በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ወባ በሽታ ማወቅ ያለብህ ነገር

ስለ ወባ በሽታ ማወቅ ያለብህ ነገር

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ግምታዊ መረጃ መሠረት በ2013 ከ198 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን 584,000 የሚያህሉ ሰዎች በወባ በሽታ ሞተዋል። በበሽታው ከሞቱት መካከል አራት አምስተኛ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው። ይህ በሽታ ወደ መቶ በሚጠጉ አገሮችና ክልሎች በሚኖሩ 3.2 ቢሊዮን ሰዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል።

1 ወባ ምንድን ነው?

ወባ በጥገኛ ተሕዋስያን ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማላብ፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት መጓጎል፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹ ከ48 እስከ 72 ሰዓት እየቆዩ በድጋሚ ይታያሉ፤ ይህን የሚወስነው ግለሰቡን ያጠቁት ተሕዋስያን ዓይነትና በበሽታው ተይዞ የቆየበት ጊዜ ነው።

2 ወባ የሚተላለፈው እንዴት ነው?

  1. የወባ ተሕዋስያን፣ ፕላዝሞዲያ ተብለው የሚጠሩ ባለ አንድ ሴል ፍጥረታት ሲሆኑ ወደ ሰው ደም ውስጥ የሚገቡት አኖፊሊስ በምትባለው ሴት ትንኝ ንክሻ አማካኝነት ነው።

  2. ተሕዋስያኑ የግለሰቡ ጉበት ሴሎች ውስጥ በመግባት ይራባሉ።

  3. በጉበቱ ውስጥ ያሉት ሴሎች ሲፈነዱ ተሕዋስያኑ ይወጡና የግለሰቡን ቀይ የደም ሴሎች ይወርራሉ። ከዚያም ተሕዋስያኑ በቀይ የደም ሴሎቹ ውስጥ መባዛታቸውን ይቀጥላሉ።

  4. ቀይ የደም ሴሎቹ በሚፈነዱበት ጊዜ ተሕዋስያኑ ይወጡና ሌሎች ቀይ የደም ሴሎችን ይወርራሉ።

  5. በቀይ የደም ሴሎቹ ውስጥ የሚካሄደው ይህ ዑደት ይቀጥላል። ቀይ የደም ሴሎቹ በፈነዱ ቁጥር በበሽታው የተያዘው ሰው የወባ በሽታ ምልክቶቹ ይታዩበታል።

3 ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ወባ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት አካባቢ የምትኖር ከሆነ . . .

  • አጎበር ተጠቀም። አጎበሩ

    • የተባይ ማጥፊያ የተረጨበት

    • ምንም ቀዳዳ የሌለው

    • በፍራሹ ዙሪያ የተጠቀጠቀ መሆን አለበት።

  • ቤት ውስጥ የሚረጭ የተባይ ማጥፊያ ተጠቀም

  • የሚቻል ከሆነ በበሮቹና በመስኮቶቹ ላይ እንደ ወንፊት ያለ መከለያ አድርግ፤ እንዲሁም ትንኞች እንዳያርፉ ሊከላከሉ ስለሚችሉ እንደ አየር ማቀዝቀዣ ያሉ መሣሪያዎችን ተጠቀም።

  • ሰውነትህን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ነጣ ያለ ቀለም ያለው ልብስ ልበስ።

  • የሚቻል ከሆነ የወባ ትንኞች በብዛት ከሚገኙበት ጥሻ የሆነ አካባቢና ለትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ የታቆሩ ውኃዎች ካሉበት ቦታ ራቅ።

  • በወባ ከተያዝክ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ።

ወባ በተደጋጋሚ ወደሚከሰትበት ቦታ ለመሄድ የምታስብ ከሆነ . . .

  • ጉዞ ከመጀመርህ በፊት ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ሞክር። በአንድ አካባቢ ያለው የወባ ዓይነት በሌላ ቦታ ካለው ሊለይ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ውጤታማ የሆነው መድኃኒት የትኛው እንደሆነ ለመወሰን ይረዳሃል። በተጨማሪም ከጤንነትህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ መረጃዎችን ለማግኘት ሐኪምህን ማነጋገርህ ጠቃሚ ነው።

  • እዚያ በምትቆይበት ወቅት፣ ወባ በሚከሰትበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚናገሩትን በዚህ ርዕስ ላይ የቀረቡ ምክሮች ተግባራዊ አድርግ።

  • በበሽታው ከተያዝክ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ሞክር። የበሽታው ምልክቶች የሚታዩት ተሕዋስያኑ ወደ ሰውነትህ ከገቡ ከአንድ እስከ አራት በሚሆኑ ሳምንታት ውስጥ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብሃል።