በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሆካን ዴቪድሰን | የሕይወት ታሪክ

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስፋፋቱ ሥራ እገዛ ማበርከት

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስፋፋቱ ሥራ እገዛ ማበርከት

 ተወልጄ ያደግኩት በስዊድን ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ፣ አምላክ የለም የሚለው ትምህርት ተጽዕኖ አሳድሮብኝ ነበር። ስለዚህ አባቴ፣ እናቴና ታናሽ እህቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ እኔ የማጥናት ፍላጎት አልነበረኝም።

 ሆኖም አባቴ በተደጋጋሚ ይወተውተኝ ስለነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ላይ ለመገኘት ተስማማሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳይንሳዊ ጉዳዮች የያዘው ሐሳብ ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። በጊዜ ሂደት መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል የሚያስተምሩትና በዚያ የሚመሩት የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ እርግጠኛ ሆንኩ። በ1970 ከአባቴ ጋር አብሬ ተጠመቅኩ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እናቴና ሁለቱ እህቶቼም ተጠመቁ።

 አብዛኞቹ እኩዮቼ የሚያስደስታቸው ጭፈራና ዘና ማለት ብቻ ነበር። እውነት ለመናገር እኔም የ17 ዓመት ወጣት ሳለሁ እነሱ የሚመሩት ዘና ያለ ሕይወት ይማርከኝ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሩኝ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈላቸው ያስገኘላቸውን ደስታ ስመለከት እኔም እንደ እነሱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ፍላጎት አደረብኝ። በኋላም በ21 ዓመቴ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባሁ።

የተጠመቅኩት ከአባቴ ጋር (ከእኔ በስተ ግራ) በተመሳሳይ ቀን ላይ ነው

 የአቅኚነት አገልግሎት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ሳይ ቀደም ብዬ ባለመጀመሬ ተቆጨሁ። በተለይ የተቦርየ ወደተባለችው ከተማ ወደብ ሄዶ ማገልገል በጣም ያስደስተኝ ነበር፤ በዚያ በጭነት መርከቦቹ ላይ ለሚሠሩት ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች እንሰብክ ነበር።

 ባለፉት አምስት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የተለያየ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ምሥራቹን ማድረስ የምችልበት ለየት ያለ አጋጣሚ አግኝቻለሁ። እስቲ ከመጀመሪያው ጀምሮ ልተርክላችሁ።

ከሜፕስ ጋር የተያያዘ ሥራ

 በአቅኚነት አገልግሎት ራሴን ለመደገፍ ለተወሰኑ ቀናት ያህል የሕትመት ባለሙያ ሆኜ እሠራ ነበር። ወቅቱ የሕትመት ኢንዱስትሪው ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ የነበረበት ነው። ቀደም ሲል የሕትመት ሥራው ይከናወን የነበረው የብረት ቅይጦችን ተጠቅሞ ፊደላቱን በመቅረጽ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ጽሑፎችንና ምስሎችን በፎቶግራፍ አማካኝነት ማተም ተጀመረ። አዲስ ቴክኖሎጂ የነበረውን በኮምፒውተር የታገዘ የማተሚያ መሣሪያ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ተማርኩ።

በሠርጋችን ቀን

 በ1980 ልክ እንደ እኔ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከመጡ ሰዎች ጋር መገናኘትና አዳዲስ ባሕሎችን ማወቅ ከሚያስደስታት ሄለን የተባለች የዘወትር አቅኚ ጋር ተጋባን። ግባችን ጊልያድ ትምህርት ቤት ተምሮ ሚስዮናዊ መሆን ነበር።

 ሆኖም በሕትመት ሥራ ልምድ ስለነበረኝ እኔና ሄለን በስዊድን ቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። ድርጅቱ የሕትመት ሥራችንን ይበልጥ የሚያቀላጥፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ፍላጎት ነበረው። በመሆኑም በ1983 ሥልጠና እንድናገኝ በኒው ዮርክ ወዳለው ዎልኪል ቤቴል ተላክን፤ በዚያ ወንድሞች ሜፕስ a የተባለውን የኮምፒውተር ፕሮግራም እያዘጋጁ ነበር።

ለሆንግ ኮንግ፣ ለሜክሲኮ፣ ለስፔን እና ለናይጄርያ የተዘጋጁ የሜፕስ መሣሪያዎች ላይ ስሠራ

 ሜፕስ ጽሑፎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ፊደላት ለመጻፍና ይህን ጽሑፍ ከሥዕሎች ጋር አብሮ ለማቀናበር የሚያስችል የኮምፒውተር ፕሮግራም እንደሆነ ተረዳን። የተሰጠን ሥራ ሜፕስን ተጠቅሞ አዳዲስ ፊደላትን በማዘጋጀት ጽሑፎቻችን በተጨማሪ ቋንቋዎች እንዲታተሙ ማገዝ ነበር። ከአሥርተ ዓመታት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ቋንቋዎች ማዘጋጀት ችለዋል!

 ከጊዜ በኋላ እኔና ሄለን ተጨማሪ ቋንቋዎችን ወደ ሜፕስ የማካተት ሥራ ተሰጥቶን ወደ እስያ ተላክን። ምሥራቹ በብዙ ቋንቋዎች እንዲሰራጭ በማድረጉ ሥራ ለማገዝ ተዘጋጅተንና ጓጉተን ነበር!

ለየት ካሉ ባሕሎች ጋር መላመድ

 በ1986 ወደ ሕንድ ሄደን። በዚያ የነበረው ባሕል እኛ ከለመድነው ፈጽሞ የተለየ ነበር! በአሁኑ ጊዜ ሙምባይ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ቦምቤይ ስንደርስ ሁሉ ነገር አዲስ ሆነብን፤ የስዊድንና የሕንድ ባሕል ጽንፍና ጽንፍ ነው ሊባል ይችላል! የመጀመሪያው ሳምንት ላይ ወደ አገራችን ለመመለስ ተፈትነን ነበር።

 ከመጀመሪያው ሳምንት በኋላ ግን ሁለታችንም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደረስን። ‘ከድሮ ጀምሮ ፍላጎታችን ሚስዮናዊ መሆን ነበር። ታዲያ አሁን ምኞታችን ደርሶ ወደ ሌላ አገር ከተመደብን በኋላ እንዴት ተስፋ ቆርጠን እንመለሳለን? እነዚህን እንቅፋቶች መወጣት አለብን’ ብለን አሰብን።

 በመሆኑም ከሁኔታው ከመሸሽ ይልቅ በዚያ ስላለው ፈጽሞ የተለየ የአኗኗር ዘይቤ የቻልነውን ያህል ለማወቅ ወሰንን። እንዲህ ማድረግ ስንጀምር እኔና ሄለን ሕንድን በጣም እየወደድናት መጣን። እንዲያውም ከዚያ በኋላ ጉጅራቲ እና ፑንጃብኛ የተባሉ የሕንድ ቋንቋዎችን ተማርን።

ጉዞ ወደ ምያንማር

በምያንማር ባለ የስብሰባ አዳራሽ የአገሪቱን ባሕላዊ ልብስ ለብሰን

 በ1988 በቻይና፣ በሕንድ እና በታይላንድ መካከል ወደምትገኝ ምያንማር የተባለች አገር ተላክን። በምያንማር የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ውጥረት የነገሠበት ሲሆን አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ነበር። አገሪቱ ትጠቀምበት የነበረው ከላቲን ፊደላት ውጭ የሆነው የአጻጻፍ ስልት በወቅቱ ሜፕስ ውስጥ አልተካተተም ነበር፤ በዚህ ረገድ ሊያግዝ የሚችል ሌላ ሶፍትዌርም አልነበረም። ስለዚህ የመጀመሪያ ሥራችን ለአዲሱ የአጻጻፍ ስልት የሚሆኑ ፊደላትን በመቅረጹ ሥራ ማገዝና ፋይሎቹ ሜፕስ ላይ እንዲጫኑ ወደ ዎልኪል መውሰድ ነበር።

 አየር መንገድ ስንደርስ ሄለን የፊደላቱን ምስል በቦርሳዋ ይዛ ነበር። በወቅቱ ከነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት አንጻር ድንበር ጠባቂዎቹ በምያንማር ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ይዘን ቢያገኙን ያስሩን ነበር። ሆኖም ሄለን ስትፈተሽ ቦርሳዋን በእጇ ይዛ እጇን ከፍ አድርጋ ቆመች። ቦርሳዋን ማንም አላስተዋለውም!

ሜፕስ የጽሑፎቻችንን ጥራት ለማሻሻል ረድቶናል

 በምያንማር ያሉት ተርጓሚዎች ከአዳዲሶቹ ፊደላት በተጨማሪ ላፕቶፖች፣ ፕሪንተሮችና የሜፕስ አጠቃቀም ሥልጠና ተሰጣቸው። ከተርጓሚዎቹ መካከል አብዛኞቹ ኮምፒውተር አይተው እንኳ አያውቁም፤ ሆኖም ለመማር ፈቃደኞች ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ብረት ላይ በእጅ የሚቀረጹ ፊደላትን ተጠቅመው የሚያትሙትን ጊዜ ያለፈባቸው የንግድ ማተሚያ ቤቶች ከመጠቀም ተገላገሉ። ይህም የጽሑፎቻችን ጥራት በእጅጉ እንዲሻሻል አድርጓል።

ቀጣይ ጉዞ ወደ ኔፓል

 በ1991 እኔና ሄለን በሂማልያ ተራሮች በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ወደ ኔፓል ሄደን እንድንረዳ ተመደብን። በወቅቱ በአገሪቱ ያለው አንድ ጉባኤ ብቻ ሲሆን በኔፓልኛ ቋንቋ የተዘጋጁት ጽሑፎችም ጥቂት ነበሩ።

 ብዙም ሳይቆይ በአገሪቱ ተጨማሪ ጽሑፎችን መተርጎምና ማሰራጨት ተቻለ። በዛሬው ጊዜ በኔፓል ከ40 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 3,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ፤ በ2022 በተደረገው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ደግሞ ከ7,500 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል!

በላሁ ቋንቋ የተዘጋጀ ብሮሹር

 በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ቺያንግ ማይ በተባለች የታይላንድ ከተማ የሚኖሩ ሚስዮናውያን በላሁ ተራሮች ላይ ላሉ ጎሳዎች መስበክ ጀመሩ። ላሁ በላኦስ፣ በምያንማር፣ በታይላንድ፣ በቻይና እና በቬትናም ድንበሮች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚናገሩት ቋንቋ ነው። ሆኖም በዚህ ቋንቋ የተዘጋጀ ምንም ጽሑፍ አልነበረንም።

 ከሚስዮናውያኑ ጋር ያጠና የነበረ አንድ ወጣት “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” የተባለውን ብሮሹር ከታይ ቋንቋ ወደ ላሁ ተረጎመ። ከዚያም እሱና በላሁ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ገንዘብ አዋጥተው ብሮሹሩንና ገንዘቡን ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ላኩ። አብረው በላኩት ደብዳቤ ላይ እነሱ ከብሮሹሩ ላይ የተማሩትን እውነት ሁሉም የላሁ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲማሩ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው ነበር።

 ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኔና ሄለን የላሁ ቋንቋ ተርጓሚዎችን ስለ ሜፕስ አጠቃቀም የማሠልጠን መብት አገኘን። ከተርጓሚዎቹ መካከል አንዱ በቺያንግ ማይ ባለ የትርጉም ቢሮ ውስጥ የሚያገለግል በቅርቡ የተጠመቀ ወንድም ነበር። ይህ ወንድም “ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” የተባለውን ብሮሹር ወደ ላሁ የተረጎመው ያ ወጣት እንደሆነ ስናውቅ በጣም ተገረምን!

 በ1995 እኔና ሄለን በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ያሉ ተርጓሚዎች ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስፈልጓቸውን የሜፕስ መሣሪያዎች ለማሟላት ወደ ሕንድ ተመለስን። በዛሬው ጊዜ ጽሑፎቻችን በአገሪቱ በሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች ይገኛሉ፤ ስለዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና እድገት አድርገው መጠመቅ የሚችሉበት ሰፊ አጋጣሚ አላቸው።

አርኪ ሕይወት

 እኔና ሄለን ከ1999 ጀምሮ በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገልን እንገኛለን። በዋናው መሥሪያ ቤት ከሚገኘው የሜፕስ ፕሮግራሚንግ ቡድን ጋር አብረን እንሠራለን። በለንደን በጉጅራቲ እና በፑንጃብኛ መስክ ላሉ ሰዎች መስበክ የምንችልበት ሰፊ አጋጣሚ ያለን መሆኑ በጣም ያስደስተናል! jw.org ላይ አዲስ ቋንቋ በተጨመረ ቁጥር በክልላችን ውስጥ የዚያን ቋንቋ ተናጋሪዎች አግኝተን ለመስበክ ጥረት እናደርጋለን።

 ገና በወጣትነቴ ጭፈራና ዘና ማለት ብቻ የሚያስደስታቸውን እኩዮቼን ከመከተል ይልቅ መንፈሳዊ ግብ ለማውጣት በመወሰኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። እኔና ሄለን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስብ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ባደረግነው ውሳኔ ፈጽሞ አንቆጭም። ከ30 የሚበልጡ አገሮችን በመጎብኘት ምሥራቹ ከሁሉም ብሔር፣ ነገድና ቋንቋ ለተውጣጡ ሰዎች ሲዳረስ በገዛ ዓይናችን ማየት መቻላችን ልዩ መብት ነው!​—ራእይ 14:6

a ይህ ምሕፃረ ቃል በወቅቱ መልቲላንግዌጅ ኤሌክትሮኒክ ፎቶታይፕሴቲንግ ሲስተም የሚለውን መጠሪያ የሚወክል ነበር። በአሁኑ ጊዜ መጠሪያው መልቲላንግዌጅ ኤሌክትሮኒክ ፐብሊሺንግ ሲስተም ወደሚለው ተቀይሯል። ሜፕስ የጽሑፎችን የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ለማዘጋጀትም ያገለግላል።