በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 4, 2023 በኬረላ፣ ሕንድ በተካሄደው ልዩ ፕሮግራም ላይ ወንድሞችና እህቶች ሰላም ሲባባሉ

ኅዳር 17, 2023 | የታደሰው፦ ታኅሣሥ 8, 2023
ሕንድ

ወቅታዊ መረጃ—በሕንድ በተከሰተው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ስምንት ደረሰ

ወቅታዊ መረጃ—በሕንድ በተከሰተው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ስምንት ደረሰ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2, 2023 አንድ የ76 ዓመት ወንድም በኬረላ፣ ሕንድ በተከሰተው ፍንዳታ ከደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሕይወቱ አልፏል፤ ይህ ወንድም በጉባኤ ሽማግሌነትና በዘወትር አቅኚነት ያገለግል ነበር። ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 ማለትም ከአምስት ቀናት በኋላ ደግሞ በዘወትር አቅኚነት ታገለግል የነበረችው ሚስቱም ፍንዳታው ባደረሰባት ጉዳት የተነሳ ሕይወቷ አልፏል። በዚህ አሰቃቂ ጥቃት ምክንያት የሞቱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቁጥር ስምንት ደርሷል።

እሁድ፣ ጥቅምት 29, 2023 በኬረላ፣ ሕንድ በተካሄደ የክልል ስብሰባ ላይ የቦንብ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር። ከዚህ በፊት በዚህ ፍንዳታ እንደሞቱ ሪፖርት ከተደረጉት ሦስት ሰዎች በተጨማሪ አሁን አንድ ሌላ ወንድምና ሁለት እህቶችም ሕይወታቸው አልፏል። ከእነዚህ መካከል ቀደም ሲል የሞተችው የ12 ዓመት ልጅ እናትና ወንድም ይገኙበታል። ሌሎች 11 ወንድሞችና እህቶች አሁንም በሆስፒታል ይገኛሉ።

የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ በጥቃቱ ለተጎዱት ሁሉ አስፈላጊውን ማጽናኛና ማበረታቻ ለመስጠት ልዩ ስብሰባ እንዲያካሂድ ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር። ይህ ስብሰባ ኅዳር 4, 2023 የተካሄደ ሲሆን ፍንዳታው በተከሰተበት የክልል ስብሰባ ላይ በተመደቡት 21 ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ስብሰባ ላይ ተጋብዘዋል። በአካባቢው ባለ የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ተጨማሪ 1,300 ሰዎች ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ፕሮግራሙን ተከታትለዋል፤ በሆስፒታል ተኝተው ላሉት ወንድሞችና እህቶች ደግሞ ስብሰባው ተቀድቶላቸዋል። በቅርንጫፍ ቢሮው የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ መዝሙር 23:1⁠ን በመጥቀስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በግለሰብ ደረጃ የሚያሳየውን አሳቢነት ጎላ አድርጎ ገልጿል፤ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ጥቅስ ላይ መዝሙራዊው ይሖዋ ‘እረኛ ነው’ ሌላው ቀርቶ ‘አስደናቂ እረኛ ነው’ አላለም። መዝሙራዊው ይሖዋን የገለጸው ‘እረኛዬ’ በማለት ነው። ይሖዋ የእያንዳንዳችን ሁኔታ እንደሚያሳስበው ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው!”

እህቶች እርስ በርስ ሲጽናኑ

ፍንዳታው በተከሰተበት ወቅት በስፍራው የነበረ አንድ ወንድም አሁንም ለመተኛት እንደሚቸገር ተናግሯል። ያም ሆኖ በሆስፒታል የተኙትን ለመንከባከብ ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ። እንዲህ ብሏል፦ “እምነታቸውንና አዎንታዊ አመለካከታቸውን ማየቴ የራሴን ጭንቀት እንድረሳ ረድቶኛል። በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ ከባድ ሥቃይ ላይ ቢሆኑም ብዙዎቹ የመንግሥቱን መዝሙሮች በደስታ ይዘምሩ ነበር።” ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ከእነዚህ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል አንዳንዶቹ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ለመመለስ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ሆኖም የወንድማማች ማኅበራችን ለእነሱ ፍቅር ማሳየቱን እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። አሳቢ የሆነው አምላካችን ኃያል በሆነው እጁ የእያንዳንዳቸውን እጅ አጥብቆ እንደያዘ አልጠራጠርም። ይህን ማሰቤ በጣም ያበረታታኛል።!”

አንድነት ባለው በዚህ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የታቀፍን ሁሉ፣ ይሖዋ በሕንድ ያሉ ውድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ‘የተሰበረ ልብ እንደሚጠግንና ቁስላቸውን እንደሚፈውስ’ ማወቃችን ያጽናናል።—መዝሙር 147:3