በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአየር ንብረት ለውጥ ያጠፋን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአየር ንብረት ለውጥ ያጠፋን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “የአየር ንብረት የሚያስከትለው ውድመት የነገ ችግር አይደለም። አሁንም እንኳ ምድራችን ለሰው ልጆች የማትመች እየሆነች ነው።”—ዘ ጋርዲያን

 የሰው ዘር በገዛ እጁ ያመጣው ጣጣ ያስከተለበትን መዘዝ እያጨደ ነው። ለዓለም ሙቀት መጨመር ዋነኛው መንስኤ የሰው ልጆች የሚያደርጉት ነገር እንደሆነ ብዙ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። የዓለም ሙቀት መጨመር የምድር የአየር ንብረት እንዲቀየር አድርጓል፤ እንዲሁም አውዳሚ ውጤቶች እያስከተለ ነው። የሚከተሉትን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፦

  •   መጥፎ የአየር ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው፤ ለምሳሌ ያህል እጅግ ሞቃታማ ወቅቶች፣ ድርቅ እና ከባድ ዝናብ። እነዚህ የአየር ሁኔታዎች ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅና ሰደድ እሳት እንዲጨምር አድርገዋል።

  •   የበረዶ ግግሮችና የአርክቲክ የበረዶ ንጣፍ እየቀለጡ ነው።

  •   የባሕር ጠለል ከፍ እያለ ነው።

 የአየር ንብረት ቀውስ ያልነካው የምድር ክፍል የለም ማለት ይቻላል። በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ በ193 አገሮች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ፕላኔታችን የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማች ነው።” የአየር ንብረት ቀውስ በዓለም ዙሪያ ብዙዎችን ለሞትና ለመከራ እየዳረገ ነው። በዚህም የተነሳ የዓለም የጤና ድርጅት ይህን ችግር “በሰው ዘር ላይ የተደቀነ ከሁሉ የከፋ የጤና ስጋት” ሲል ጠርቶታል።

 ታዲያ ነገ ሁኔታዎች ይሻሻላሉ ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? በሚገባ! መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ የምናያቸው እነዚህ ክስተቶች እንደሚፈጸሙ አስቀድሞ ተናግሯል። ይህ ብቻ ግን አይደለም፤ አምላክ ጣልቃ ይገባል ብለን መጠበቅ የምንችለው ለምን እንደሆነና ምድራችንን ከጥፋት ለመታደግ ምን እንደሚያደርግም ይናገራል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአየር ንብረት ለውጥ እንደሚከሰት ትንቢት ተናግሯል?

 አዎ። በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የተከሰተው የአየር ንብረት ቀውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘመናችን ከተናገረው ትንቢት ጋር ይስማማል።

 ትንቢት፦ አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋል]።”—ራእይ 11:18

 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ይህ ትንቢት እንደሚናገረው የሰው ልጆች በሚያደርጉት ነገር የተነሳ ምድራችን ቋፍ ላይ ትደርሳለች። ከዓለም ሙቀት መጨመር ጋር በተያያዘ የሰው ልጆች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ምድርን እያጠፏት ነው።

 ይህ ትንቢት የሰው ልጆች ምድራችንን ይታደጓታል ብለን የማንጠብቅበትን አንድ ምክንያት ይነግረናል። አምላክ እርምጃ የሚወስደው የሰው ልጆች “ምድርን እያጠፉ” ሳለ እንደሆነ ልብ በል። ሰዎች በጥሩ ዓላማ ተነሳስተው የአየር ንብረትን ለማስተካከል ብዙ ጥረት ያደርጉ ይሆናል፤ ሆኖም የሰው ልጅ የሚያደርገው የትኛውም ጥረት ምድርን ለመታደግ በቂ አይሆንም።

 ትንቢት፦ “የሚያስፈሩ ነገሮች . . . ይታያሉ።”—ሉቃስ 21:11

 መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን “የሚያስፈሩ ነገሮች” እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተናግሯል። የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ዙሪያ አስፈሪ የአየር ሁኔታዎች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል። አሁን አሁን፣ በምድራችን ላይ የሚከሰተውን ጥፋት በመስጋት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

 ትንቢት፦ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ታማኝ ያልሆኑ፣ . . . ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ . . . ከዳተኞች፣ ግትሮች” ይሆናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4

 ለአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት የሆኑ ባሕርያት በዚህ ትንቢት ላይ ተጠቅሰዋል። መንግሥታትም ሆኑ የንግድ ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጡት ለትርፋቸው ነው፤ የቀጣዩ ትውልድ ደህንነት አያሳስባቸውም። እነዚህ ተቋማት የዓለምን ሙቀት መጠን ለመቀነስ ተባብረው ለመሥራት ይሞክሩ ይሆናል፤ ችግሩን ለመዋጋት ምን እርምጃ እንውሰድ በሚለው ላይ ግን ስምምነት ላይ አይደርሱም።

 ከዚህ ትንቢት እንደምንረዳው፣ በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ምድርን ለመታደግ ሲሉ አካሄዳቸውን ይቀይራሉ ብለን መጠበቅ አንችልም። እንዲያውም ትንቢቱ እንደሚገልጸው ራስ ወዳድ ሰዎች “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:13

አምላክ ጣልቃ እንደሚገባ እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው?

 ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንረዳው ፈጣሪያችን ይሖዋ a አምላክ የምድራችንም ሆነ የነዋሪዎቿ ደህንነት ያሳስበዋል። አምላክ ጣልቃ እንደሚገባ የሚጠቁሙንን ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እስቲ እንመልከት።

  1.  1. አምላክ “ምድርን የሠራት. . . መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [አይደለም]።”—ኢሳይያስ 45:18

     አምላክ ምድርን የፈጠረበት ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ኢሳይያስ 55:11) ምድር እንድትጠፋም ሆነ ሰው የማይኖርባት ቦታ እንድትሆን አይፈቅድም።

  2.  2. “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:11, 29

     አምላክ የሰው ልጆች ምድር ላይ ለዘላለም በሰላም እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል።

  3.  3. “ክፉዎች . . . ከምድር ገጽ ይጠፋሉ።”—ምሳሌ 2:22

     አምላክ ምድርን የሚያበላሹትን ጨምሮ ከክፋት ጎዳናቸው የማይመለሱ ሰዎችን ለማጥፋት ቃል ገብቷል።

አምላክ ምድርን ለመታደግ ምን ያደርጋል?

 አምላክ ምድርን በተመለከተ የገባውን ቃል የሚፈጽመው እንዴት ነው? ባቋቋመው ዓለም አቀፍ መንግሥት አማካኝነት ነው፤ ይህ መንግሥት፣ የአምላክ መንግሥት ተብሎ ይጠራል። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት የሚገዛው ከሰማይ ሆኖ ነው። በመሆኑም ምድርንና ሥነ ምህዳሯን በተመለከተ የሰው ልጆች ካቋቋሟቸው መንግሥታት ጋር ለመነጋገር ሲል ለድርድር መቀመጥ አያስፈልገውም። እንዲያውም ምድርን የሚያስተዳድረው እነዚህን መንግሥታት ካጠፋ በኋላ ነው።—ዳንኤል 2:44

 የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ላሉ የሰው ልጆችም ሆነ ለተፈጥሮ ብዙ መልካም ነገሮችን ያደርጋል። (መዝሙር 96:10-13) ይሖዋ አምላካችን በመንግሥቱ አማካኝነት የሚከተሉትን ነገሮች ያደርጋል፦

  •   የምድርን ሥነ ምህዳር ያስተካክላል

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤ በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1

     ይህ ጥቅስ ምን ተስፋ ይዞልናል? ይሖዋ ምድራችንን ይፈውሳታል፤ የሰው ልጆች ከባድ ውድመት ያደረሱባቸው ቦታዎችም እንኳ ይታደሳሉ።

  •   መጥፎ የአየር ሁኔታዎችን ይቆጣጠራል

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ] አውሎ ነፋሱ እንዲቆም ያደርጋል፤ የባሕሩም ሞገዶች ጸጥ ይላሉ።”—መዝሙር 107:29

     ይህ ጥቅስ ምን ተስፋ ይዞልናል? ይሖዋ የምድርን ተፈጥሯዊ ኃይሎች የመቆጣጠር ኃይል አለው። ወደፊት ሰዎች በመጥፎ የአየር ሁኔታ የተነሳ ለመከራ አይዳረጉም።

  •   የሰው ልጆች ምድርን እንዲንከባከቡ ያሠለጥናቸዋል

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ።”—መዝሙር 32:8

     ይህ ጥቅስ ምን ተስፋ ይዞልናል? ይሖዋ የሰው ልጆች ምድርን እንዲንከባከቡ በአደራ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15) የምድር ባለ አደራ በመሆን የተሰጠንን ኃላፊነት እንዴት እንደምንወጣም ሆነ ከተፈጥሮ ጋር እንዴት ተስማምተን እንደምንኖር ያስተምረናል።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።