በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

ጓደኝነት ገደቡን ሲያልፍ

ጓደኝነት ገደቡን ሲያልፍ

ተፈታታኙ ነገር

ስሜትሽን በደንብ የሚረዳልሽ ጓደኛ አለሽ። * ከእሱ ጋር ማንኛውንም ነገር ማውራት ትችያለሽ፤ ደግሞም ታወራላችሁ። ‘ከጓደኝነት ያለፈ ምንም ነገር የለንም’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል፤ ይሁንና የትዳር ጓደኛሽ፣ ከዚህ ሰው ጋር ረዘም ላለ ጊዜ እንደምታወሩ ቢያውቅ ጓደኝነታችሁ ከልክ እንዳለፈ ሊሰማው ይችላል።

ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ወዳጅነታችሁ ገደቡን አልፏል፤ በመሆኑም ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልግሻል። እስቲ በመጀመሪያ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ጓደኝነት ለመመሥረት ምክንያት የሆነሽ ምን ሊሆን እንደሚችል እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

ጥሩ ስሜት ይፈጥራል። ነገሩን በአጭሩ ለማስቀመጥ፣ ተቃራኒ ፆታ ያለውን ሰው ትኩረት ማግኘት ደስ ይላል። ተፈላጊ እንደሆንን ማወቅ ልዩ ስሜት የሚፈጥርብን ሲሆን ተወዳጅ እንደሆንን እንዲሰማን ያደርጋል። በትዳር ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ከቆየሽ በኋላ፣ ተቃራኒ ፆታ ካለው ጓደኛሽ ጋር ማውራትሽ ስለ ራስሽ ጥሩ እንዲሰማሽ እንደሚያደርግሽ ማሰብ ጀምረሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልታውቂው የሚገባ ነገር አለ፤ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት እንዲያሟላልሽ የትዳር ጓደኛሽ ወዳልሆነ ሰው መሄድ ጣጣ አለው። ከሌላ ወንድ ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ ስትፈጥሪ ከባለቤትሽ ጋር ያለሽ ቅርበት እየቀነሰ ይሄዳል። በሌላ አባባል ለባለቤትሽ ልትሰጪው የሚገባውን ፍቅር እየነፈግሽው ነው ማለት ነው።

• ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦ ‘በትዳሬ ውስጥ ላገኝ የሚገባኝ፣ ሆኖም የትዳር ጓደኛዬ ያልሆነ ሰው እንዲያሟላልኝ እየፈለግሁ ያለሁት ነገር አለ?’

በትዳር ውስጥ ችግር መኖሩ። የሚያገቡ ሰዎች “መከራ” እንደሚደርስባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ለምሳሌ ያህል፣ የትዳር ጓደኛሽ ችላ እንዳለሽ ወይም እንደማያደንቅሽ የሚሰማሽ ጊዜ ይኖራል፤ ወይም በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ባለመቻላችሁ ቅሬታ ሊኖርሽ ይችላል። ምናልባትም የትዳር ጓደኛሽ ስለ እነዚህ ጉዳዮች አለማውራትን ይመርጥ ይሆናል፤ ይህም ስለሚያበሳጭሽ ትኩረት ለማግኘት ስትዪ ወደ ሌላ ሰው ለመሄድ ትፈተኚ ይሆናል። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከባድ ጉዳዮችን አንስቶ ለመወያየት ፈቃደኛ አለመሆን የትዳር ጓደኛሞች ደስተኛ እንዳይሆኑ ሊያደርግ አልፎ ተርፎም ወደ ፍቺ ሊመራ ይችላል።

• ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦ ‘ተገቢ ያልሆነ ወዳጅነት እንድመሠርት ያደረገኝ በትዳሬ ውስጥ የተፈጠረ ችግር አለ?’

 ምን ማድረግ ይቻላል?

አደጋ እንዳለው እወቂ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?” ይላል። (ምሳሌ 6:27) እውነቱን ለመናገር፣ ትዳር እያለሽ ለሌላ ሰው የፍቅር ስሜት ማዳበር በጣም ጎጂ ነው። (ያዕቆብ 1:14, 15) ሊያሳስብሽ የሚገባው፣ ገና ለገና ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ብቻ አይደለም። አሁንም እያደረስሽ ያለውን ጉዳት አስቢ። የትዳር ጓደኛሽ ላልሆነ ሰው እንዲህ ዓይነት ትኩረት ስትሰጪ ባለቤትሽ ከአንቺ ሊያገኝ የሚገባውን ትኩረት እየነፈግሽው ነው።

ራስሽን አታታልዪ። የትዳር ጓደኛሽ ካልሆነ ሰው ጋር የቀረበ ጓደኝነት ካለሽ ይህን ሰው አግብተሽው ቢሆን ኖሮ ሕይወትሽ ምን ሊመስል ይችል እንደነበረ ማሰብ ልትጀምሪ ትችያለሽ። ይሁንና ይህን ስታደርጊ የጓደኛሽን ጠንካራ ጎን ከባለቤትሽ ድክመት ጋር እያወዳደርሽ ነው፤ ይህ ደግሞ ሁኔታውን በትክክል እንድትመዝኚ አያደርግሽም! ሌላው ልትዘነጊው የማይገባ ነገር ደግሞ አሁን ስለ ጓደኛሽ የሚሰማሽ ስሜት ቀደም ሲል ለባለቤትሽ ይሰማሽ የነበረው ዓይነት መሆኑን ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ኤርምያስ 17:9

ገደብ አብጂ። ሰዎች ሌባን ለመከላከል ሲሉ በተሽከርካሪያቸው ወይም በቤታቸው ውስጥ የማንቂያ ድምፅ የሚያሰማ ደወል ያስገጥማሉ። አንቺም ከትዳርሽ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ትችያለሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብህን ጠብቅ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 4:23) ይህን ማድረግ የምትችዪው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሪ፦

  • የትዳር ጓደኛ እንዳለሽ ግልጽ አድርጊ፤ ለምሳሌ የትዳር ጓደኛሽን ፎቶግራፍ በሥራ ቦታሽ ልታስቀምጪ ትችያለሽ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ዘፍጥረት 2:24

  • ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባለሽ ግንኙነት ረገድ ተገቢ የሆነውንና ተገቢ የማይሆነውን ምግባር አስቀድመሽ ወስኚ። ለምሳሌ ያህል፣ በትዳርሽ ስላጋጠሙሽ ችግሮች ጓደኛዬ ለምትዪው ሰው መንገር ወይም ተቃራኒ ፆታ ካለው የሥራ ባልደረባሽ ጋር ለመዝናናት ወጣ ማለት ጨርሶ ተገቢ አይሆንም።

  • ከአንድ ወንድ ጋር በጣም ተቀራርበሽ ከሆነ ጓደኝነትሽን ልታቋርጪ ይገባል። ይህን ማድረግ ከከበደሽ እንዲህ የሚሰማሽ ለምን እንደሆነ ራስሽን ጠይቂ። ከዚህ ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረትሽ ምንም ስህተት እንደሌለው ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ የትዳር ጓደኛሽን ፍላጎት ለማስቀደምና ትዳርሽን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች ውሰጂ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 5:18, 19

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የቀረቡት ከሚስት አንጻር ቢሆንም መመሪያዎቹ ለባሎችም ይሠራሉ።