በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጽናኑ—ሌሎችንም አጽናኑ

ተጽናኑ—ሌሎችንም አጽናኑ

ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም እንታመማለን፤ እንዲያውም አንዳንዶቻችን ከባድ የጤና ችግር ሊያጋጥመን ይችላል። እንዲህ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

ያጋጠመንን ችግር መቋቋም እንድንችል የሚረዳን አንዱ ጠቃሚ ነገር ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችንና ከእምነት ባልንጀሮቻችን የምናገኘው ማጽናኛ ነው።

አንድ ጓደኛችን በደግነትና በፍቅር የሚሰጠን ማበረታቻ እንደሚፈውስና ብርታት እንደሚሰጥ ማስታገሻ ቅባት ነው። (ምሳሌ 16:24፤ 18:24፤ 25:11) ይሁንና እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያሳስባቸው እነሱ ማጽናኛ ማግኘታቸው ብቻ አይደለም። “አምላክ [እነሱን] እያጽናናበት ባለው ማጽናኛ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ማጽናናት” እንዲችሉ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። (2 ቆሮ. 1:4፤ ሉቃስ 6:31) በሜክሲኮ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው አንቶንዮ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር።

አንቶንዮ ሊምፎማ የተባለ የደም ካንሰር እንደያዘው ባወቀ ጊዜ በጭንቀት ተውጦ ነበር። ይሁንና ያደረበትን አፍራሽ ስሜት ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል። እንዴት? የመንግሥቱን መዝሙሮች ለማስታወስ ይጥር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጮክ ብሎ እየዘመረ በስንኞቹ ላይ ያሰላስል ነበር። በተጨማሪም ጮክ ብሎ መጸለዩና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡ ከፍተኛ ማጽናኛ አስገኝቶለታል።

ይሁን እንጂ አንቶንዮ ከፍተኛ ማጽናኛ ካስገኙለት ነገሮች አንዱ የእምነት ባልንጀሮቹ ያደረጉለት እርዳታ እንደሆነ ተገንዝቧል። እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እኔና ባለቤቴ በጭንቀት ስንዋጥ የጉባኤ ሽማግሌ የሆነ አንድ ዘመዳችን መጥቶ እንዲጸልይልን እንጠይቀው ነበር። ይህ እንድንጽናና እንዲሁም እንድንረጋጋ ረድቶናል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እንዲያውም ቤተሰባችንና መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ባደረጉልን እርዳታ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደረብንን አፍራሽ ስሜት መቋቋም ችለናል።” እንዲህ ያሉ አፍቃሪና አሳቢ ወዳጆች በማግኘቱ እጅግ አመስጋኝ ነው!

ጭንቀት በሚያጋጥመን ጊዜ እርዳታ የምናገኝበት ሌላው ምንጭ ቃል የተገባልን መንፈስ ቅዱስ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ “ነፃ ስጦታ” እንደሆነ ተናግሯል። (ሥራ 2:38) በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ብዙዎች በመንፈስ በተቀቡ ጊዜ ይህ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። ይሁንና ጴጥሮስ እየተናገረ የነበረው ቅቡዓንን አስመልክቶ ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ ሁላችንም ልናገኘው የምንችለው ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ እንደ ልብ የሚገኝ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ በብዛት እንዲሰጥህ ለምን አትጠይቅም?—ኢሳ. 40:28-31

መከራ ለደረሰባቸው ጥልቅ አሳቢነት አሳዩ

ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ መከራ አሳልፏል፤ እንዲያውም ለሞት የተጋለጠባቸው ወቅቶች ነበሩ። (2 ቆሮ. 1:8-10) ሆኖም ጳውሎስ ሕይወቴን አጣለሁ የሚል ከልክ ያለፈ ፍርሃት አልተሰማውም። አምላክ እንደሚደግፈው በማወቁ ተጽናንቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የተባረከ ይሁን፤ . . . እሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።” (2 ቆሮ. 1:3, 4) ጳውሎስ የገጠሙት ችግሮች ስሜቱን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ በጽናት ያሳለፋቸው ፈተናዎች ለሰው የርኅራኄ ስሜት እንዲያድርበት የረዱት በመሆኑ ሌሎችን በችግራቸው ጊዜ ለማጽናናት የተሻለ ብቃት እንዲኖረው አስችለውታል።

አንቶንዮ ከሕመሙ ካገገመ በኋላ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ቀድሞም ለእምነት ባልንጀሮቹ አሳቢነት ያሳይ የነበረ ቢሆንም ከታመመ በኋላ ግን እሱና ባለቤቱ የታመሙትን ለመጠየቅና ለማበረታታት ለየት ያለ ጥረት አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንቶንዮ ከከባድ የጤና ችግር ጋር ይታገል የነበረን አንድ ክርስቲያን ከጠየቀ በኋላ ይህ ወንድም ወደ ስብሰባ መሄድ እንደማይፈልግ ተገነዘበ። አንቶንዮ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ወንድም ወደ ጉባኤ መሄድ ያልፈለገው ይሖዋን ወይም ወንድሞችን ስለማይወድ ሳይሆን በሽታው ካሳደረበት ተጽዕኖ የተነሳ አልረባም የሚል ስሜት ስለተሰማው ነው።”

አንቶንዮ ከሌሎች ጋር ለመጫወት አንድ ላይ ተሰብስበው ሳለ የታመመውን ወንድም ለማበረታታት ሲል እነሱን ወክሎ እንዲጸልይ ጋበዘው። ወንድም ብቁ እንዳልሆነ ቢሰማውም እንኳ ለመጸለይ ተስማማ። አንቶንዮ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ወንድም ግሩም የሆነ ጸሎት ያቀረበ ሲሆን ከዚያ በኋላ ስሜቱ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ደግሞም ተፈላጊ እንደሆነ ተሰማው።”

አዎ፣ ይብዛም ይነስ ሁላችንም አንድ ዓይነት መከራ ተቋቁመን ለመኖር የተገደድንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ሆኖም ጳውሎስ እንደተናገረው እንዲህ ያለው ሁኔታ ሌሎች ችግር ሲያጋጥማቸው እነሱን ለማጽናናት ብቃት እንዲኖረን ያስችለናል። እንግዲያው የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚደርስባቸው መከራ የሚሰማን ዓይነት ሰዎች እንሁን፤ እንዲሁም ለሌሎች የመጽናኛ ምንጭ በመሆን አምላካችንን ይሖዋን እንምሰል።