በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የጉባኤ ስብሰባ ሲያደርጉ። በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ብዙዎች የጌታ ራትን የሚያከብሩት በዚህ መንገድ ይሆናል

ሚያዝያ 3, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ታሪካዊ በሆነ መንገድ ማክበር

በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ የተነሳ በርካታ ጉባኤዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ይሰበሰባሉ

የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ታሪካዊ በሆነ መንገድ ማክበር

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች ሰዎች ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7, 2020 በዓመቱ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጠውን ክንውን ማለትም የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ይሰበሰባሉ። ሆኖም በዚህ ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አከባበሩ ለየት ያለ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች የሚሰበሰቡት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ነው።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ በበርካታ አገሮች ያሉ ባለሥልጣናት ብዙ ሰው አንድ ላይ እንዳይሰበሰብ አግደዋል። በዚህም የተነሳ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ጉባኤዎች ሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸውን ለማድረግ የቪዲዮ ኮንፈረንስ እየተጠቀሙ ነው። እነዚህ ጉባኤዎች የመታሰቢያውን በዓል የሚያከብሩትም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ይሆናል። በተጨማሪም jw.org ላይ የወጣውን አስቀድሞ የተቀዳ ንግግር ማንኛውም ሰው ማግኘት ይችላል።

ባለፈው ዓመት ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። ዘንድሮም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በስልክ አማካኝነት ፕሮግራሙን በቀጥታ እንደሚከታተሉ አሊያም jw.org ላይ የወጣውን ቪዲዮ እንደሚመለከቱ ተስፋ እናደርጋለን።

በብዙ አገሮች ውስጥ ቫይረሱ አሁንም እየተስፋፋ ነው። የወንድሞቻችንን ደህንነት አደጋ ላይ ላለመጣል ሲባል ሁላችንም ይህ ወረርሽኝ እስኪያልፍ ድረስ ንቁ መሆንና የሚሰጠንን መመሪያ መከተል ይኖርብናል። ያም ቢሆን ይሖዋ እንደሚደግፈን በመተማመን ኢየሱስ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት የሰጠውን መመሪያ እንታዘዛለን።—ሉቃስ 22:19