በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዓለም

ከናፍጣ መኪኖች የሚወጣን ጭስ መተንፈስ “በሳንባ ካንሰር የመያዝ አጋጣሚን [እንደሚጨምር]” እንዲሁም ለፊኛ ካንሰር ሊያጋልጥ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል።

አንታርክቲካ

በአንታርክቲክ ክልል ከባሕር ሥር ባለ መሬት ውስጥ የተቀበሩ የአበባ ብናኞችና ዘሮች መገኘታቸው በአንድ ወቅት በዚህ ቦታ በሞቃታማ አካባቢ የሚበቅሉ እንደ ዘንባባ ያሉ ዛፎች እንደነበሩ አረጋግጧል። “ኢዮሲን ግሪንሃውስ ፒሬድ” ተብሎ በሚጠራው ዘመን ክረምቱ የማይከብድና “በረዶ የማይጥልበት” ነበር፤ በተጨማሪም በዋልታዎች አካባቢ የነበረው የአየር ሁኔታ ከምድር ወገብ ብዙም የተለየ አልነበረም።

አየርላንድ

የአየርላንድ ካቶሊክ ቀሳውስት ማኅበር በ2012 ያወጣው ሪፖርት እንደጠቆመው ጥናት ከተካሄደባቸው በአገሪቱ የሚኖሩ ካቶሊኮች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት፣ ቀሳውስት ሚስት ማግባት ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ ያምናሉ፤ 77 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች የቅስና ሥልጣን ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይሰማቸዋል።

ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮችና ደቡብ ምሥራቅ እስያ

በወባ መድኃኒቶች ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚሰራጩት መድኃኒቶች በአብዛኛው የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው፤ አሊያም የውሸት ናቸው። ይህ ደግሞ የሚሰጠው ሕክምና ውጤታማ እንዳይሆን አስተዋጽኦ አድርጓል። ለሙከራ ጥናት ከተደረገባቸው መድኃኒቶች መካከል በደቡብ ምሥራቅ እስያ 36 በመቶ የሚሆኑት እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ 20 በመቶ የሚሆኑት የውሸት እንደሆኑ ተረጋግጧል።

ኤል ሳልቫዶር

በ2012 የሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ የኤል ሳልቫዶር ባለሥልጣናት በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ግድያ ሳይፈጸም የዋለበት ቀን እንደነበር አስታውቀዋል። በአደገኛ ዕፆች ምክንያት በሚፈጸሙ ዓመፆች በምትታመሰው በኤል ሳልቫዶር ውስጥ በ2011፣ ከ100,000 ሰዎች መካከል በ69ኙ ላይ ግድያ ተፈጽሟል፤ ይህም ኤል ሳልቫዶርን ከፍተኛ ግድያ ከሚፈጸምባቸው አገሮች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል።