በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆች በሚሰሟቸው የዜና ዘገባዎች እንዳይረበሹ መርዳት

ልጆች በሚሰሟቸው የዜና ዘገባዎች እንዳይረበሹ መርዳት

 አሰቃቂ የዜና ዘገባዎች በቴሌቪዥን፣ በስልክ፣ በታብሌትና በኮምፒውተር አማካኝነት በማንኛውም ሰዓት ይተላለፋሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ዘገባዎች ሁኔታውን ግልጽልጽ አድርገው በሚያሳዩ ቪዲዮዎች የተደገፉ ናቸው።

 ልጆች ደግሞ እነዚህን ዘገባዎች ይመለከታሉ።

 ልጆቻችሁ በሚሰሟቸው የዜና ዘገባዎች የተነሳ ለጭንቀት እንዳይዳረጉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

 የዜና ዘገባዎች በልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

  •   ብዙ ልጆች በዜና ዘገባዎች ላይ በሚያዩት አሳዛኝ ነገር ይጨነቃሉ። አንዳንድ ልጆች ስሜታቸውን በግልጽ አይናገሩ ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያሉ የዜና ዘገባዎች በእጅጉ ሊረብሿቸው ይችላሉ። a ወላጆች ከልክ በላይ የሚጨነቁ ከሆነ ደግሞ የልጆቹ ጭንቀት ሊባባስ ይችላል።

  •   ልጆች ዜና ላይ የሚያዩትን ነገር በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ልጆች ዜና ላይ ያዩት ነገር በቤተሰባቸው ላይ እንደሚደርስ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም አንድን የሚረብሽ የዜና ዘገባ ደጋግመው የሚመለከቱ ትናንሽ ልጆች ሁኔታው በተደጋጋሚ እየተከሰተ እንዳለ ሊያስቡ ይችላሉ።

  •   ልጆች ዘገባውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት ሊቸገሩ ይችላሉ። የዜና አቅራቢ ድርጅቶች ትርፋማ መሆን የሚችሉት ብዙ ተመልካቾች ሲኖሯቸው ነው። በመሆኑም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ የዜና ዘገባዎችን በመጠኑም ቢሆን አጋነው ሊያቀርቡ ይችላሉ። ልጆች ደግሞ ይህን አያውቁም።

 ልጃችሁ በሚሰማቸው የዜና ዘገባዎች የተነሳ በጭንቀት እንዳይዋጥ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

  •   በሚያየው የዜና ዘገባ ላይ ገደብ አድርጉ። ይህ ሲባል ልጃችሁ በዙሪያው ስለሚከናወነው ነገር ሊያውቅ አይገባም ማለት አይደለም። ሆኖም የሚረብሹ ዜናዎችን ደግሞ ደጋግሞ መስማቱ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድርበታል።

     “አንዳንዴ ልጆቻችን ሲሰሙ ምን ያህል ሊደነግጡ እንደሚችሉ ሳናስብ ስለ አንድ የዜና ዘገባ በዝርዝር እናወራለን።”—ማሪያ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል።”—ምሳሌ 12:25

  •   በትዕግሥት አዳምጡ እንዲሁም ስሜቱን እንደተረዳችሁ በሚያሳይ መንገድ መልስ ስጡ። ልጃችሁ ስሜቱን አውጥቶ መናገር ከከበደው ሐሳቡን በሥዕል መግለጽ እንደሚችል ንገሩት። ልጃችሁን ባሳሰበው ነገር ላይ ስትወያዩ ሊገባው በሚችል መንገድ ተናገሩ፤ ሆኖም ዘገባውን በተመለከተ አላስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጠቡ።

     “ልጃችንን ቁጭ ብለን ስናዳምጣት ጭንቀቷ ቀለል ይልላታል። ‘አሁን ያለው ሁኔታ ይህ ነው። ስለዚህ ተቀብለነው ልንኖር ይገባል’ እንደሚሉት ያሉ ንግግሮች ግን ለእሷ ምንም አይጠቅሟትም።”—ሰራሂ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።”—ያዕቆብ 1:19

  •   ልጃችሁ ለዜና ዘገባዎች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው እርዱት። ለምሳሌ ልጆች፣ አፍኖ ስለመውሰድ የሚገልጽ የዜና ዘገባ ሲያዩ እንዲህ ያለው ወንጀል ከእውነታው በላይ በብዛት የሚፈጸም ሊመስላቸው ይችላል። ስለዚህ እነሱን ከአደጋ ለመጠበቅ ስለወሰዳችኋቸው እርምጃዎች ለልጆቻችሁ ንገሯቸው። በተጨማሪም አንድ ነገር ልታስታውሱ ይገባል፦ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ክስተት ዜና ተብሎ የሚቀርበው በተደጋጋሚ ሳይሆን አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ስለሆነ ነው።

     “ልጆቻችሁ አሉታዊ ስሜቶችን ማሸነፍ እንዲችሉ እርዷቸው። የሚሰማን ስሜት በአብዛኛው ከምናስበው ነገር ጋር የተያያዘ ነው፤ ልጆቻችን አዎንታዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ የምንረዳቸው ከሆነ ሊረጋጉ ይችላሉ።”—ሎርደስ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የጥበበኛ ሰው ልብ፣ አንደበቱ ጥልቅ ማስተዋል እንዲኖረው ያደርጋል፤ ለንግግሩም የማሳመን ችሎታ ይጨምርለታል።”—ምሳሌ 16:23

a ትናንሽ ልጆች በሚጨነቁበት ጊዜ አልጋቸው ላይ ሊሸኑ፣ ትምህርት ቤት ለመሄድ ሊፈሩና ከወላጆቻቸው ለመለየት ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ።