በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 23, 2020
ኢኳዶር

በኢኳዶር የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤታቸው ሳይወጡ እየሰበኩ ነው

በኢኳዶር የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤታቸው ሳይወጡ እየሰበኩ ነው

በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ አገልግሎታቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ ማስተካከያ እያደረጉ ነው። በኢኳዶር የሚኖሩ አስፋፊዎች ለሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ ሲሉ የተለያዩ የስብከት ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው።

በአምባቶ ከተማ የምትኖር አንዲት የሰባት ዓመት አስፋፊ ከእናቷ ጋር ሆና ለአስተማሪዎቿ የጽሑፍ መልእክት ላከች። መልእክቱ እንዲህ ይላል፦ “እንደምን አደሩ መምህር። የምንኖርበት ዘመን አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት የሚያጽናና መልእክት ልልክልዎት እፈልጋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 21:4 ላይ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። ተጨማሪ መረጃ የሚገኝበት ሊንክ ልኬልዎታለሁ።”

አንዲት አስተማሪ እንዲህ በማለት መልሳላታለች፦ “አመሰግናለሁ የእኔ ቆንጆ። ዕድሜሽ ትንሽ ቢሆንም ንግግርሽ እንደ አዋቂ ነው።” አንዲት ሌላ አስተማሪ ደግሞ ለመልእክቱ ካመሰገነች በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ በዲጂታል ፎርማት ማግኘት ትችል እንደሆነ ጠየቀች። አስተማሪዋ ቀደም ሲል ይህ መጽሐፍ የነበራት ቢሆንም መጽሐፉን ለሌላ ተማሪ እንዳዋሰችው ተናገረች። ልጅቷም መጽሐፉን ከ​jw.org ላይ ማውረድ እንደምትችል ለአስተማሪዋ ነገረቻት።

በኬቬዶ የሚኖሩ ባልና ሚስት ስልካቸው ውስጥ ያሉትን ቁጥሮች በማየት የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ከለዩ በኋላ እንደሚከተለው በማለት የጽሑፍ መልእክት ላኩላቸው፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ነን። በዚህ አገርም ሆነ በመላው ዓለም ባለው ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት ወደ ቤት መስበክ አንችልም፤ ሆኖም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ብናነጋግርዎት ደስ ይለናል።”

አብዛኞቹ ሰዎች በዚህ መልኩ ለመነጋገር ፈቃደኛ ሆነዋል። ለምሳሌ እነዚህ ባልና ሚስት ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች ሲመሠክሩላት ለማነጋገር ፈቃደኛ ያልነበረችን አንዲት ሴት አነጋግረው ነበር፤ ይህች ሴት ባልና ሚስቱ ሰዎችን ለማጽናናት ጥረት በማድረጋቸው አመሰገነቻቸው። ሴትየዋ በዓለም ላይ ባለው ሁኔታ የተነሳ ውጥረት እንደተሰማት ነገረቻቸው። ባልና ሚስቱም “ከውጥረት እፎይታ ማግኘት” የሚል ርዕስ ያለውን ንቁ! ቁጥር 1 2020 በፒዲኤፍ ፎርማት ላኩላት። በቀጣዩ ውይይታቸው ወቅት ሴትየዋ መጽሔቱን እንደወደደችውና በተደጋጋሚ እንዳነበበችው ተናግራለች።

በሳንቶ ዶሚኒጎ ዴ ሎስ ሳቺላስ የምትኖር ጆሃና የተባለች መስማት የተሳናት እህት ሥዕሎችን በመጠቀም ደብዳቤ “ጻፈች።” a ከዚያም ሥዕሉን ፎቶ አንስታ ለምታውቃቸው መስማት የተሳናቸው ሰዎች ላከችላቸው። ሆኖም መልእክቱ ከደረሳቸው ሰዎች መካከል አንዷ መስማት የምትችል ሴት ነበረች። ሴትየዋ ወዲያውኑ ጥያቄዎች ላከች። ጆሃና ጥያቄዎቹን መረዳት ሳላልቻለች ሮንዳ የተባለች መስማት የምትችል አቅኚ እህት ሴትየዋን አነጋገረቻት።

ሴትየዋ ጆሃና የላከችላት ሥዕል ትኩረቷን እንደሳበው ለሮንዳ ነገረቻት። ከዚያም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ስላለው ሁኔታ የሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይኖሩ እንደሆነ ጠየቀች። ሮንዳም ሉቃስ 21:10, 11ን ካነበበችላት በኋላ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? እና አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው? የተባሉትን ቪዲዮዎች ሊንክ ላከችላት። ሴትየዋ ውይይቱን ለመቀጠል ፈቃደኛ ሆናለች።

ሐዋርያው ጳውሎስ ታስሮ በነበረበት ወቅት ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ ይመሠክር’ እንደነበረ ሁሉ ወንድሞቻችን ከቤታቸው መውጣት ባይችሉም ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል።—የሐዋርያት ሥራ 28:23

a በርካታ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጽሑፍ አንብበው መረዳት ስለሚከብዳቸው በምልክት ቋንቋ መስክ የሚያገለግሉ አንዳንድ አስፋፊዎች ቃላት ከመጻፍ ይልቅ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ሥዕሎችን ይጠቀማሉ።