በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር ትጠፋ ይሆን?

ምድር ትጠፋ ይሆን?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

ምድር ትጠፋ ይሆን?

ምድራችን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አደጋ ትጠፋለች ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት የለም። እንዲህ ብለን በእርግጠኝነት የምንናገረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላክ፣ ምድር ‘ለዘላለም እንደማትናወጥ’ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 104:5) መጽሐፍ ቅዱስ “ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” ይላል።—መክብብ 1:4

በመዝሙር 104:5 ላይ የሚገኘው “ዘላለም” የሚለው ቃል መጀመሪያ በተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ኦላም እና አድ በሚሉ ሁለት ቃላት ተገልጿል። ኦላም የሚለው ቃል “ብዙ ዓመታት” ወይም “ማብቂያ የሌለው” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ሃርካቪ ያዘጋጁት ስቱደንትስ ሂብሪው ኤንድ ካልዲ ዲክሽነሪ እንደሚለው ከሆነ አድ የሚለው ቃል “ዘላቂ፣ መጨረሻ የሌለው፣ ዘላለማዊ፣ ፍጻሜ የሌለው” ማለት ነው። እነዚህ ሁለት የዕብራይስጥ ቃላት ምድር የማትጠፋ ስለመሆኗ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርጉናል። ምድር ለዘላለም እንደምትኖር እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርጉ ሦስት ተጨማሪ ምክንያቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ አምላክ ምድርን የፈጠረው የሰው ልጆች በደስታ የሚኖሩባት ውብ ገነት እንድትሆን እንጂ ጠፍ ሆና እንድትቀር አይደለም። ኢሳይያስ 45:18 ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ሰማያትን የፈጠረ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን [አይደለም]።”

በሁለተኛ ደረጃ፣ አምላክ እሱን ለመታዘዝ የሚመርጡ ሰዎች ወደፊት በዚህች ምድር ላይ በሰላም ለዘላለም እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። ሚክያስ 4:4 የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።” በመሆኑም ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ምድር የሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ መሆን አለባት። አለበለዚያ ግን አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሁሉ መና ይቀራሉ ማለት ነው።—መዝሙር 119:90፤ ኢሳይያስ 55:11፤ 1 ዮሐንስ 2:17

በሦስተኛ ደረጃ፣ አምላክ የሰው ልጆች ምድርን እንዲንከባከቡ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። የአምላክ ቃል “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል። (መዝሙር 115:16) አንድ አፍቃሪ አባት ለልጁ በጣም የሚያምር ስጦታ ከሰጠው በኋላ ስጦታውን ነጥቆ ይሰባብርበታል ብለህ ታስባለህ? በጭራሽ! በተመሳሳይም ይሖዋ በምድርም ሆነ በነዋሪዎቿ ላይ እንዲህ ያለ ነገር አያደርግም። ምክንያቱም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።”—1 ዮሐንስ 4:8

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት አባቱ የተናገራቸው ነገሮች መፈጸማቸው እንደማይቀር ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 17:17) ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ደግሞ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝሙር 37:29፤ ቲቶ 1:2

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሉል፦ Based on NASA photo