በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሀብታም እንድትሆን ይፈልጋል?

አምላክ ሀብታም እንድትሆን ይፈልጋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ሀብታም እንድትሆን ይፈልጋል?

“አምላክ ቀን እንዲወጣልኝ አድርጓል! የናጠጥኩ ሀብታም ልሆን ነው!”

“በሰማይ ያሉት ሁሉ ሀብታም እንድሆን ስለሚፈልጉ ሀብታም የመሆን ሕልም አለኝ።”

“አምላክ ባለጸጋ እንድንሆን ኃይል ይሰጠናል።”

“ሀብታም የሆንኩት በመጽሐፍ ቅዱስ የተነሳ ነው።”

እነዚህ አባባሎች፣ ሀብት የአምላክ በረከት መግለጫ እንደሆነ የሚያስቡ በርካታ ሃይማኖቶችን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ናቸው። እነዚህ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት ከሆነ አምላክ የሚፈልገውን ካደረግክ በአሁኑ ሕይወትህ ሀብታም ያደርግሃል፤ ወደፊትም ይባርክሃል። እንዲህ ያለው ሃይማኖታዊ ትምህርት በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ከመሆኑም ሌላ ስለዚህ ጉዳይ የሚያብራሩ መጻሕፍት ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው። ይሁን እንጂ ሀብታም መሆንን የሚያበረታታው እንዲህ ያለው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ደስተኛ አምላክ’ ብሎ የሚጠራው ፈጣሪያችን የተሳካና ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ እንደሚፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ መዝሙር 1:1-3) ከዚህም በላይ አምላክ፣ እሱን የሚያስደስት ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን ይባርካል። (ምሳሌ 10:22) ይሁንና በአሁኑ ጊዜ አምላክ የሚባርከን ቁሳዊ ሀብት በመስጠት ነው? በአምላክ ዓላማ ውስጥ አሁን በየትኛው ጊዜ ላይ እንደምንገኝ መገንዘባችን የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ይረዳናል።

ሀብታም የምንሆንበት ጊዜ ነው?

በጥንት ዘመን ይሖዋ አምላክ አንዳንድ አገልጋዮቹን ሀብት በመስጠት ባርኳቸዋል፤ ለዚህም ኢዮብና ንጉሥ ሰለሞን ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። (1 ነገሥት 10:23፤ ኢዮብ 42:12) በሌላ በኩል ግን መጥምቁ ዮሐንስንና ኢየሱስን ጨምሮ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው በርካታ ሰዎች ቁሳዊ ሀብት አልነበራቸውም። (ማርቆስ 1:6፤ ሉቃስ 9:58) ከዚህ ምን እንረዳለን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው አምላክ ለአገልጋዮቹ አንድ ነገር የሚያደርገው በወቅቱ ለእነሱ ካለው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። (መክብብ 3:1) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚያሳዩት የምንኖረው ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ወይም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ ነው። ባለንበት ዘመን ጦርነት፣ በሽታ፣ ረሃብ፣ የመሬት መናወጥ እንዲሁም የማኅበራዊ ግንኙነት መበላሸት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በብዙ ቦታዎች እንደሚኖር አስቀድሞ ተነግሯል፤ እነዚህ ችግሮች ከ1914 ወዲህ ባሉት ዓመታት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዓለማችንን እያመሷት ነው። (ማቴዎስ 24:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ሉቃስ 21:10, 11፤ ራእይ 6:3-8) በአጭር አነጋገር ዓለማችን በመስመጥ ላይ እንዳለች መርከብ ናት! ከእነዚህ ሁኔታዎች አንጻር አምላክ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ ቁሳዊ ሀብት በመስጠት ይባርከዋል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል? ወይስ አምላክ ቅድሚያ እንድንሰጣቸው የሚፈልጋቸው ሌሎች ነገሮች ይኖራሉ?

ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንበትን ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም። የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:37-39) ኢየሱስ ያለንበትን ዘመን ከሎጥ ዘመን ጋርም አመሳስሎታል። በሰዶምና ገሞራ የነበሩት የሎጥ ጎረቤቶች “ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይገዙ፣ ይሸጡ፣ ይተክሉና ይገነቡ ነበር።” ሆኖም “ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ከሰማይ እሳትና ድኝ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል።—ሉቃስ 17:28-30

መብላት፣ መጠጣት፣ ማግባት፣ መግዛትና መሸጥ ምንም ስህተት እንደሌለው ግልጽ ነው። አደገኛ የሚሆነው የጊዜውን አጣዳፊነት ማስተዋል እስኪሳነን ድረስ በእነዚህ ነገሮች ከመጠን በላይ መጠመዳችን ነው። በመሆኑም ራስህን እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ ‘አምላክ ትኩረታችንን የሚከፋፍሉ ነገሮችን በመስጠት የሚባርከን ከሆነ የሚጠቅመንን ነገር አድርጎልናል ማለት ይቻላል?’ * በጭራሽ። እንዲያውም በጣም የሚጎዳንን ነገር ማድረጉ ይሆናል። የፍቅር አምላክ ደግሞ እንዲህ አያደርግም!—1 ጢሞቴዎስ 6:17፤ 1 ዮሐንስ 4:8

ሕይወት የምናድንበት ጊዜ ነው!

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ዘመን የአምላክ ሕዝቦች የሚያከናውኑት አጣዳፊ ሥራ አላቸው። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጥቅስ በቁም ነገር ይመለከቱታል። በዚህም ምክንያት ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ሊያሟሏቸው ስለሚገቡት ብቃቶች እንዲማሩ ያበረታታሉ።—ዮሐንስ 17:3

ይህ ሲባል ግን አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ የብሕትውና ሕይወት እንዲመሩ ይጠብቅባቸዋል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እሱን በማገልገል ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ ለሕይወት አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ረክተው እንዲኖሩ ይፈልጋል። (ማቴዎስ 6:33) ይህን ካደረጉ የሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች እንዲሟሉላቸው ያደርጋል። ዕብራውያን 13:5 እንዲህ ይላል፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ አሁን ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። ምክንያቱም [አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏል።”

አምላክ፣ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሆኑ እውነተኛ አምላኪዎቹ በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈው ሰላም ወደሰፈነበትና እውነተኛ ብልጽግና ወደሚገኝበት አዲስ ዓለም እንዲገቡ ሲያደርግ ከላይ የገባውን ቃል በላቀ ሁኔታ ይፈጽማል። (ራእይ 7:9, 14) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የመጣሁት [ታማኝ ተከታዮቼ] ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው።” (ዮሐንስ 10:10) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘የተትረፈረፈ ሕይወት’ የሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ ቁሳዊ ብልጽግና ማግኘትን ሳይሆን በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘትን ነው።—ሉቃስ 23:43

የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስትችል፣ ሀብታም መሆንን በሚያበረታታው ትምህርት በመታለል የዚህን ዓለም ሀብት ለማግኘት ለምን ትሮጣለህ? እንደ እውነቱ ከሆነ ሀብታም መሆንን የሚያበረታታው ይህ ትምህርት አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንዳታተኩር የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስቶ የሰጠውን የሚከተለውን አጣዳፊ ምክር ተግባራዊ አድርግ፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል።”—ሉቃስ 21:34, 35

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ሀብታሞች ናቸው። ይሁንና አምላክ እነዚህ ክርስቲያኖች በሀብታቸው እንዳይመኩ እንዲሁም ትኩረታቸው በቁሳዊ ነገሮች እንዳይከፋፈል አስጠንቅቋቸዋል። (ምሳሌ 11:28፤ ማርቆስ 10:25፤ ራእይ 3:17) ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች ሁሉም ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል።—ሉቃስ 12:31

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ያለንበት ዘመን ምን የሚደረግበት ጊዜ ነው?—ማቴዎስ 24:14

▪ ኢየሱስ ዘመናችንን ከእነማን ዘመን ጋር አመሳስሎታል?—ማቴዎስ 24:37-39፤ ሉቃስ 17:28-30

▪ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ምን ከማድረግ መቆጠብ አለብን?—ሉቃስ 21:34

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሀብታም መሆንን የሚያበረታታው ትምህርት አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንዳታተኩር የሚያደርግ ነው