በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚልክያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የሚልክያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የሚልክያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ እንደገና የመገንባቱ ሥራ ከተጠናቀቀ 70 ዓመታት አልፈዋል። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የአይሁዳውያኑ መንፈሳዊነት እየተዳከመ ነው። ካህናቱም ሳይቀር ምግባረ ብልሹ ሆነዋል። አይሁዳውያኑ ያሉበትን ሁኔታ እንዲገነዘቡና በመንፈሳዊ እንዲነቃቁ ማን ሊረዳቸው ይችላል? ይሖዋ ይህንን ኃላፊነት ለነቢዩ ሚልክያስ ሰጠው።

ሚልክያስ ጠንከር ባለ መንገድ የጻፈው ይህ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጨረሻ መጽሐፍ፣ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ትንቢት ይዟል። ሚልክያስ ለጻፈው ትንቢት ትኩረት መስጠታችን አሁን ያለንበት ክፉ ሥርዓት ለሚጠፋበት ‘ለታላቁና ለሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ እንድንዘጋጅ ይረዳናል።—ሚልክያስ 4:5

ካህናቱ “ብዙዎች እንዲሰናከሉ” አድርገዋል

(ሚልክያስ 1:1 እስከ 2:17)

ይሖዋ ስለ እስራኤላውያን ምን እንደሚሰማው ሲገልጽ “እኔ ወድጃችኋለሁ” ብሏል። ካህናቱ ግን የአምላክን ስም አቃልለዋል። እንዴት? ‘በመሠዊያው ላይ የረከሰ ምግብ በማስቀመጥ’ እንዲሁም “አንካሳውን ወይም በሽተኛውን እንስሳ” መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ ነው።—ሚልክያስ 1:2, 6-8

ካህናቱ ‘በትምህርታቸው ብዙዎች እንዲሰናከሉ አድርገዋል።’ ሕዝቡ ‘እርስ በርሳቸው ታማኝነትን አጕድለዋል።’ አንዳንዶች፣ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሚስቶች አግብተዋል። ሌሎች ደግሞ ‘የወጣትነት ሚስቶቻቸውን’ አታልለዋል።—ሚልክያስ 2:8, 10, 11, 14-16

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

2:3—በካህናቱ ፊት ላይ “ፋንድያ . . . እበትናለሁ” የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው? በሕጉ መሠረት መሥዋዕት የሚሆኑት እንስሳት ፈርስ ከከተማው ውጭ ተወስዶ ይቃጠል ነበር። (ዘሌዋውያን 16:27) ይሖዋ በካህናቱ ፊት ላይ ፋንድያ መበተኑ፣ መሥዋዕታቸውን እንዳልተቀበለውና መሥዋዕቱን ያቀረቡት ሰዎች በፊቱ አስጸያፊ እንደሆኑ ያሳያል።

2:13—የይሖዋ መሠዊያ የተጥለቀለቀው በእነማን እንባ ነበር? መሠዊያው የተጥለቀለቀው ወደ ቤተ መቅደሱ መጥተው ልባቸውን በይሖዋ ፊት በሚያፈሱ ሚስቶች እንባ ነበር። እነዚህ ሚስቶች ይህን ያህል እንዲያዝኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? አይሁዳውያን የሆኑት ባሎቻቸው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ፍቺ ፈጽመው ትተዋቸው ስለሄዱ ነበር፤ ወንዶቹ እንዲህ ያደረጉት አይሁዳውያን ያልሆኑ ወጣት ሴቶችን ለማግባት ሳይሆን አይቀርም።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:10 የቤተ መቅደሱን በር እንደ መዝጋት ወይም በመሠዊያ ላይ እሳት እንደ ማንደድ ላሉ ቀላል አገልግሎቶች ክፍያ የሚጠይቁት ስግብግብ ካህናት በሚያቀርቡት መሥዋዕት ይሖዋ አልተደሰተም። ክርስቲያናዊውን አገልግሎታችንን ጨምሮ ለይሖዋ አምልኮ እንድናቀርብ የሚገፋፋን ለአምላክና ለሰዎች ያለን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንጂ የገንዘብ ጥቅም የማግኘት ፍላጎት ሊሆን አይገባም!—ማቴዎስ 22:37-39፤ 2 ቆሮንቶስ 11:7

1:14፤ 2:17 ይሖዋ ግብዝነትን በቸልታ አይመለከተውም።

2:7-9 በጉባኤ ውስጥ የማስተማር ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡት ትምህርት፣ የአምላክ ቃል ከሆኑት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲሁም ‘በታማኙ መጋቢ’ ከሚዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው።—ሉቃስ 12:42፤ ያዕቆብ 3:11

2:10, 11 ይሖዋ፣ አምላኪዎቹ “በጌታ” ብቻ እንዲያገቡ የሰጠውን ምክር በቁም ነገር እንዲመለከቱት ይጠብቅባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:39

2:15, 16 እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች በወጣትነታቸው ካገቧቸው ሚስቶቻቸው ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ያከብራሉ።

‘ጌታ ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል’

(ሚልክያስ 3:1 እስከ 4:6)

‘ከቃል ኪዳኑ መልእክተኛ [ከኢየሱስ ክርስቶስ]’ ጋር በመሆን “ጌታ [ይሖዋ አምላክ] በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል።” አምላክ ‘ለፍርድ ወደ [ሕዝቡ] ይመጣል፤’ እንዲሁም በክፉ አድራጊዎች ሁሉ ላይ ለመመሥከር ይፈጥናል። ከዚህም በላይ ይሖዋን ለሚፈሩ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ይጻፋል።—ሚልክያስ 3:1, 3, 5, 16

“እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን” መጥቶ ክፉዎችን ሁሉ ያቃጥላቸዋል። ይህ ቀን ከመምጣቱ በፊት ግን “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች [ለመመለስ]” ነቢይ ይላካል።—ሚልክያስ 4:1, 5, 6

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

3:1-3—“ጌታ” እና “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ወደ ቤተ መቅደሱ የመጡት መቼ ነበር? ከእነሱ በፊት የተላከውስ ማን ነው? ይሖዋ፣ ኒሳን 10 ቀን 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተወካዩ አማካኝነት ወደ ቤተ መቅደሱ በመምጣት ቤተ መቅደሱን አጽድቷል። ይህ የሆነው ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ባስወጣበት ወቅት ነው። (ማርቆስ 11:15) ኢየሱስ ይህንን ያደረገው ተቀብቶ ንጉሥ ለመሆን ከታጨ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ነበር። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ከሆነ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ከይሖዋ ጋር ሆኖ ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ሲመጣ፣ የአምላክ ሕዝቦች መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት አይሁዳውያንን እንዲያዘጋጅ ተልኮ ነበር። በዘመናችንም ይሖዋ ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ከመምጣቱ በፊት መንገዱን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛ ተልኳል። በ1880ዎቹ ዓመታት የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን በርካታ መሠረታዊ እውነቶች ቅን ለሆኑ ግለሰቦች ማስተማር ጀምረው ነበር።

3:10—“ዐሥራቱን ሁሉ” እንዲያስገቡ የተሰጠው መመሪያ ያለንን ሁሉ ለይሖዋ መስጠትን ያመለክታል? የኢየሱስ መሞት የሙሴ ሕግ እንዲቀር ስላደረገ አምላክ በዛሬው ጊዜ የገንዘብ ዐሥራት እንድንሰጥ አይጠብቅብንም። ያም ሆኖ ዐሥራት ምሳሌያዊ ትርጉም አለው። (ኤፌሶን 2:15) ዐሥራት ያለንን ሁሉ ለይሖዋ መስጠትን አያመለክትም። እስራኤላውያን ዐሥራት የሚያስገቡት በየዓመቱ ሲሆን እኛ ግን ሁለንተናችንን ለይሖዋ የሰጠነው አንድ ጊዜ ነው፤ ይህም የሆነው ራሳችንን ለእሱ ወስነን በውኃ ስንጠመቅ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለን ነገር ሁሉ የይሖዋ ነው። እንደዚያም ሆኖ ካለን ነገር የተወሰነውን ለእሱ አገልግሎት በማዋል በምሳሌያዊ ሁኔታ ዐሥራት እንድናስገባ ፈቅዶልናል። ይህም ሁኔታችን እንደፈቀደልንና ልባችን እንዳነሳሳን የምንሰጠው ነገር ነው። ለይሖዋ የምናቀርበው መሥዋዕት ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ጥሪታችንን መጠቀምን ይጨምራል። ከዚህም በላይ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ የታመሙና በዕድሜ የገፉ የእምነት ባልንጀሮቻንን መጠየቅን እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ በገንዘብ መደገፍንም ያጠቃልላል።

4:3—የይሖዋ አምላኪዎች ‘ክፉዎችን የሚረግጡት’ በምን መንገድ ነው? በምድር ላይ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ቃል በቃል ‘ክፉዎችን አይረግጡም’ ወይም በእነሱ ላይ የፍርድ እርምጃ አይወስዱም። ከዚህ ይልቅ ይህ አባባል፣ በምድር ላይ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች የሰይጣን ዓለም ከጠፋ በኋላ በሚኖረው የድል በዓል ላይ ሙሉ በሙሉ በመካፈል በምሳሌያዊ ሁኔታ ክፉዎችን እንደሚረግጡ ያሳያል።—መዝሙር 145:20፤ ራእይ 20:1-3

4:4—‘የሙሴን ሕግ ማሰብ’ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ እንዲያከብሩ ባይጠበቅባቸውም ሕጉ “ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” ሆኖ አገልግሏል። (ዕብራውያን 10:1) በመሆኑም ለሙሴ ሕግ ትኩረት መስጠታችን በሕጉ ውስጥ የሰፈሩት ነገሮች እንዴት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ለማስተዋል ሊረዳን ይችላል። (ሉቃስ 24:44, 45) ከዚህም በላይ “የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት . . . ነገሮች” በሕጉ ውስጥ ተካትተዋል። ስለ ክርስቲያናዊ ትምህርትና አኗኗር ለመረዳት ከፈለግን ሕጉን ማጥናታችን አስፈላጊ ነው።—ዕብራውያን 9:23

4:5, 6—“ነቢዩ ኤልያስ” ማንን ያመለክታል? “ኤልያስ” የሕዝቡን ልብ በማዘጋጀት የተሃድሶ ሥራ እንደሚያከናውን አስቀድሞ ተነግሯል። ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ “ኤልያስ” መጥምቁ ዮሐንስን እንደሚያመለክት ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 11:12-14፤ ማርቆስ 9:11-13) ዘመናዊው ኤልያስም ‘ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት’ ተልኳል። በዛሬው ጊዜ ኤልያስ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ ሌላ ማንንም ሊያመለክት አይችልም። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ይህ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን፣ ሰዎች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያስተካክሉ ለመርዳት በትጋት እየሠራ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

3:10 ለይሖዋ ምርጣችንን አለመስጠት የእሱን በረከት እንድናጣ ያደርገናል።

3:14, 15 የካህናቱ መጥፎ ምሳሌነት አይሁዳውያኑ ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት አቅልለው መመልከት እንዲጀምሩ አድርጓቸው ነበር። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችም ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:1-3

3:16 ይሖዋ እሱን ለሚፈሩት ታማኝ አገልጋዮቹ የመታሰቢያ መጽሐፍ ያጽፋል። የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ሲያጠፋ እነዚህን አገልጋዮቹን በማስታወስ ከጥፋት ይጠብቃቸዋል። እንግዲያው ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ እንጽና።—ምሳሌ 20:7

4:1 ለይሖዋ መልስ በምንሰጥበት ዕለት “ቅርንጫፍ” እና “ሥር” ተመሳሳይ ዕጣ ይኖራቸዋል፤ ይህም ልጆች የወላጆቻቸው ዓይነት ፍርድ እንደሚሰጣቸው ያመለክታል። ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸውን በተመለከተ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ክርስቲያን አባቶችና እናቶች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት እንዲሁም በእሱ ዘንድ ጥሩ አቋም ይዘው ለመኖር ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:14

‘አምላክን ፍራ’

‘ከታላቁና ከሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ ማን ሊድን ይችላል? (ሚልክያስ 4:5) ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሐይ በክንፎቿ ፈውስ ይዛ ትወጣለች፤ እናንተም ከጋጥ እንደ ተለቀቀ እንቦሳ እየቦረቃችሁ ትወጣላችሁ።”—ሚልክያስ 4:2

“የጽድቅ ፀሐይ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ስም አክብሮታዊ ፍርሃት ላላቸው ሰዎች እንደ ፀሐይ ሲያበራላቸው የይሖዋን ሞገስ ያገኛሉ። (ዮሐንስ 8:12) ከዚህም በላይ እነዚህ ሰዎች ‘በክንፎቹ ፈውስ’ ያገኛሉ፤ ይኸውም በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ፈውስ በአምላክ አዲስ ዓለም ደግሞ አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ፈውስ ያገኛሉ። (ራእይ 22:1, 2) በደስታ ተውጠው እንደ ደለቡ ‘እንቦሳዎች’ ይቦርቃሉ። እንዲህ ዓይነት በረከት ከፊታችን ስለሚጠብቀን ንጉሥ ሰሎሞን የተናገረውን የሚከተለውን ምክር ልብ እንበል:- “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።”—መክብብ 12:13

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀናተኛና ለአምላክ ያደረ አገልጋይ የነበረው ነቢዩ ሚልክያስ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምናስተምረው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ አገልጋዮች የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ያከብራሉ