በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራን ማስቀረት ያልቻለው የቴሬዚን ግንብ

መከራን ማስቀረት ያልቻለው የቴሬዚን ግንብ

መከራን ማስቀረት ያልቻለው የቴሬዚን ግንብ

ድሬዝደንና ፕራግ በተባሉት ሁለት የማዕከላዊ አውሮፓ ከተሞች መካከል የቴሬዝየንሽታት (ወይም ቴሬዚን) ከተማ ትገኛለች። ከተማዋ ትልቅ ግንብ ያላት ሲሆን በግንቡ ዙሪያ ደግሞ ጠላትን ለመመከት እንደ ምሽግ የሚያገለግል ሌላ ሰፊ ቅጥር አለ። ትልቁ ግንብ የተሠራው ወራሪ ሠራዊቶች ወደ አገሪቱ ዘልቀው እንዳይገቡ ለማገድና በዙሪያው ባሉ ክልሎች የሚኖሩ ሕዝቦች ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ ተብሎ ነበር።

ግንቡ እንዲሠራ ያዘዘው የጀርመን ንጉሥና የቅድስቷ ሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረው ዳግማዊ ጆሴፍ ሲሆን ስፍራው ለግንባታ ሲቀየስም ሆነ በ1780 ማለቂያ አካባቢ የመሠረት ድንጋዩ ሲጣል በቦታው ተገኝቶ ነበር። ግንቡ የተሠራው ለእናቱ ለእቴጌ መሪያ ተሬዛ መታሰቢያ እንዲሆን ስለነበር በቼክ ቋንቋ “የተሬዛ ከተማ” የሚል ትርጉም ያለው ቴሬዚን የሚል ስያሜ ተሰጠው። * አንዳንድ ጊዜ እስከ 14,000 የሚደርሱ ሠራተኞች በግንባታው ይካፈሉ እንደነበር ይነገራል። አብዛኛው ሥራ በአራት ዓመት ውስጥ ተጠናቀቀ።

ቴሬዚን በ1784 ሲጠናቀቅ በሃፕስበርግ ግዛት ውስጥ ጠላትን ለመመከት የሚያገለግል ትልቁ ግንብ ሆነ። ግንቡን ለመሥራት ያገለገለው የምሕንድስና ዘዴ እስከዚያ ዘመን ድረስ ግንብ ከሚሠራባቸው ዘዴዎች ጋር ሲነጻጸር እጅግ የመጠቀ ነበር። ይሁን እንጂ ግንቡ ተሠርቶ ከመጠናቀቁ በፊት በወታደራዊ የጦር ስልቶች ረገድ ጉልህ ለውጥ ታይቶ ነበር።

የጠላት ኃይሎች አንድ አገርን ሲወርሩ እንደ ቀድሞው በተመሸጉ ከተሞች ላይ ከበባ ማድረጋቸውን ትተው ነበር። ከዚህ ይልቅ በአካባቢው የሚገኙትን መንደሮች በመክበብ ይዘርፏቸው ነበር። በዚህም የተነሳ በ1888 ቴሬዚን ጠላትን ለመመከት የሚያገለግል ግንብ መሆኑ ቀረ። ከቴሬዚን ግንብ ውጭ ያለው እንደ ምሽግ የሚያገለግለው ሰፊ ቅጥርም የሚያማምሩ መናፈሻዎች የተሠሩበት ሲሆን መተላለፊያ መንገዶችና አግዳሚ ወንበሮች ነበሩት።

ግንቡና ከተማዋ

የቴሬዚን ግንብ የተሠራው የተመሸገ ከተማ እንዲሆን ታስቦ ነበር። ሰፊ ከሆነው ቅጥር በስተጀርባ ለወታደሮች፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለሌሎች ሰዎችም የሚሆኑ ቤቶች ተሠርተው ነበር።

ከዋናው ግንብ ቀጥሎ ወታደራዊ እስር ቤት ሆኖ የሚያገለግል አነስ ያለ ግንብ ተሠርቶ ነበር። በ1800ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሃፕስበርግ አገዛዝ ተቃዋሚ የነበሩ ፖለቲከኞች የሚታሠሩት በዚያ ነበር። ከመቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ በ1914 በሳረዬቮ አልጋ ወራሹን ፍራንሲስ ፈርዲናንድን በመግደል ወንጀል የተካፈሉት ወጣቶች በዚያ ወኅኒ ቤት ተጣሉ። እነዚህ ወጣቶች ከሞት ቅጣት ያመለጡት ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች በመሆኑ ነው። ብዙም ሳይቆይ ግን ከመካከላቸው አብዛኞቹ በእስር ቤት ሞቱ። በወኅኒ ቤት እያሉ ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰባቸው ሲሆን አንዳንዶቹም የአእምሮ ሕመምተኞች ሆነዋል። ግድያውን የፈጸመው ጋቭሪሎ ፕሪንሲፕም አንደኛው የዓለም ጦርነት በተጧጧፈበት ወቅት በዚያው እስር ቤት ሕይወቱ አለፈ።

ትንሹ ግንብ በኦስትሪያና በሃንጋሪ ከነበሩት በጣም መጥፎ ወኅኒ ቤቶች አንዱ ነበር። ብዙውን ጊዜ እስረኞች በከባድ እግር ብረት ተጠፍረው ምድር ቤት ውስጥ በሚገኙ በጣም የሚቀዘቅዙና እርጥበት ያላቸው ጨለማ ክፍሎች ውስጥ ይቀመጡ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ በዚህ እስር ቤት ውስጥ ከዚህ የከፉ ዘግናኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል።

“የቴሬዚን ጠበል” ምን ነበር?

በአሁኑ ጊዜ ቼክ ሪፑብሊክ የሚባለውን ክፍል ናዚዎች ወርረው ከያዙት በኋላ በ1941 አይሁዶችን ወደ ዋናው ግንብ መውሰድ ጀመሩ። ናዚዎች የቴሬዝየንሽታትን ከተማ አይሁዳውያን ተገልለው የሚኖሩበት ቦታ እንድትሆን አደረጓት። ናዚዎች በአይሁዳውያንና አይሁዳውያን ባልሆኑት መካከል ግጭት እንዳይፈጠር አይሁዳውያኑ በዚህ መንገድ መገለል እንዳለባቸው ይናገሩ ነበር። ምንም እንኳ ናዚዎች፣ ቴሬዝየንሽታት ለአይሁዶች ብቻ ሕክምና የሚሰጥባት የጠበል ከተማ እንደሆነች አድርገው ቢናገሩም በድብቅ አይሁዳውያንን በሙሉ ለመፍጀት አቅደው ነበር።

ናዚዎች ከቴሬዝየንሽታትና ከሌሎችም ተመሳሳይ አካባቢዎች ቀስ በቀስ የሚያመጧቸውን አይሁዶች የሚገድሉባቸው ካምፖች ቀደም ብለው በምሥራቅ አውሮፓ አቋቁመው ነበር። * የእነዚህ ካምፖች መኖር ከ1930ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በሰፊው የታወቀ ቢሆንም ናዚዎች እነዚህ ካምፖች እርማት መስጫ ተቋማት ከመሆን ያለፈ ዓላማ እንደሌላቸው የሚገልጽ ፕሮፖጋንዳ ይነዙ ነበር። ይሁን እንጂ በካምፖቹ ውስጥ ስለነበረው ሁኔታ የሚገልጹ ወሬዎች እየተበራከቱ ሄዱ። በዚህም ምክንያት የናዚ ባለሥልጣናት የሚናፈሰው ወሬ ትክክል አለመሆኑን የሚገልጽ መረጃ እንዲያቀርቡ ጫና ተደረገባቸው። ስለዚህ ናዚዎች ስለ ጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መልስ ለመስጠት ዘዴ ቀየሱ። እንዴት?

በ1944 እና በ1945 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ እያለ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ወኪሎች ዋናውን ግንብ እንዲጎበኙና በዚያ ያለውን ሁኔታ ራሳቸው እንዲያጣሩ ናዚዎች ጋበዟቸው። ይሁን እንጂ ናዚዎች የቴሬዚን ግንብ የጠበል ከተማ ከመሆን ውጪ ሌላ ሚና እንደሌለው ለማሳመን ሲሉ ከተማዋን ለማሰማመር ብዙ ሥራዎችን አከናውነው ነበር።

የሕንፃዎቹ ቁጥሮች ደስ በሚሉ የጎዳና ስሞች ተተኩ። ባንክ፣ መዋዕለ ሕፃናት እንዲሁም ሱቆች ያሉ እንዲመስል ተደረገ። ሌላው ቀርቶ አይሁዳውያኑ ተገልለው በሚኖሩበት በዚህ አካባቢ ማዕከላዊ ቦታ ላይ ካፊቴሪያ ተከፈተ። መንገድ ዳር ያሉ ቤቶች ከውጭ በኩል ታደሱ፤ በማዕከላዊው መናፈሻ ውስጥ ዕፅዋት ተተከሉ። እንዲሁም እንደ መዝናኛ ቦታ የሚያገለግሉ ዳሶች የተጣሉ ሲሆን ሙዚቃና ውዝዋዜም ነበር።

ከዚያ በኋላ የቀይ መስቀል ተወካዮች አስጎብኚ ተመድቦላቸው ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ተጋበዙ። እንዲሁም ከአይሁድ “ራስ ገዝ አስተዳደር” ተወካዮች ጋር እንዲነጋገሩ ተፈቀደላቸው። ይሁን እንጂ ያነጋገሯቸው ሰዎች ከነዋሪዎቹ መካከል በጥንቃቄ የተመረጡና እንደተባሉት አድርገው መልስ እንዲሰጡላቸው ናዚዎች ያሠለጠኗቸው ነበሩ። የቀይ መስቀል ልዑካኑ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ከተማዋን የጎበኙ ሲሆን ናዚዎች እነሱን በማታለል ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ልዑካኑም ቴሬዝየንሽታት ለነዋሪዎቿ ጥሩ እንክብካቤ የሚደረግባት የአይሁድ ከተማ እንደሆነች የሚገልጽ የተሳሳተ ሪፖርት አቀረቡ። የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ልዑካን ከቴሬዝየንሽታት ከሄዱ በኋላ ግን በዚያ የሚኖሩት አይሁዳውያን መሠቃየታቸውና በረሃብ አለንጋ መገረፋቸው የቀጠለ ሲሆን ብዙዎች ለሞት ይዳረጉ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ ለማየት የታደሉት ጥቂቶች ነበሩ።

ትንሹ ግንብ

ናዚዎች ትንሹን ግንብም ቢሆን እንደ ወኅኒ ቤት ተጠቅመውበታል። በዚያ የነበረው ሁኔታ በማጎሪያ ካምፖች ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው። ትንሹ ግንብ፣ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች በጀርመን ግዛት ወደሚገኙ ትልልቅ ካምፖች ከመዛወራቸው በፊት የሚታሰሩበት ወኅኒ ቤት ነበር።

ከፕራግ፣ ከፒልዘንና ከሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የተወሰዱ ቢያንስ 20 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች በትንሹ ግንብ ውስጥ ታስረው ነበር። የፈጸሙት ወንጀል ምን ነበር? ናዚዎችን ለመደገፍ ፈቃደኞች አለመሆናቸውና በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋም መያዛቸው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራቸው ላይ እገዳ ቢጣልም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙትን ምሥራች ለሌሎች ማካፈላቸውን ቀጥለው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ሁሉ መከራ የደረሰባቸው፣ አንዳንዶቹም እስኪሞቱ ድረስ የተሠቃዩት ወይም የተገደሉት በእምነታቸው ምክንያት እንጂ የሠሩት ወንጀል ኖሮ አይደለም።

የምናገኘው ትምህርት

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።” (መዝሙር 146:3, 4) የቴሬዚን ግንብ ይህ ጥቅስ እውነት መሆኑን የሚያሳይ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 እቴጌዋ ከጊዜ በኋላ የፈረንሳይ ንግሥት የሆነችው የመሪ አንቶኔት እናትም ነበረች።

^ አን.12 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የነሐሴ 22, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-15 እና ሚያዝያ 8, 1989 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-20 ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የይሖዋ ምሥክሮች በትንሹ ግንብ

በቴሬዝየንሽታት ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ መጀመሪያ ምርመራ የተካሄደባቸው በፕራግ በሚገኘው የጌስታፖ ዋና መምሪያ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ከቴሬዝየንሽታት ተወስደው በጀርመን ወዳሉ ማጎሪያ ካምፖች ይላኩ ነበር። ታዲያ በእስር ቤት የነበረውን መጥፎ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ተገልሎ ለብቻ መታሠር የሚያስከትለውን ጫና ተቋቁመው ያሳለፉት እንዴት ነበር?

በቴሬዝየንሽታት ታስራ የነበረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንደሚከተለው በማለት ታስታውሳለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንዳልረሳ ስል ደጋግሜ አሰላስልባቸው ነበር። ተዛውሬ በተወሰድኩበት እስር ቤት ሁሉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ለማጣራት የምሞክር ሲሆን መኖራቸውን ካወቅሁ ደግሞ ከእነሱ ጋር ለመገናኘት እጥራለሁ። እግረ መንገዴንም ሁኔታዎች በፈቀዱልኝ መጠን ለሌሎች ለመስበክ ጥረት አደርግ ነበር።”

ይህች ሴት የተጠቀመችበት ዘዴ እንደረዳት ግልጽ ነው። በእስር ቤትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሳለፈችው ሕይወት ለአምላክ ታማኝ ሆና ኖራለች።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ውብ የነበረችውን ቴሬዚንን የሚያሳይ ቴምብር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዲስ የመጡ እስረኞች ወደ ካምፖቹ ይወሰዱ ነበር። ምልክቱ በጀርመንኛ “Arbeit Macht Frei” (ሥራ አርነት ያወጣል) ይላል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴሬዚን ግንብ ውስጥ ሴት እስረኞች የሚጠቀሙባቸው የጣውላ አልጋዎች

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ትንሹ ግንብ የሚያስገባው ዋና በር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Both photos: With courtesy of the Memorial Terezín