ልጃችሁ በምግብ ሰዓት ስልኩን ይዞ እንዲቀመጥ ትፈቅዱለታላችሁ? አሊያም ደግሞ ከዘመዶቻችሁ ወይም ከወዳጆቻችሁ ጋር ስትሆኑ ስልኩን እንዲጠቀም ትፈቅዱለታላችሁ?

    ልጃችሁ ሌሊቱን ስልኩን ይዞ እንዲያድር ትፈቅዱለታላችሁ?

    የምትፈቅዱለት የትኞቹን አፕሊኬሽኖች እንዲጠቀም ነው?

    ልጃችሁ ስልኩ ላይ ምን ያህል ሰዓት እንዲያሳልፍ ልትፈቅዱለት ይገባል?

    ልጃችሁ በቀን ውስጥ ምን ያህል ሰዓት ስልኩን መጠቀም እንደሚችል ገደብ ታበጁለታላችሁ?

    ያወጣችሁትን ገደብ ለልጃችሁ በግልጽ ንገሩት፤ እንዲሁም ገደቡን ከጣሰ ተገቢውን ቅጣት ከመስጠት ወደኋላ አትበሉ።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጅን ከመገሠጽ ወደኋላ አትበል።”—ምሳሌ 23:13

  • ተቆጣጠሩት። የልጃችሁን የይለፍ ቃል እወቁ፤ እንዲሁም የጽሑፍ መልእክቶቹን፣ አፕሊኬሽኖቹን፣ ፎቶዎቹንና የሚጎበኛቸውን ድረ ገጾች ጨምሮ በስልኩ ውስጥ ያሉትን ነገሮች እንደ አስፈላጊነቱ ገምግሙ።

    “ለልጃችን አልፎ አልፎ ስልኳን በድንገት ልንመረምረው እንደምንችል ነግረናታል። ስልኳን አላግባብ ከተጠቀመችበት በስልክ አጠቃቀሟ ረገድ ገደብ ሊጣልባት ይችላል።”—ሎሬን

    ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጃችሁ ስልኩን እንዴት እየተጠቀመበት እንዳለ የማወቅ ሙሉ መብት አላችሁ።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ በአድራጎቱ ይታወቃል።”—ምሳሌ 20:11

  • መልካም እሴት ቅረጹበት። ልጃችሁ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንዲፈልግ እርዱት። እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ልጃችሁ ከልቡ ከቆረጠ እሱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ብታደርጉም ሊያታልላችሁ ይችላል። b

    በመሆኑም ልጃችሁ እንደ ሐቀኝነት፣ ራስን መግዛት እና ለድርጊቱ ኃላፊነት መውሰድ ያሉ መልካም ባሕርያትን እንዲያዳብር እርዱት። መልካም እሴቶችን ያዳበረ ልጅ ስልኩን በጥበብ መጠቀሙ አይቀርም።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ጎልማሳ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን አሠልጥነዋል።’—ዕብራውያን 5:14

a በዚህ ርዕስ ውስጥ “ዘመናዊ ስልክ” የሚለው አገላለጽ የተሠራበት ኢንተርኔት መጠቀም የሚያስችሉ ስልኮችን ለማመልከት ነው። ትንሽዬ ኮምፒውተር ናቸው ሊባል ይችላል።

b ለምሳሌ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው እንዲያዩት የማይፈልጉትን ነገር ለመደበቅ የተለያዩ አፕሊኬሽኖችን ይጠቀማሉ፤ እነዚህ አፕሊኬሽኖች ከላይ ሲታዩ ካልኩሌተር ወይም ምንም ጉዳት የሌለው አፕሊኬሽን ይመስላሉ።