በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 2024 መጠበቂያ ግንብ በሴብዋኖ (በስተ ግራ) እና በፓንጋሲናን (በስተ ቀኝ) ቋንቋዎች መታተም ከጀመረ 75 ዓመት ሞላው

ሚያዝያ 3, 2024
ፊሊፒንስ

መጠበቂያ ግንብ በሴብዋኖ እና በፓንጋሲናን ቋንቋዎች 75 ዓመት ሞላው

መጠበቂያ ግንብ በሴብዋኖ እና በፓንጋሲናን ቋንቋዎች 75 ዓመት ሞላው

ሚያዝያ 2024 በፊሊፒንስ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሕትመት ሥራችን ምዕራፍ ከፋች የሆነ አንድ ክንውን 75ኛ ዓመት ነው። መጠበቂያ ግንብ በአገሪቱ በሚነገሩት የሴብዋኖ እና የፓንጋሲናን ቋንቋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ የወጣው ሚያዝያ 1949 ነበር።

የመንግሥቱ ምሥራች ፊሊፒንስ የደረሰው በ1900ዎቹ መጀመሪያ ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጀመሪያ አካባቢ የእንግሊዝኛ ጽሑፎችን አገልግሎት ላይ ይጠቀሙ ነበር፤ ሆኖም በጊዜ ሂደት በአገሬው ቋንቋዎች ጽሑፎች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ሆነ። በ1947 በአገሪቱ በሰፊው በሚነገረው የታጋሎግ ቋንቋ መጠበቂያ ግንብን ለመተርጎም ሥራ ተጀመረ። በ1948 መገባደጃ ላይ ደግሞ በሴብዋኖ እና በፓንጋሲናን ቋንቋዎች መጠበቂያ ግንብን ለመተርጎም ዝግጅት ተደረገ። ከጥቂት ወራት በኋላ የመጀመሪያዎቹ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ታተሙ።

በእጅ በሚሠራ ማሽን የተባዛ አንድ የፓንጋሲናን መጠበቂያ ግንብ ቅጂ፣ 1949

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሕትመቱ የሚካሄደው እዚያው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በእጅ በሚሠራ የማባዣ ማሽን ነበር። የመጽሔቶቹ ተፈላጊነት እየጨመረ ሲሄድ ግን የሴብዋኖ እና የፓንጋሲናን ቋንቋዎች የሕትመት ሥራ በወቅቱ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተዛወረ። a

ወንድም ሁዋን ላንዲቾ

በሴብዋኖ እና በፓንጋሲናን ቋንቋዎች በሚካሄደው የመጠበቂያ ግንብ የትርጉም ሥራ ይካፈሉ የነበሩ በርካቶች፣ ስላገኙት መብት አስደሳች ትዝታ አላቸው። በ1980ዎቹ ዓመታት በፓንጋሲናን የትርጉም ቡድን ውስጥ ያገለግል የነበረው ወንድም ሁዋን ላንዲቾ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “በትርጉም ሥራ ላይ በሚፈጠር መዘግየት የተነሳ መጀመሪያ አካባቢ የፓንጋሲናን የመጠበቂያ ግንብ እትም እጃችን የሚደርሰው የእንግሊዝኛው ከወጣ ከስድስት ወር በኋላ ነበር። በትርጉም ሥራችን ላይ ማሻሻያ ተደርጎ በ1986 የፓንጋሲናን መጠበቂያ ግንብ ከእንግሊዝኛ እኩል ሲወጣ በጣም ነው የተደሰትነው። የይሖዋ መንፈስ በሥራችን እንደሚመራን ያለን እምነት ተጠናከረ።”

እህት ቤለን ካኜቴ በፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለ46 ዓመታት በሴብዋኖ የትርጉም ሥራ ስታገለግል ቆይታለች፤ እሷም እንዲህ ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፦ “መጀመሪያ አካባቢ ተርጓሚዎቹ ጥቂት፣ ሥራው ግን ብዙ ነበር። አንዳንዴ በጣም ይከብደን ነበር። አሁን ግን ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ እየታገዘ የሚሠራ በሚገባ የሠለጠነ የትርጉም ቡድን አለን። ይሖዋ ከመዳብ ወደ ወርቅ ሲያሻግረን አይቻለሁ፤ በእርግጥም እሱ ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልገውን ማቅረብ ያውቅበታል።”

የፓንጋሲናን (በስተ ግራ) እና የሴብዋኖ (በስተ ቀኝ) የትርጉም ቡድን አባላት

ፊሊፒንስ ውስጥ ከ26 ሚሊዮን የሚበልጡ ሴብዋኖ ተናጋሪዎች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል በሴብዋኖ ቋንቋ በሚመሩ 1,150 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ከ76,000 በላይ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይገኙበታል። በተጨማሪም የፓንጋሲናን ተናጋሪ ከሆኑት 2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች መካከል 6,000 ገደማ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚገኙበት ሲሆን በ68 የፓንጋሲናን ቋንቋ ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ። በፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር በድምሩ በ24 ቋንቋዎች የትርጉም ሥራ ይካሄዳል። ከእነዚህ ውስጥ በአሥሩ በየወሩ መጠበቂያ ግንብ ይወጣል። በአሁኑ ወቅት የሴብዋኖ እና የፓንጋሲናን ጽሑፎችን የሚያትመው የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ነው።

ይሖዋ የትርጉም ሥራውን ስለባረከውና ቃሉ እውነትን ለተጠሙ የሴብዋኖ እና የፓንጋሲናን ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲደርስ በማድረጉ እናመሰግነዋለን።​—ኢሳይያስ 55:1

a በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው ዋርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው።