በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ፈተናዎችን መቋቋም እንድችል ረድቶኛል

አምላክ ፈተናዎችን መቋቋም እንድችል ረድቶኛል

አምላክ ፈተናዎችን መቋቋም እንድችል ረድቶኛል

ቫዚር አዛኖቭ እንደተናገረው

ከአልጋዬ ላይ ዘልዬ ወረድኩና ልብሴን በፍጥነት ለባበስኩ። የተኛሁ ለማስመሰል የተወሰኑ ልብሶችን ጠቅልዬ አልጋው ላይ ካደረግኳቸው በኋላ በብርድ ልብስ ሸፈንኳቸው። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሴን በጀርባዬ ሻጥ አድርጌ በመስኮት ዘልዬ ወጣሁ። አምላክ እንዲረዳኝ እየጸለይኩ በሩጫ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄድኩ። ይህ የተፈጸመው በ1991 ሲሆን በወቅቱ የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ።

ቤተሰቦቼ ኩርዶች ሲሆኑ የምንኖረው አሁን ካዛክስታን ተብላ በምትጠራው አገር ደቡባዊ ክፍል ነበር፤ በዚያ ወቅት ካዛክስታን ከ15ቱ የሶቪየት ኅብረት ሪፑብሊኮች አንዷ ነበረች። ወላጆቼም ሆኑ ዘመዶቼ ወደፊት የሕዝባችን መሪና ነፃ አውጪ መሆን እንደምችል እንዲሰማኝ ያደርጉኝ ነበር። እኔም ለኩርድ ሕዝብ ጠላቶች ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበረኝ ሕዝባችንን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ ስል ጠላቶቻችን ከመግደል ወደኋላ አልልም ነበር።

በ1980ዎቹ መገባደጃ አካባቢ እኔ፣ እናቴና ታናሽ ወንድሜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። ይሁን እንጂ አባቴ ከክርስቲያኖች ጋር እንዳናጠና ከለከለን። እኔ ግን ማጥናቴን አላቋረጥኩም። በኩርድ ቤተሰብ ውስጥ ለቤተሰቡ ራስ አለመታዘዝ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። አባቴን እወደዋለሁ፤ የምማረውንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወድጄው ነበር።

በቤትና በትምህርት ቤት ያጋጠመኝ ተቃውሞ

በአንድ ወቅት አስተማሪዬ ቦርሳዬ ውስጥ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ተመለከተና ለወላጆቼ ነገራቸው። አባቴ ይህን ሲሰማ በጣም ተናዶ በኃይል ስለመታኝ ነሰረኝ። “አሁንም ያን ሃይማኖት አልተውክም?” በማለት ጮኸብኝ።

አባቴ ከዚያን ቀን ጀምሮ እንደ ልጁ አድርጎ እንደማይመለከተኝ ተናገረ። ይህን ስሰማ ስሜቴ በጣም ተጎዳ! በዚያን ወቅት በርካታ የክፍል ጓደኞቼ የራቁኝ ሲሆን አንዳንዶቹም ፊት ለፊት ይሰድቡኝ ነበር። አስተማሪዎቼ ዝቅተኛ ውጤት ይሰጡኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ በትምህርት ክፍለ ጊዜ እምነቴን የሚያቃልል ነገር በመናገር እንደ እነሱ አምላክ የለሽ እንድሆን ለማድረግ ይሞክሩ ነበር።

እንደዚህ ያለ ተቃውሞ ቢያጋጥመኝም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና የተማርኩትን እውነት ለሌሎች ለማሳወቅ ጥረት አደርግ ነበር። ብዙም ሳይቆይ አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰቤን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤን እንዳልተውኩ አወቀ። አንድ እሁድ ቀን፣ ስብሰባ ለመሄድ ስል ከቤት ለመውጣት የሚያስችለኝ ምክንያት ፈጥሬ ለአባቴ ነገርኩት። አባቴ ግን ወዲያውኑ እንድተኛ አዘዘኝ። አክሎም “ከአሁን በኋላ እሁድ እሁድ በዚህ ሰዓት መተኛት አለብህ” አለኝ። መመሪያውን ከጣስኩ ከባድ ቅጣት እንደሚደርስብኝ ያስጠነቀቀኝ ሲሆን አባቴ የተናገረውን እንደሚፈጽመው አንዳች ጥርጣሬ አልነበረኝም።

የአባቴን ልብ እንዲያራራልኝ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን እያለቀስኩ ለመንኩት፤ የአባቴ አመለካከት ግን አልተለወጠም። ይህ ሁኔታ እስራኤላውያን በግብጽ ይደርስባቸው የነበረውን ጭቆና እንዳስብ አደረገኝ። አባቴ የወሰደው እርምጃ እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲያመልኩ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ያልነበረውን ፈርዖንን አስታወሰኝ።—ዘፀአት 5:1, 2

ውሳኔ ማድረግ

አንድ እሁድ ቀን ወደ ስብሰባ ለመሄድ ወሰንኩ። አልጋዬ ላይ ተኝቼ ከጭንቀቴ የተነሳ ልቤ በኃይል እየመታ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። ወላጆቼ ሊያዩኝ ወደ ክፍሌ ሲመጡ ልክ እንደተኛ ሰው ሆንኩ። አባቴም “እንዴት ዓይነት ታዛዥ ልጅ እንዳለኝ አየሽ” በማለት በኩራት ተናግሮ ከሳመኝ በኋላ ቀስ ብለው ከክፍሌ ወጡ። እኔም ልባዊ ጸሎት ማቅረቤን ቀጠልኩ።

ወላጆቼ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት በፍጥነት ተነሳሁና አልጋዬ ሥር የነበረውን ጫማዬን አድርጌ በመስኮት ዘልዬ ወጣሁ። ሁለት ሰዓት የሚወስደው ስብሰባ ሳላስበው አለቀ፤ ከዚያም ቤት ስመለስ ምን እንደሚጠብቀኝ ማሰብ ጀመርኩ። ደግነቱ፣ እናቴ እኔ እንደወጣሁና አልጋው ላይ ያለው ልብሴ እንደሆነ ብታይም ለአባቴ አልነገረችውም። ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ እንዲህ ባደርግ ሁኔታውን ለአባቴ እንደምትነግረው አስጠነቀቀችኝ።

በ1992 አንድ ቀን፣ ጓደኛዬ አንድ ልዩ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝና እኔም አብሬው እንድሄድ እንደተጋበዝኩ ለወላጆቼ ነገርኳቸው። እንዲህ ያልኳቸው የትውልድ ከተማዬ ከሆነችው ከካራታዉ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ በምትገኘው በታራዝ ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ስለፈለግኩ ነበር። ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት የማሳየው በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። በስብሰባው ላይ ለመገኘት የሚያስችለኝን ገንዘብ ለማግኘት ስል እናቴ ከጎተራችን አንድ ባልዲ ሱፍ እንድትሰጠኝ ጠየቅኋትና ሱፉን ቆልቼ ገበያ ወስጄ ሸጥኩት።

ከስብሰባው ወደ ቤት ስመለስ አባቴ ‘ከጓደኛህ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳለፍክ?’ በማለት ጠየቀኝ። እኔም አስደሳች ጊዜ እንዳሳለፍኩ ነገርኩት። አባቴ ተጨማሪ ጥያቄ ስላልጠየቀኝ ይሖዋ እንደረዳኝ ተሰማኝ። በምሳሌ 3:5, 6 ላይ የሚገኘውን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” የሚለውን ሐሳብ በጣም እወደዋለሁ።

በመንፈሳዊ ተዳከምኩ

ከተጠመቅሁ በኋላም ቢሆን አባቴ ተቃውሞውን አላቆመም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘቴን ስለቀጠልኩ አባቴ በሰው ፊትም ሆነ ብቻዬን ስሆን በኃይል ይደበድበኝ ነበር። በየቀኑ ማለት ይቻላል ስለሚያዋርደኝና ሃይማኖቴን እንድተው ጫና ስለሚያደርግብኝ ብዙ ጊዜ አለቅስ ነበር። በወቅቱ ካዛክስታን ከሶቭየት ኅብረት ነፃ መውጣቷ ስለነበር ወላጆቼም ሆኑ ዘመዶቼ ፓለቲከኛ ሆኜ ለአገር የሚጠቅም አንድ ነገር እንድሠራ ይገፋፉኝ ነበር። ቤተሰቦቼ ጥሩ አጋጣሚ እያመለጠኝ እንዳለ ተሰምቷቸው ነበር።

ታላቅ ወንድሜ በስፖርቱ ዓለም ዝነኛ ሆኖ ስለነበር አባቴ የእሱን ምሳሌ እንድከተል ብዙ ጊዜ ያበረታታኝ ነበር። በ1994 መገባደጃ አካባቢ እኔም ስፖርተኛ ሆንኩ። በእግር ኳስና በጂምናስቲክ ጥሩ ችሎታ ስለነበረኝ ብዙም ሳይቆይ ሽልማቶችን ከማግኘቴም በላይ አድናቆት አተረፍኩ። ከዚህም በላይ የኩርዶችን ጥቅም ለማስጠበቅ እንድችል ሕግ ማጥናት ጀመርኩ። ሌላው ቀርቶ ፖለቲካ ትኩረቴን ስለሳበው የኩርድ ወጣቶች ፓርቲ ለማቋቋም አሰብኩ። በዚህ ጊዜ አባቴ ያደንቀኝ ጀመር።

“አንተ አሸንፈሃል አባባ”

በመንፈሳዊ ተዳክሜ የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብም ሆነ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት አቆምኩ። ሳድግ እንደገና ይሖዋን አመልካለሁ በማለት ራሴን አጽናና ነበር። በአንድ ወቅት አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እገናኝ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም “አልገናኝም። አንተ አሸንፈሃል አባባ። አሁን ደስ አለህ?” በማለት መለስኩለት። አባቴ ይህን ሲሰማ በጣም ተደሰተ። ከዚያም “አሁን የእኔ ልጅ ሆነሃል!” በማለት በኩራት ተናገረ።

በስብሰባዎች ላይ ሳልገኝ ሁለት ዓመታት አለፉ። አንዳንድ ጊዜ ወደ ስብሰባ መሄድ ብፈልግም እፍረት ስለሚሰማኝ መሄድ አልቻልኩም። በጉባኤ ያሉት ወንድሞች ሁኔታዬን እንደማይረዱልኝ ይሰማኝ ነበር።

ያም ቢሆን ይሖዋን ከማገልገል የተሻለ ምንም ነገር እንደሌለ አስብ ነበር። ‘ምንም ሆነ ምን፣ ይሖዋን እወደዋለሁ!’ የሚለው ሐሳብ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር። ከዚያም አባቴ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንድከታተል ጫና ያደርግብኝ ጀመር። እኔም የአባቴን ሐሳብ የተቀበልኩ ሲሆን እንዲያውም ትምህርቴን በማዕረግ ለማጠናቀቅ ቃል ገባሁ። በልቤ ግን ዩኒቨርሲቲው ወደሚገኝባት ከተማ እንደደረስኩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት አስቤ ነበር፤ ዩኒቨርሲቲው ያለው በደቡባዊ ካዛክስታን በምትገኘው ኦልማቲ የተባለች ትልቅና ዘመናዊ ከተማ ውስጥ ነው።

ሁኔታዎች በሚያስደስት መንገድ ተለወጡ

በዩኒቨርሲቲው መማር ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች መንገድ ላይ ሲያገለግሉ አገኙኝና “ዓለምን የሚገዛው ማን ይመስልሃል?” ብለው ጠየቁኝ።

እኔም “የይሖዋና የሰው ዘር ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው” በማለት መለስኩላቸው። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ከዚያም የተጠመቅሁ የይሖዋ ምሥክር እንደነበርኩ፣ አሁን ግን ስብሰባ እንደማልሄድና እንደማላገለግል ነገርኳቸው።

በ1996 መጨረሻ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በድጋሚ ማጥናት ጀመርኩ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ካጠናሁ በኋላ ይሖዋን እንደገና በሙሉ ልቤ ለማገልገል የተነሳሳሁ ሲሆን በኦልማቲ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በሁሉም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ጀመርኩ። በመስከረም 1997 የዘወትር አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ) ሆንኩ።

ከአንድ ዓመት በኋላ አባቴ ሊጠይቀኝ መጣ። አባቴን ሳየው ሮጬ ወደ እሱ ሄድኩና ተቃቅፈን ሰላም ተባባልን። አባቴ በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ላደረጋቸው ነገሮች ይቅርታ ጠየቀኝ። ስለ እምነቴ የተሳሳተ አመለካከት እንደነበረውና እኔንም እንዳልተረዳኝ ነገረኝ። እኔም “አባባ፣ በጣም እወድሃለሁ” አልኩት።

አባቴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከመውሰዱም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት እንደሚፈልግ ሲነግረኝ በጣም ደስ አለኝ! መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ እንዳሰበ ገለጸልኝ። ከአንድ ዓመት በኋላ ከእናቴ ጋር በመሆን እንደገና ሊጠይቀኝ መጣ። ወደ መንግሥት አዳራሽ አብረን የሄድን ሲሆን በዚያም የተለያየ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ወደ ወላጆቼ መጥተው ሞቅ ያለ ሰላምታ በመስጠት ተዋወቋቸው። አባቴ በዚህ ሁኔታ ልቡ በጥልቅ ስለተነካ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በጉጉት ማንበብ ጀመረ።

የተትረፈረፈ በረከት

በመስከረም 2001 ዬሌና ከተባለች ጥሩ ባሕርይ ያላት ሩሲያዊት ወጣት ጋር ተጋባን። ዬሌና የተጠመቀችው በ1997 ሲሆን በግንቦት 2003 ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ወላጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደጀመሩና መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ እንደሆነ ስንሰማ በጣም ተደሰትን። ይህን አስደሳች ዜና ከአባቴ አንደበት እስክሰማ ድረስ አላመንኩም ነበር። ከአባቴ ጋር በስልክ ስናወራ ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን ነገረኝ!

በኦልማቲ ስኖር ከሶርያ፣ ከቱርክ፣ ከቻይና፣ ከኢራን፣ ከፓኪስታን እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናት አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በቅርቡ አንድ ኢራናዊ ቄስ፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በፋርስ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳስጠናው ጠይቆኛል። ከአፍጋኒስታን የመጣ ቀደም ሲል ጄኔራል የነበረ አንድ ሰው ስለ ይሖዋ በተማረው ነገር በጣም ተደነቀ። ከሶርያ የመጣን ሌላ ሰው ደግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ በሆነው በኩርድ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናቴ አስደስቶኛል። ከዚህም በተጨማሪ በልጅነቴ በተማርኳቸው በሩሲያና በካዛክ ቋንቋዎች ሰዎችን አስጠናለሁ።

በአሁኑ ጊዜ እኔና ዬሌና በኦልማቲ ከሚገኙት ከ35 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች መካከል በአንዱ እያገለገልን ነው። ያለንበት ጉባኤ በካዛክ ቋንቋ ከሚመሩት ጉባኤዎች አንዱ ነው። ባለፈው ዓመት እኔና ዬሌና በቅርቡ ግንባታው በተጠናቀቀው በኦልማቲ አቅራቢያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የማገልገል መብት አግኝተን ነበር።

በአንድ ወቅት ጠላቶቼን እንድጠላ ተምሬ ነበር፤ ይሖዋ ግን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንድወድ አስተምሮኛል። ስለ እኛ የሚያስቡ ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ይሖዋን ማምለካችንን እንድናቆም ተጽዕኖ ቢያደርጉብንም ፈጽሞ እነሱን መስማት እንደሌለብን ተረድቻለሁ። (ገላትያ 6:9) በአሁኑ ጊዜ እኔና ባለቤቴ ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ በመሆናችን በጣም ደስተኛ ነን።—1 ቆሮንቶስ 15:58 የ1954 ትርጉም

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እናቴ ከዚህ በኋላ እንዲህ ባደርግ ሁኔታውን ለአባቴ እንደምትነግረው አስጠነቀቀችኝ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣት እያለሁ እሰበሰብበት የነበረው በካራታዉ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቼ በአሁኑ ወቅት ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት አላቸው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ዬሌና በሠርጋችን ቀን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዬሌና ጋር፣ በኦልማቲ አቅራቢያ በሚገኘው አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ፊት ለፊት