በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓሣ ነባሪዎቹ መጡ!

ዓሣ ነባሪዎቹ መጡ!

በየዓመቱ ሐምሌ ወር ላይ ሳውዘርን ራይት ዌልስ (Eubalaena australis) ተብለው የሚጠሩት እንስት ዓሣ ነባሪዎች በብራዚል ወደሚገኘው ሳንታ ካተሪና ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ይመጣሉ። እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች የሚመጡት በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከሚገኘው የአንታርክቲክ ሰሜናዊ ክልል ሲሆን የሚመጡትም ውኃው እምብዛም ጥልቅ ባልሆነበት አካባቢ ለመውለድና ግልገሎቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ነው። ለበርካታ ወራት፣ በባሕሩ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችና ጎብኚዎች ዓሣ ነባሪዎቹ ከግልገሎቻቸው ጋር እረፍት ሲያደርጉና ሲቦርቁ በመመልከት ይዝናናሉ! *

አስገራሚ ትርዒት የሚያሳዩ ግዙፍ የባሕር ፍጥረታት

እንስቷ ዓሣ ነባሪ 16 ሜትር ርዝመት ያላት ሲሆን ይህም ከአንድ ረጅም (ተጣጣፊ) አውቶቡስ ጋር የሚመጣጠን ነው፤ ክብደቷ ደግሞ 80 ቶን ሊደርስ ይችላል! አብዛኞቹ ዓሣ ነባሪዎች ጥቁር ቀለም ያላቸው ቢሆንም አንዳንዴ ሆዳቸው አካባቢ ነጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ጭንቅላታቸው በጣም ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ የአካላቸውን አንድ አራተኛ ያክላል። አፋቸው ረጅም ሲሆን ግማሽ ክብ ቅርጽ አለው። እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች እንደ ሌሎቹ የዓሣ ነባሪ ዝርያዎች ጀርባቸው አካባቢ ክንፍ የላቸውም። ወደፊት ለመዋኘት ሰፊና የV ቅርጽ ያለውን ጅራታቸውን እንደ ሌሎች ዓሣዎች ወደ ቀኝና ወደ ግራ ከማወዛወዝ ይልቅ ወደ ላይና ወደ ታች እጥፍ ዘርጋ ያደርጋሉ። አቅጣጫ ለመቀየር ደግሞ መቅዘፊያቸውን ይጠቀማሉ። ይህም አውሮፕላን ከሚበርበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው።

እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች በጣም ግዙፍ ቢሆኑም እንኳ አካላቸው እንደ ልብ ስለሚታዘዝላቸው አስገራሚ ትርዒቶች ያሳያሉ። ጅራታቸውን ለረጅም ጊዜ ከውኃ አውጥተው ይንሳፈፋሉ። ጅራታቸውን ወደ ላይ እያነሱ ውኃውን በኃይል ይመታሉ። እንዲሁም ከውኃው ተስፈንጥረው ከወጡ በኋላ ተመልሰው በማረፍ ውኃውን በጣም ያንቦራጭቁታል፤ ይህን ትርዒት ከርቀትም ሆኖ ማየት ይቻላል።

ለየት ያለ አካላዊ ገጽታ

እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች ጭንቅላታቸው ላይና ጭንቅላታቸው አካባቢ ነጭ ወይም ቢጫ ቀለም ያላቸው የደደሩ ነገሮች አሏቸው፤ ይህ ሻካራ የሆነ የቆዳ ክፍል ‘የዓሣ ነባሪ ቅማል’ በመባል በሚታወቁ ትናንሽ የሸርጣን ዝርያዎች የተሸፈነ ነው። የብራዚል ራይት ዌል ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው ካሪና ግሮሽ እንዲህ ብላለች፦ “በእያንዳንዱ ዓሣ ነባሪ ላይ ያለው ሻካራ ቆዳ ንድፍ እንደ ሰው አሻራ የተለያየ ነው። ይህም አንዱን ዓሣ ነባሪ ከሌላው ለመለየት ያስችላል። ዓሣ ነባሪዎቹ ወደ ባሕር ዳርቻው ሲመጡ ቆዳቸው ላይ ያለውን ንድፍ ፎቶግራፍ አንስተን መዝገባችን ውስጥ እናስቀምጠዋለን።”

ይህ የዓሣ ነባሪ ዝርያ ጥርስ ስለሌለው ሲሞት ትክክለኛ ዕድሜውን ማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ይሁንና በአማካይ ቢያንስ 65 ዓመት እንደሚኖር ይገመታል። *

አስገራሚ የአመጋገብ ልማድ

ይህ ዓሣ ነባሪ የሚመገበው እንደ ሸርጣን ያሉ ትናንሽ ፍጥረታትን ነው። ዓሣ ነባሪው የላይኛው መንጋጋው ላይ ቀጫጭን ፀጉር ያላቸውና ለማጣራት የሚያገለግሉ ቤሊን ፕሌት በመባል የሚታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካል ክፍሎች አሉት። ዓሣ ነባሪው አፉን ከፍቶ ሲዋኝ እነዚህ የአካል ክፍሎች ውኃውን እያሳለፉ ትናንሽ የባሕር ፍጥረታትን ያስቀራሉ። በዚህ መንገድ እያንዳንዱ ዓሣ ነባሪ በአንድ ቀን እስከ ሁለት ቶን የሚደርሱ የሸርጣን ዝርያዎችን ይመገባል።

እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች በበጋ ወራት (ጥር/የካቲት) አንታርክቲክ ውቅያኖስ ውስጥ በመመገብ ስብ ያከማቻሉ። ይህ ወፍራም የስብ ሽፋን፣ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ የሚያሞቃቸው ከመሆኑም በላይ ወደ ሌላ ቦታ ሲፈልሱ የኃይል ምንጭ ሆኖ ያገለግላቸዋል።

ይታደኑ የነበረው ለምንድን ነው?

ከ18ኛው መቶ ዘመን ወዲህ አዳኞች በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙትን ዓሣ ነባሪዎች በብዛት ያድኑ ነበር። ምክንያቱም እነሱን ማደን በጣም ቀላል ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ቀስ ብለው ስለሚዋኙ፣ ብዙም ጥንካሬ በሌላቸው የእንጨት ጀልባዎች የሚጠቀሙና በእጃቸው ጦር የያዙ ሰዎች እንኳ በቀላሉ ሊያጠምዷቸው ይችላሉ። በተጨማሪም ከሌሎች ዓሣ ነባሪዎች በተለየ ብዙ ስብ ስላላቸው ሲሞቱ ይንሳፈፋሉ። በመሆኑም አዳኞች ወደ ባሕሩ ዳርቻ በቀላሉ ጎትተው ሊያወጧቸው ይችላሉ።

በተጨማሪም በወቅቱ የዓሣ ነባሪ ስብና ቤሊን በጣም ተፈላጊ ነገሮች ነበሩ። የዓሣ ነባሪ ስብ በዘይት ለሚሠሩ የመንገድ መብራቶች የሚያገለግል ከመሆኑም ሌላ እንደ ግራሶ ያገለግላል። ቤሊን የቦርጭ መሰብሰቢያ ኩርሲ፣ የፈረስ አለንጋ እንዲሁም የጃንጥላ መወጠሪያ ለመሥራት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። እንዲያውም ከአንድ ዓሣ ነባሪ ብቻ የሚገኘው ቤሊን ዓሣ ነባሪውን ለመያዝ የወጣውን ወጪ በሙሉ መሸፈን ይችል ነበር።

በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አደን በጣም በመፋፋሙ የዓሣ ነባሪዎቹ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ነበር፤ በኋላም ከዓሣ ነባሪ አደን የሚገኘው ትርፍ አዋጭ አልሆነም። ብራዚል ውስጥ የነበረው የመጨረሻው የአደን ጣቢያ በ1973 ተዘጋ። የአንዳንድ ዝርያዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ ቢሄድም አንዳንድ ዝርያዎች ግን አሁንም ከምድረ ገጽ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

ይህ የዓሣ ነባሪ ዝርያ፣ በምድር ላይ ያለው ብዝሃ ሕይወት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው። እንዲሁም ታላቁ ንድፍ አውጪ ይሖዋ አምላክ ያለውን ወደር የሌለው ጥበብና ኃይል ያሳያል።—መዝሙር 148:7

^ አን.2 ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች በአርጀንቲና፣ በአውስትራሊያ፣ በኡራጓይና በደቡብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻዎች እንዲሁም በኦክላንድ ደሴቶች ይዋለዳሉ።

^ አን.8 የሳይንስ ሊቃውንት ራይት ዌል የሚባሉት ዓሣ ነባሪዎች ሦስት ዝርያዎች እንዳሏቸው ይናገራሉ። በደቡብ ንፍቀ ክበብ ከሚገኘው ዝርያ (Eubalaena australis) በተጨማሪ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ሁለት ዝርያዎች (Eubalaena glacialis, Eubalaena japonica) ይገኛሉ።