በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

Albert Wright/iStock via Getty Images

ንድፍ አውጪ አለው?

ማሊ የተባሉት ወፎች ጎጆ

ማሊ የተባሉት ወፎች ጎጆ

 በደቡባዊ አውስትራሊያ የሚገኙት ማሊ የተባሉት ወፎች ጎጆ የሙቀት መጠን፣ በአማካይ 34 ዲግሪ ሴልሸስ ነው፤ እነዚህ ወፎች የጎጇቸው የሙቀት መጠን ከአማካይ የሙቀት መጠኑ ከሁለት ወይም ከሦስት ዲግሪ ሴልሸስ በላይ እንዳይጨምር ወይም እንዳይቀንስ የማድረግ ችሎታ አላቸው። ለመሆኑ ዓመቱን ሙሉ ቀንም ሆነ ሌሊት ይህን የሙቀት መጠን አመጣጥነው ማቆየት የሚችሉት እንዴት ነው?

 በየክረምቱ ወንዱና ሴቷ ወፍ የአንድ ሜትር ጥልቀትና የሦስት ሜትር ስፋት ያለው ጉድጓድ ይቆፍራሉ፤ ከዚያም ወንዱ ወፍ ጉድጓዱን በሣር፣ በቅጠልና በሌሎች ተክሎች ይሞላዋል። የተቆለለው አትክልት ምሽት ላይ በሚጥለው የክረምት ዝናብ ከረሰረሰ በኋላ ወፉ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ ለእንቁላል መጣያ የሚሆን ሌላ ክፍል ያዘጋጃል፤ ከዚያም የተቆለለውን አትክልት በአሸዋማ አፈር ይሸፍነዋል። ብዙም ሳይቆይ፣ የተቆለለው አትክልት መበስበስና ሙቀት መፍጠር ይጀምራል፤ በመሆኑም ቦታው ልክ እንደ እንቁላል መፈልፈያ ሆኖ ያገለግላል።

ማሊ የተባሉት ወፎች እንቁላላቸውን ለመፈልፈል (ሀ) ከፀሐይ ብርሃን እንዲሁም ከአትክልት ብስባሽ የሚገኘውን ሙቀት ይጠቀማሉ (ለ)። ጎጆውን የሚሸፍነውን አፈር መጠን በማስተካከል (ሐ) እንቁላሎቹ የሚጣሉበት ጎጆ የሙቀት መጠን ከ34 ዲግሪ ሴልሸስ ብዙም ሳይበልጥ ወይም ሳያንስ ለበርካታ ወራት እንዲቆይ ማድረግ ይችላሉ። ለዚህም ሲባል ወንዱ ወፍ ከፍተኛ መጠን ያለው አፈር እየጫረ ያስወግዳል እንዲሁም ይመልሳል (መ)

 ሴቷ ወፍ እንቁላል ለመጣል ዝግጁ ስትሆን ወንዱ ወፍ አፈሩን በማውጣት እንቁላሉን በእንቁላል መጣያው ክፍል ውስጥ መጣል እንድትችል ቦታውን ያዘጋጅላታል። ከዚያም ወዲያውኑ ቁልሉን መልሶ በአፈር ይሸፍነዋል። ከመስከረም እስከ የካቲት ባለው ጊዜ ውስጥ ወፏ እስከ 35 እንቁላል ድረስ ልትጥል ትችላለች። a

 ወፎቹ መንቆራቸውን በተደጋጋሚ አፈሩ ውስጥ በማስገባት የሙቀት መጠኑን ይከታተላሉ። ከዚያም የወቅቱን የአየር ጠባይ ግምት ውስጥ በማስገባት ቁልሉን ያስተካክላሉ። ለምሳሌ ያህል፦

  •   እየበሰበሰ ባለው አትክልት ምክንያት የጎጆው የሙቀት መጠን በጣም በሚጨምርበት የጸደይ ወራት ወንዱ ወፍ ከእንቁላል ክፍሉ በላይ ያለውን አፈር እየጫረ በማስወገድ ሙቀቱን ያስተነፍሳል። ከዚያም ጎጆውን ቀዝቀዝ ባለ አፈር መልሶ ይሸፍነዋል።

  •   በበጋ ወራት ወንዱ ወፍ በአትክልት ቁልሉ ላይ ተጨማሪ አፈር በማድረግ እንቁላሎቹን ከፀሐይ ይከልላል። ሆኖም በየማለዳው አፈሩን እየጫረ በማስወገድ ጎጆውንና አሸዋውን ካቀዘቀዘ በኋላ መልሶ ሌላ አፈር ያደርጋል።

  •   የአትክልት ቁልሉ በስብሶ በሚጨርስበት የመከር ወራት ወንዱ ወፍ የቀትሩ ፀሐይ እንቁላሎቹን እንዲያገኛቸውና የተበተነውን አፈር እንዲያሞቀው ሲል አፈሩን በሙሉ ያስወግዳል። በኋላም የአትክልት ቁልሉን በሞቀው አፈር መልሶ በመሸፈን በምሽቱ ክፍለ ጊዜ ጎጆው ሙቀት እንዲያገኝ ያደርጋል።

 ወንዱ ወፍ በየቀኑ 850 ኪሎ ግራም ገደማ የሚሆን አፈር በማንሳትና በመመለስ በአማካይ ከአምስት ሰዓት በላይ በሥራ ያሳልፋል። አፈሩ በተደጋጋሚ መንቀሳቀሱ ሌላም የሚያስገኘው ጥቅም አለ፦ አፈሩ እንዳይጠቀጠቅ ስለሚያደርግ እንቁላሎቹ ሲፈለፈሉ ጫጩቶቹ በቀላሉ ወደ ውጭ መውጣት ይችላሉ።

 ማሊ የተባሉት ወፎች ከጎጇቸው አፈሩን እየጫሩ ሲያስወግዱ የሚያሳይ ቪዲዮ ተመልከት

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? ማሊ የተባሉት ወፎች ያላቸው የጎጇቸውን የሙቀት መጠን የመቆጣጠር ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የመጣ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

a እንቁላሎቹ የሚፈለፈሉት ከሰባት እስከ ስምንት ሳምንት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ነው፤ በመሆኑም የአትክልት ቁልሉን የመከታተሉ ሥራ እስከ ሚያዝያ ድረስ ሊዘልቅ ይችላል።