በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓይነ ስውርነት

ዓይነ ስውርነት

“የዓይኔን ብርሃን ያጣሁት ገና እንደተወለድኩ ኃይለኛ የዓይን ጠብታ በተደረገልኝ ጊዜ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውር ሆንኩ፤ ከዚያም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ።” —ፓኪ፣ ባለቤቷም ዓይነ ስውር የሆነ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት።

ዓይነ ስውርነት ወይም ሥር የሰደደ የማየት እክል አደጋንና በሽታን ጨምሮ ብዙ መንስኤ ሊኖረው ይችላል። እነዚህ ችግሮች ዓይንን፣ የዓይን ነርቮችን ወይም አንጎልን ሊጎዱ ይችላሉ። በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ሁኔታውን መቀበል ይከብዳቸዋል፤ እንዲሁም በሐዘንና በፍርሃት ይዋጣሉ። ይሁንና ብዙዎች ችግሩን መቋቋምና አርኪ ሕይወት መምራት ችለዋል።

ዓይናችን በዙሪያችን ስላለው ዓለም መረጃ የምናገኝበት ዋነኛው መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው የዓይኑን ብርሃን ሲያጣ ሌሎች የስሜት ሕዋሳቱን ይኸውም የማዳመጥ፣ የማሽተት፣ የመዳሰስና የመቅመስ ችሎታዎቹን ይበልጥ ለመጠቀም ይገደዳል።

ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት በገለጸው መሠረት፣ በአንጎልና በነርቮች ላይ የተደረገው ምርምር አንጎላችን “አንድ ዓይነት ለውጥ ሲያጋጥመው በሂደት ራሱን ከሁኔታው ጋር እንደሚያስማማ” ያሳያል። መጽሔቱ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “አንጎላችን ከአንድ የስሜት ሕዋስ መረጃ ማግኘት ሲያቅተው ሌሎች የስሜት ሕዋሳትን ለመደገፍና መረጃ እንዲሰጡት ለማስተባበር ሲል ራሱን እንደ አዲስ የማደራጀት ችሎታ አለው።” እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።

ማዳመጥ፦ ከእግር ኮቴ አንስቶ እስከ ሰው ድምፅ ድረስ፣ የምንሰማው ማንኛውም ድምፅ በዓይነ ሕሊናችን አንድ ምስል እንድንስል ይረዳናል። ፈርናንዶ የተባለ ዓይነ ስውር “ሰዎችን በድምፃቸው ወይም በኮቴያቸው ብቻ መለየት እችላለሁ” በማለት ተናግሯል። ኹዋን የተባለ ሌላ ዓይነ ስውር ደግሞ “ዓይነ ስውራን ሰዎችን የሚለዩት በድምፃቸው ነው” ብሏል። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ዓይነ ስውራንም የተለያየ ዓይነት ስሜት ለማስተላለፍ የሚረዳውን የሰዎችን የድምፅ ቃና ያስተውላሉ።

በሚገባ የሠለጠነ ጆሮ ያለው አንድ ዓይነ ስውር ከሚሰማቸው ድምፆች በመነሳት ስለ አካባቢው፣ ለምሳሌ መኪና እየመጣ ስላለበት አቅጣጫ፣ ስለ አንድ ክፍል ስፋት እንዲሁም ሊያደናቅፉት የሚችሉ ነገሮች ስላሉበት ቦታ ብዙ መረጃ ማግኘት ይችላል።

ማሽተት፦ አንድ ዓይነ ስውር በዚህ የስሜት ሕዋስ አማካኝነት የአንድን ነገር ሽታ ከማወቅ ባለፈ ብዙ መረጃ ማግኘት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በመንገድ ላይ እየሄደ ሳለ የማሽተት ችሎታው እንደ ሻይ ቤት፣ ምግብ ቤት፣ የገበያ ስፍራና እነዚህን የመሳሰሉ ቦታዎች የት እንደሚገኙ በዓይነ ሕሊናው መሳል እንዲችል ይረዳዋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የተለመዱ ድምፆችም ከሽታው ጋር ተዳምረው መረጃውን ያጠናክሩለታል፤ ከመዳሰስ ችሎታም ጋር በተያያዘ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

መዳሰስ፦ ፍራንሲስኮ “ጣቶቼ ዓይኖቼ ናቸው” በማለት ተናግሯል። ዱላ መጠቀም የእነዚህን “ዓይኖች” “የማየት” ችሎታ ይጨምረዋል። ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረውና ከልጅነቱ ጀምሮ ዱላ ሲጠቀም የኖረው ማናሴስ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች የስሜት ሕዋሳቴን፣ የማስታወስ ችሎታዬን እንዲሁም የመንገዱን ዓይነት የሚነግረኝን ዱላዬን በመጠቀም ያለሁበትን ቦታ በእርግጠኝነት ማወቅ እችላለሁ።”

በብሬይል የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ማንበብ

የመዳሰስ ችሎታ በርካታ ዓይነ ስውራን በብሬይል የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማንበብ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በአሁኑ ጊዜ አንድ ዓይነ ስውር አእምሮውንም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወቱን ሊያጎለብቱለት የሚችሉ የተለያዩ አጋዥ መሣሪያዎችን ማግኘት ይችላል። በብሬይል ከተዘጋጁ ጽሑፎች በተጨማሪ በድምፅ የተቀዱ ነገሮችና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉ። ዓይነ ስውራን በእነዚህ መሣሪያዎች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስንና የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ይችላሉ። *

እነዚህ ዝግጅቶች ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፓኪና ባለቤቷ ወደር የሌለው መጽናኛና ተስፋ እንዲያገኙ ረድተዋቸዋል። ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ የሆነው፣ በአካባቢው የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ጉባኤም ድጋፍ አልተለያቸውም። ፓኪ “አሁን በተወሰነ መጠንም ቢሆን የሌሎች እርዳታ ሳያስፈልገን ጥሩ ኑሮ እየመራን ነው” ብላለች።

እርግጥ ነው፣ ዓይነ ስውርነት የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት። እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች ተጋፍጠው ከሕይወት የሚገኘውን ደስታ እያጣጣሙ ያሉ ሰዎች መኖራቸው፣ የሰው ልጅ ምን ያህል ከሁኔታዎች ጋር የመላመድና ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ እንዳለው ያሳያል!

^ አን.10 የይሖዋ ምሥክሮች ከ25 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በብሬይል ያዘጋጃሉ።