በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኒውበርግ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ የተካሄደው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የ2023 የክልል ስብሰባ

ግንቦት 15, 2023
ዩናይትድ ስቴትስ

“በትዕግሥት ጠብቁ”! የ2023 የክልል ስብሰባዎች ጀመሩ

“በትዕግሥት ጠብቁ”! የ2023 የክልል ስብሰባዎች ጀመሩ

በአካል የሚደረጉ የክልል ስብሰባዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከመጋቢት 2020 ጀምሮ ተቋርጠው ቆይተዋል። በዚህ ዓመት “በትዕግሥት ጠብቁ”! በሚል ርዕስ በዓለም ዙሪያ ከ6,000 በላይ የክልል ስብሰባዎች ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይካሄዳሉ። ተሰብሳቢዎች በአካል ከሚገኙባቸው ከእነዚህ የክልል ስብሰባዎች የመጀመሪያው ከግንቦት 12 እስከ 14, 2023 ተካሂዷል።

እህት ክርስቲን ቶረስ በኒውበርግ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኒውበርግ የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ከተገኙት 1,800 ታዳሚዎች አንዷ ናት። እንዲህ ብላለች፦ “ሊቀ መንበሩ ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ ሲል በመላው አዳራሽ ጭብጨባው አስተጋባ። ሁላችንም አንድ ላይ መሰብሰብ በመቻላችን በጣም ተደስተን ነበር።” ወንድም ዱዌን ስሚዝም በስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል ሲሆን “በተሰብሳቢዎቹ ላይ የሚነበበው የደስታ ስሜት አስደናቂ ነበር። በአካል አብረው በመሰብሰባቸው ልባቸው በሐሴት እንደተሞላ ማየት ይቻላል” ብሏል።

እህት ጄሲካ ዶልቼማስኮሎ የተጠመቀችው በኮቪድ ወቅት ነበር፤ ስለዚህ በአካል በሚደረግ የክልል ስብሰባ ላይ ተገኝታ አታውቅም። በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘት ምን ስሜት እንደፈጠረባት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እዚህ የምታዩት ደስታና ፍቅር፣ ለረጅም ጊዜ ከተለያችሁት የልብ ጓደኛችሁ ጋር በድጋሚ ስትገናኙ የሚሰማችሁ ዓይነት ነው።” በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተጠመቀችው የ18 ዓመቷ ኖኤሚ ቲናጄሮ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ስብሰባው ላይ ደስተኛ ቤተሰቦችና ደስተኛ ወዳጆች ታያላችሁ። . . . አዲሱ ዓለም የገባሁ ያህል ነው የተሰማኝ።”

እህቶች በኒውበርግ ወደተካሄደው የክልል ስብሰባ ሲገቡ፣ ዓርብ ጠዋት

ብዙዎች ለስብስባው የተመረጠውን ጭብጥ በጣም እንደወደዱት ተናግረዋል። ወንድም ሳም ሁህ እንዲህ ብሏል፦ “ታጋሽ መሆን ለብዙዎቻችን ከባድ ነገር ነው። የይሖዋን የትዕግሥት ምሳሌ እንድንኮርጅ ማሳሰቢያ የተሰጠን በሚያስፈልገን ጊዜ ነው።” እህት ፍሬንቺ ስሚዝም እንዲህ ብላለች፦ “ይህ የክልል ስብሰባ በሁሉም የሕይወቴ ክፍል ትዕግሥት ማሳየቴ አስፈላጊ መሆኑን አስተምሮኛል። በስብሰባው ላይ የተላለፈው ትምህርት ሁሉ በጣም ጠቃሚ ነው።”

በኒውበርግ፣ ኒው ዮርክ በተካሄደው የመጀመሪያ የክልል ስብሰባ ላይ የመገኘት መብት ያገኙት ሁሉ በስብሰባው በእጅጉ ተበረታተዋል! በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በቀጣዮቹ ወራት የሚቀርበውን ይህን መንፈሳዊ ድግስ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው።—መዝሙር 122:1