በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

DEA/G. Dagli Orti/De Agostini via Getty Images

ሁልድሪክ ዝዊንግሊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ

ሁልድሪክ ዝዊንግሊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ

 በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ቅን ልብ ያላቸው ሃይማኖተኛ ሰዎች የሚያምኑበት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለመሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላሉ። በ16ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ የነበረው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ለምን? ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ማግኘት አይችሉም ነበር። በመሆኑም ብዙዎች ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምረውን ትምህርት በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር ማመሣከር የሚችሉበት አጋጣሚ አልነበራቸውም። ቀሳውስቱም ቢሆኑ በዚህ ረገድ እምብዛም እርዳታ አላበረከቱም። ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክሪስቲያን ቸርች የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “በስዊዘርላንድ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ምግባረ ብልሹ ነበር። ቀሳውስቱ ጭፍን፣ በአጉል እምነት የሚመሩና በሥነ ምግባር ያዘቀጡ ነበሩ።”

 ሁልድሪክ ዝዊንግሊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ፍለጋ ማድረግ የጀመረው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበር። ታዲያ ምን አገኘ? የተማረውን ነገር ለሌሎች ያካፍል የነበረው እንዴት ነው? እኛስ ከእሱ ሕይወትና ከሚያምንባቸው ነገሮች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

ዝዊንግሊ ፍለጋውን ጀመረ

 ዝዊንግሊ በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የካቶሊክ ቄስ ለመሆን ቆርጦ ተነሳ። ቀሳውስት ለመሆን ከሚፈልጉ ሰዎች እንደሚጠበቀው እሱም ፍልስፍና፣ የቤተ ክርስቲያኗን ወጎች እንዲሁም “የሃይማኖት አባቶች” የጻፏቸውን ጽሑፎች ማጥናት ይጠበቅበት ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ግን ከመሥፈርቶቹ ውስጥ አልተካተተም።

 ዝዊንግሊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያገኘው እንዴት ነው? በባዝል፣ ስዊዘርላንድ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ ሳለ ቶማስ ቪተንባክ የተባለ ሰው በሚያስተምርባቸው ክፍለ ጊዜዎች ላይ ይገኝ ነበር፤ ቶማስ ቪተንባክ ቤተ ክርስቲያኗ የምትከተለውን የጸሎተ ፍትሐት ሥርዓት a ይቃወም ነበር። አንድ የታሪክ ዘጋቢ እንደተናገረው ዝዊንግሊ “የክርስቶስ ሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኃጢአታችን የተከፈለ መሥዋዕት እንደሆነ የተማረው [ከቪተንባክ] ነው።” (1 ጴጥሮስ 3:18) ዝዊንግሊ የኃጢአት ይቅርታ የሚገኝበት ብቸኛው መሠረት የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሆነ ሲረዳ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ገንዘብ በመቀበል የኃጢአት ይቅርታ ሊያስገኙ እንደሚችሉ የሚገልጸውን ትምህርት መቃወም ጀመረ። (የሐዋርያት ሥራ 8:20) ያም ሆኖ ዝዊንግሊ በትምህርቱ ቀጥሎ በ22 ዓመቱ የካቶሊክ ፓስተር ሆነ።

 ዝዊንግሊ በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ፣ በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መጀመሪያ የተጻፈበትን ቋንቋ ለመረዳት ሲል በራሱ ግሪክኛ ተማረ። ከዚህም በተጨማሪ የኢራስመስን ሥራዎች በመመርመር መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው በአምላክና በሰዎች መካከል ያለው ብቸኛው መካከለኛ ኢየሱስ መሆኑን ተገነዘበ። (1 ጢሞቴዎስ 2:5) በመሆኑም ቅዱሳን፣ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ እንደሚረዱ የሚገልጸውን የካቶሊክ ትምህርት መጠራጠር ጀመረ።

 ዝዊንግሊ 30ዎቹ ዕድሜ ላይ ሲደርስ እውነትን ለማግኘት የሚያደርገውን ፍለጋ አጧጧፈ። በሌላ በኩል ግን ጣሊያንን ለመቆጣጠር ሲባል በአውሮፓ በተካሄዱት ተከታታይ ጦርነቶች ላይ የሠራዊቱ ቄስ ሆኖ ያገለግል ነበር። በ1515 በማሪንያኖ ጦርነት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ካቶሊኮች በሌሎች ካቶሊኮች እጅ ሲገደሉ ተመልክቷል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በእጁ የገለበጠ ከመሆኑም ሌላ አብዛኞቹን ክፍሎች በቃሉ መያዝ ችሎ ነበር። በ1519 ዝዊንግሊ የሚኖረው የስዊዘርላንድ የፖለቲካ ማዕከል በሆነችው በዙሪክ ነበር። ‘ቤተ ክርስቲያኗ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያልተመሠረተን ማንኛውንም ትምህርት ማስተማሯን ማቆም አለባት’ የሚል አቋም የያዘው እዚያ ሳለ ነው። ሆኖም ሌሎችም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ መርዳት የሚችለው እንዴት ነው?

“እንዲህ ያለ ስብከት ሰምተን አናውቅም”

 ዝዊንግሊ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲሰሙ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ውድቅ ያደርጋሉ የሚል እምነት ነበረው። በመሆኑም በዙሪክ ታዋቂ የነበረው የግሮስመንስተር ቤተ ክርስቲያን ቄስ ሆኖ ሲመረጥ ስብከቱን የጀመረው አቋሙን በድፍረት በመግለጽ ነበር፤ ቀሳውስት ለዘመናት ሲደግሙ የኖሩትን የቅዳሴ መጽሐፍ b ከዚህ በኋላ እንደማያነብ ገለጸ። ከዚህ ይልቅ ወንጌልን ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምዕራፍ በምዕራፍ፣ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚሰብክ ተናገረ። ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማብራራት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚያስተምሩትን ሐሳብ ከመጠቀም ይልቅ እዚያው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ጥቅሶችን ለመጠቀም ወሰነ። ይህን የሚያደርገው ከበድ ያሉ ጥቅሶችን፣ ለመረዳት ቀላል በሆኑ ጥቅሶች በመፍታት ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

Sergio Azenha/Alamy Stock Photo

በዙሪክ ያለው የግሮስመንስተር ቤተ ክርስቲያን

 ዝዊንግሊ በስብከቱ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ለዕለት ተዕለት ሕይወት የሚጠቅም ምክር እንደያዘ ያስተምር ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ያስተምር እንዲሁም ለኢየሱስ እናት ለማርያም አምልኮ ማቅረብለቅዱሳን መጸለይና ገንዘብ እያስከፈሉ ጸሎተ ፍትሐት ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጽ ነበር፤ የቀሳውስቱን የሥነ ምግባር ብልሹነትም አውግዟል። ታዲያ ሰዎች ምን ምላሽ ሰጡ? የመጀመሪያ ስብከቱን ካቀረበ በኋላ አንዳንዶች “እንዲህ ያለ ስብከት ሰምተን አናውቅም” በማለት ተናግረዋል። አንድ የታሪክ ጸሐፊ የዝዊንግሊን ስብከት ያዳምጡ ስለነበሩ ካቶሊኮች ሲጽፉ “የቀሳውስቱ ጭፍንነትና ምግባረ ብልሹነት አንገፍግፏቸው ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያቆሙ ሰዎች መመለስ ጀመሩ” ብለዋል።

 በ1522 ቀሳውስቱ የዙሪክ ፖለቲከኞችን በማነሳሳት የቤተ ክርስቲያኗን አስተምህሮ የሚቃወሙ ልማዶችን እንዲያስቆሙ ለማድረግ ሞከሩ። በውጤቱም ዝዊንግሊ በመናፍቅነት ተወነጀለ። የሚያምንባቸውን ነገሮች ለድርድር ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆን ከካቶሊክ ቄስነት ራሱን አገለለ።

ዝዊንግሊ ምን አደረገ?

 ዝዊንግሊ ከቄስነት ኃላፊነቱ ቢወርድም እንደ ቀድሞው መስበኩንና ሌሎችም እምነቱን እንዲጋሩ ማስተማሩን ቀጠለ። በስብከቱ የተነሳ እውቅናን ያተረፈ ሲሆን ይህም በዙሪክ ፖለቲከኞች ዘንድ ተሰሚነት እንዲኖረው አደረገ። በፖለቲካው መስክ ያገኘውን ተሰሚነት ተጠቅሞ ሃይማኖታዊ ለውጦችን ማራመድ ጀመረ። ለምሳሌ በ1523 በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያልተመሠረተን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ትምህርት ማስተማር እንደ ወንጀል እንዲቆጠር የዙሪክን የሕግ አካላት አሳመነ። በ1524 ደግሞ ጣዖት አምልኮን የሚከለክል ሕግ እንዲያወጡ አሳመናቸው። የሕዝቡን ፈቃድ ያገኙት የሕግ አስከባሪዎች ከአካባቢው ሰባኪዎች ጋር በመተባበር መሠዊያዎችን፣ ጣዖታትን፣ ምስሎችንና ጥንታዊ ማምለኪያዎችን ለማፈራረስ የተደረገውን ሰፊ ዘመቻ በበላይነት ተከታትለዋል። ዝዊንግሊ—ጎድስ አርምድ ፕሮፌት የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ቫይኪንግ የተባሉት ጎሳዎች በአምልኮ ቦታዎች ላይ ዝርፊያ ካካሄዱ ወዲህ የምዕራቡ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ሆን ተብሎ የተሰነዘረ ጥፋት አስተናግዶ አያውቅም።” በ1525 ዝዊንግሊ በባለሥልጣናት ላይ ተጽዕኖ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኗ ይዞታዎች ወደ ሆስፒታልነት እንዲቀየሩ እንዲሁም መነኮሳት ማግባት እንዲፈቀድላቸው አደረገ። በተጨማሪም የቁርባን ሥርዓቱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተገለጸው መሠረት ቀለል ያለ ሥነ ሥርዓት እንዲሆን ሐሳብ አቀረበ። (1 ቆሮንቶስ 11:23-25) የታሪክ ምሁራን ዝዊንግሊ ያደረገው እንቅስቃሴ የዙሪክን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አካላት አንድ በማድረግ ለተሃድሶ ንቅናቄና ለአዲሱ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሠረት እንደጣለ ይናገራሉ።

በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው የዙሪክ መጽሐፍ ቅዱስ የ1536 እትም

 ዝዊንግሊ ካከናወናቸው ሥራዎች ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራው ነው። በ1520ዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከተጻፈባቸው ከዕብራይስጥና ከግሪክ እንዲሁም ከግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም እና ከላቲን ቩልጌት ከሚተረጉም የምሁራን ቡድን ጋር አብሮ ይሠራ ነበር። ይህ ቡድን የሚከተለው አሠራር ቀላል ነበር። ከበኩረ ጽሑፉና ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ እያንዳንዱን ጥቅስ ያነብባሉ። ከዚያም በጥቅሱ ትርጉም ላይ ከተወያዩ በኋላ የደረሱበትን ድምዳሜ ይጽፋሉ። የአምላክን ቃል ለማብራራትና ለመተርጎም ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ በ1531 ባለ አንድ ጥራዙን የዙሪክ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ማዘጋጀት ቻሉ።

 ዝዊንግሊ ቅን ሊሆን ቢችልም ትዕግሥት የለሽና ቁጡ ሰው ነበር። ለምሳሌ በ1525 አናባብቲስት በተባለው ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በተመሠረተው የክስ ሂደት ላይ ተሳትፎ ነበር፤ የዚህ እምነት ተከታዮች እሱ የሚያምንበትን ሕፃናት ሊጠመቁ ይገባል የሚለውን ትምህርት አይቀበሉም። በኋላ ላይ ፍርድ ቤቶች የሕፃናትን ጥምቀት መቃወሙን የሚቀጥል ማንኛውም ሰው እንዲገደል ውሳኔ ሲያስተላልፉ ዝዊንግሊ ይህን ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ድርጊት አልተቃወመም። በተጨማሪም የፖለቲካ መሪዎች የተሃድሶ ንቅናቄውን ለማስፋፋት የጦር ኃይል እንዲጠቀሙ አነሳስቷል። እንደዚያም ሆኖ ግን በስዊዘርላንድ አክራሪ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ያሉባቸው አካባቢዎች የተሃድሶ ንቅናቄውን ተቃወሙ። ይህም የእርስ በርስ ጦርነት አስነሳ። ዝዊንግሊ የዙሪክ ሠራዊትን አጅቦ ወደ ጦር ሜዳ የወጣ ሲሆን በዚያም በ47 ዓመቱ ተገደለ።

ዝዊንግሊ ለትውልድ የተወው ውርስ

 ሁልድሪክ ዝዊንግሊ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ንቅናቄ መሪዎች የሆኑትን የማርቲን ሉተርን እና የጆን ካልቪንን ያህል ባይሆንም በታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው። ዝዊንግሊ የሮም ካቶሊክ ሃይማኖትን ከሉተር ይበልጥ በግልጽ በመቃወም ለካልቪን መንገድ ጠርጓል። በዚህም የተነሳ ‘የተሃድሶ ንቅናቄው ሦስተኛ ሰው’ የሚል ስም ሊያተርፍ ችሏል።

 ዝዊንግሊ የተወው ውርስ ሁለት ገጽታ ያለው ነው ሊባል ይችላል። የሚያምንባቸውን ነገሮች ለማስፋፋት ሲል ፖለቲካና ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ ነበር። እንዲህ በማድረግ ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ያልነበረውንና ደቀ መዛሙርቱ ጠላቶቻቸውን እንዲገድሉ ሳይሆን እንዲወዱ ያስተማረውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ሳይከተል ቀርቷል።—ማቴዎስ 5:43, 44፤ ዮሐንስ 6:14, 15

 ያም ሆኖ ዝዊንግሊ የተማረውን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ቆርጦ የተነሳ ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በመሆኑ ይታወሳል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ያገኘ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም ይህን እውነት እንዲያገኙ ረድቷል።

a ጸሎተ ፍትሐት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያወጡት ድንጋጌ ሲሆን የሃይማኖት መሪዎቹ ይህ ሥነ ሥርዓት ሰዎች ከሞቱ በኋላ በመንጽሔ የሚደርስባቸውን ቅጣት ለመቀነስ አልፎ ተርፎም ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እንደሚረዳ ይናገራሉ።

b የቅዳሴ መጽሐፍ የሚባለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስቀድመው ተመርጠው በዓመቱ ውስጥ የሚነበቡ ጥቅሶችን የያዘ መጽሐፍ ነው።