በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጦር መሣሪያዎች፦ Anton Petrus/Moment via Getty Images; ገንዘብ፦ Wara1982/iStock via Getty Images Plus

ነቅታችሁ ጠብቁ!

ጦርነት የሚያስከትለው ኪሳራ የገንዘብ ብቻ ነው?

ጦርነት የሚያስከትለው ኪሳራ የገንዘብ ብቻ ነው?

 ለጦርነት የሚውለው ገንዘብ ይህ ነው የሚባል አይደለም።

  •   “በዓለም ዙሪያ ለተለያዩ ጦርነቶች የወጣው ገንዘብ 2.2 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል።”—ዘ ዋሽንግተን ፖስት፣ የካቲት 13, 2024

 ይሁንና ጦርነት የሚያስከትለው የገንዘብ ኪሳራ ብቻ አይደለም። የዩክሬንን ጦርነት እንደ ማሳያ እንመልከት።

  •   ወታደሮች። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በፊት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 500,000 ገደማ ወታደሮች እንደተገደሉ ወይም እንደቆሰሉ ይገመታል።

  •   ንጹሐን ዜጎች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ከ28,000 የሚበልጡ ንጹሐን ዜጎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል። ይሁንና አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ አስከፊ ጦርነት በንጹሐን ዜጎች ላይ ያስከተለው ዘላቂ ጉዳት በቁጥር ሊገለጽ የሚችል አይደለም።” a

 በዓለም ዙሪያ በጦርነትና በግጭት ሳቢያ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ እጅግ ከፍተኛ ነው።

  •   114 ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ዙሪያ በጦርነት ወይም በዓመፅ ምክንያት ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ የመስከረም 2023 ሪፖርት ያሳያል።

  •   783 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ረሃብ ተዳርገዋል። “አሁንም የረሃብ ዋነኛ መንስኤ ጦርነት ነው፤ በዓለም ዙሪያ ለረሃብ ከተጋለጡት ሰዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት በጦርነትና በዓመፅ በሚታመሱ አካባቢዎች ነው።”—የዓለም የምግብ ፕሮግራም

 ጦርነት ማብቂያ ይኖረው ይሆን? ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ በእርግጥ ይመጣ ይሆን? ምድር ያላት የተትረፈረፈ ሀብት ረሃብንና ድህነትን ለማስወገድ የሚውለው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የጦርነት ዘመን

 መጽሐፍ ቅዱስ ጦርነት እንደሚስፋፋ በትንቢት ተናግሯል፤ ጦርነትን ከአንድ ፈረስ ጋላቢ ጋር ያመሳስለዋል።

  •   “ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።”​—ራእይ 6:4

 ይህን ምሳሌያዊ ጋላቢ ሌሎች ሁለት ፈረሰኞች ይከተሉታል፤ እነሱም አስከፊ ረሃብንና በበሽታ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የሚከሰተውን ሞት ያመለክታሉ። (ራእይ 6:5-8) ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲሁም ትንቢቱ በዘመናችን እየተፈጸመ እንዳለ እርግጠኛ መሆን የምንችልበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “አራቱ ፈረሰኞች—እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ

 በቅርቡ፣ የምድር ሀብት ለጦርነት መዋሉ ያበቃል። ይሁንና እንዲህ ያለው ጊዜ የሚመጣው በሰዎች ጥረት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦

  •   አምላክ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።”​—መዝሙር 46:9

  •   አምላክ፣ ጦርነት ያስከተለውን አስከፊ ጉዳት ያስተካክላል። “እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”​—ራእይ 21:4

  •   አምላክ ሁሉም ሰው ዘላቂ ሰላም እንዲያገኝ ያደርጋል። “ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ የመኖሪያ ስፍራ፣ አስተማማኝ በሆነ መኖሪያና ጸጥታ በሰፈነበት የማረፊያ ቦታ ይኖራል።”​—ኢሳይያስ 32:18

 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ጦርነቶችና በዛሬው ጊዜ የምናያቸው ክስተቶች ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ እንደቀረበ ያሳያሉ።

 አምላክ በምድር ላይ ሰላምን የሚያሰፍነው እንዴት ነው? በሰማይ ላይ ባለው መንግሥቱ አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 6:10) የዚህን መንግሥት ምንነት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የሚለውን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ሚሮስላቭ ጄንካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአውሮፓ ረዳት ዋና ጸሐፊ፣ ታኅሣሥ 6, 2023።