በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሞለስክ ዛጎል

የሞለስክ ዛጎል

ንድፍ አውጪ አለው?

የሞለስክ ዛጎል

ዛጎሎች ሲታዩ በቀላሉ የሚሰበሩ ይመስላሉ፤ ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ዛጎሎችን በቀላሉ መስበር አይቻልም። ኬነዝ ቬክዮ የተባሉ ኢንጅነር የልጅነት ጊዜያቸውን አስታውሰው ሲናገሩ “አንዳንዶቹን [ዛጎሎች] ለመስበር መዶሻ መጠቀም አስፈልጎኝ ነበር” ብለዋል። የዛጎል ጥንካሬ በተለይ በሞለስኮች * ዛጎል ላይ በግልጽ ይታያል።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የሞለስክ ዛጎል ውስጠኛ ክፍል (ኔከር ወይም የእንቁ እናት ይባላል) በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታዩ ቅርፊቶች አሉት፤ በእነዚህ ቅርፊቶች መካከል ያለው ክፍተት የሚለካው በናኖሜትር ሲሆን ይህም የአንድ ሜትር አንድ ቢልዮነኛ ማለት ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኘው የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም፣ የቁስ አካል ሳይንስና ምህንድስና ዲፓርትመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ክርስቲን ኦርቲስ “በናኖሜትር የሚለካ ስፋት ባለው በኔከር ላይ ያየነው ውስብስብ የሆነ አሠራር በጣም አስደናቂ ሲሆን [ለዛጎሉ] ጥንካሬ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የተሠራበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።

ሳይንስ ነክ ስለሆኑ ጉዳዮች የሚጽፉት ቻርልስ ፔቲት ኔከርን በአጉሊ መነጽር ከተመለከቱ በኋላ ቅርፊቶቹ “በአስገራሚ ሁኔታ ሥርዓታቸውን ጠብቀው የተደረደሩ” እንደሆኑ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “[ኔከር] መሃል ለመሃል ተቆርጦ በአጉሊ መነጽር ሲታይ ከጡብ የተሠራ ግድግዳ ይመስላል፤ ግድግዳው በሥርዓት በተነባበሩ ጠፍጣፋና ባለ ስድስት ማዕዘን ቅርጽ ባላቸው የካልሽየም ካርቦኔት ክሪስታሎች የተገነባ ነው። እነዚህን ክሪስታሎች እርስ በርስ ያያያዛቸው ባለ ዛጎል ዓሦቹ የሚያመነጩት በፕሮቲን የበለጸገ ሙጫ የሚመስል ነገር ነው።”

የሳይንስ ሊቃውንት ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አዳጋች የሆነውን የሞለስክ ዛጎል አሠራር በማጥናት ብዙ ነገሮችን መሥራት እንደሚቻል ያምናሉ። ከእነዚህም መካከል ይበልጥ ጠንካራ የሆኑና ጥይት የማያስገቡ የጦር ዕቃዎች፣ የመኪና ውጫዊ አካሎች እንዲሁም የአውሮፕላን ክንፎች ይገኙበታል። ኦርቲስ እንዲህ ብለዋል፦ “ተፈጥሮ በናኖሜትር የሚለካ ንድፍን በመጠቀም ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ውስብስብ ነገሮችን ይሠራል። አብዛኛውን ጊዜ ግን የሰው ልጆች እንዲህ ማድረግ አልቻሉም።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? አስደናቂ ጥንካሬ ያለው የሞለስክ ዛጎል እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ይመስልሃል? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ሞለስኮች፣ ለስላሳ ሰውነት ያላቸው አጥንት አልባ እንስሳት ናቸው። በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት ሞለስኮች መካከል ክላም፣ መስል፣ ኦይስተር፣ ስካለፕ፣ ኦክተፐስና ስኩዊድ ይገኙበታል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሃል ለመሃል የተቆረጠ የሞለስክ ዛጎል ውስጠኛ ክፍል ጎላ ተደርጎ ሲታይ

[ምንጭ]

Inset: © Eye of Science/Photo Researchers, Inc.