በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ቀኑን ጨለማ ዋጠው”

“ቀኑን ጨለማ ዋጠው”

“ቀኑን ጨለማ ዋጠው”

ቤኒን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“የሚደንቅ ነው! የፀሐይ ግርዶሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስደመመ።” መጋቢት 29, 2006 በታየው ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ማግስት የጋናው ዴይሊ ግራፊክ በርዕሰ አንቀጹ ላይ ከላይ ያለውን ሐሳብ አስፍሮ ነበር። ይህ የፀሐይ ግርዶሽ መጀመሪያ የታየው በብራዚል ምሥራቃዊ ጫፍ ሲሆን በሰዓት 1,600 ኪሎ ሜትር ገደማ በሆነ ፍጥነት እየተጓዘ አትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥ ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ በውቅያኖሱ ዳርቻ ላይ በሚገኙት በጋና፣ በቶጎና በቤኒን ታየ። በእነዚህ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የፀሐይ ግርዶሹ ሲታይ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ከዚህ በፊት በጋና ላይ ሙሉ ግርዶሽ የታየው በ1947 ነበር። በዚያን ጊዜ ዕድሜው 27 ዓመት የነበረው ቲኦዶር በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “በዚያን ጊዜ የነበሩ ብዙ ሰዎች ከዚያ ቀደም የፀሐይ ግርዶሽ አይተው ስለማያውቁ ምን እየተፈጸመ እንዳለ አልገባቸውም ነበር። በዚህም ምክንያት ሰዎች ሁኔታውን የገለጹት ‘ቀኑን ጨለማ ዋጠው’ በማለት ነበር።”

ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ የተደረጉ ዘመቻዎች

ባለ ሥልጣናት በግርዶሹ ወቅት ፀሐይን መመልከት አደገኛ መሆኑን ለሕዝቡ ለማስጠንቀቅ ሰፊ የዘመቻ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። በቶጎ፣ “ለዓይናችሁ ተጠንቀቁ! ልትታወሩ ትችላላችሁ!” የሚሉ ትኩረት የሚስቡ ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፈው ነበር።

የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ሕዝቡ ሁለት አማራጮችን እንዳለው ጠበቅ አድርገው ገለጹ። አንደኛው፣ የፀሐይ ግርዶሹ በሚታይበት ሰዓት ከቤት ሳይወጡ ትርዒቱን በቴሌቪዥን መከታተል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከቤት ውጭ ከሆኑ ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጁ ለየት ያሉ መከላከያ መነጽሮችን ማድረግ ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን አስደናቂ ክስተት ለማየት በቴሌቪዥናቸውና በኮምፒውተራቸው ፊት ተደቅነው ይጠባበቁ ነበር። ይሁን እንጂ ቴሌቪዥንም ሆነ ኮምፒውተር የፀሐይ ግርዶሹ ከመከሰቱ በፊትና በግርዶሹ ወቅት ሕዝቡ ሁኔታውን በጉጉትና በመደነቅ ሲመለከት የነበረውን ሁካታ ፈጽሞ ማስተላለፍ አይችሉም። እስቲ በዚያ ወቅት በቦታው ተገኝቶ ሁኔታውን መመልከት ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ እንሞክር።

በጉጉት መጠባበቅ

በምዕራብ አፍሪካ፣ ማለዳ ላይ ቀኑ እንደወትሮው ብራ ነበር፤ ሰማዩም ጥርት ብሏል። ግርዶሹ ይከሰት ይሆን? የፀሐይ ግርዶሹ ይታያል የተባለበት ሰዓት እየተቃረበ ሲመጣ ከቤት ውጭ ያሉት ሰዎች ልዩ መነጽራቸውን አድርገው ወደ ሰማይ ማንጋጠጥ ጀመሩ። አንዳንዶች ደግሞ በሌላ አካባቢ ወዳሉት ወዳጆቻቸው በሞባይል ስልካቸው እየደወሉ ያዩት ነገር ካለ ይጠይቁ ነበር።

መጀመሪያ ላይ ባትታይም ከተመልካቹ ሕዝብ አናት በላይ 350,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጨረቃ ፀሐይዋን ወደምትጋርድበት ቦታ እየገሰገሰች ነበር። በድንገት አንዲት ጥቁር ስንጥር መስላ በመታየት ፀሐይን መጋረድ ጀመረች። ቀስ በቀስ ሕዝቡ ሲመለከታት ሁካታው እየጨመረ ሄደ።

የፀሐይ ግርዶሹ በጀመረበት ሰዓት ሕዝቡ በአካባቢው አንዳች ለውጥ መኖሩን ልብ አላለም ነበር። ይሁን እንጂ ጨረቃዋ እያሸነፈች ስትሄድ ሰማዩ መለወጥ ጀመረ። ሰማያዊ የነበረው ሰማይ እየጠቆረ መጣ። የአየሩ ሙቀት ቀነሰ። ንጋቱ እየጨለመ ሲሄድ የመንገድና የጥበቃ መብራቶች በሩ። ጎዳናዎቹም ጭር አሉ። ሱቆች ተዘጉ። ወፎች መንጫጫታቸውን አቆሙ፤ ሌሎቹ እንስሳትም መጠለያ ፈልገው ለመተኛት ይዘጋጁ ጀመር። ፀሐይዋ ሙሉ በሙሉ ስትጋረድ አካባቢው በጨለማ ተዋጠ፤ ሁሉም ነገር ፀጥ ረጭ አለ።

ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽየማይረሳ ክስተት

ከዋክብት ሲያንጸባርቁ ይታዩ ጀመር። አንጸባራቂ የሆነው የፀሐይ ውጫዊ ክፍል ጥቁር በሆነችው ጨረቃ ዙሪያ ያለ የብርሃን አክሊል መሰለ። ፀሐይዋ፣ ጨረቃ ላይ በሚገኙት ሸለቆዎችና ወጣ ገባ ቦታዎች ላይ ስትፈነጥቅ የሚፈጠሩት አንጸባራቂ ነጥቦች (የቤሊ ዶቃዎች * ተብለው ይጠራሉ) በጨረቃ ዙሪያ መታየት ጀመሩ። በፀሐይዋ ዙሪያ የሚፈነጥቀው የአልማዝ ቀለበት የሚመስል ቅርጽ ያለው ብርሃን ይበልጥ ደምቆ ታየ። ከፀሐይዋ ውጫዊ ክፍል በታች ባለው ገጽ ላይ አስደናቂ የሆነ ቀላ ያለና ሮዝ ቀለም ያለው ብርሃን ታየ። አንድ ተመልካች “እስከ ዛሬ ካየኋቸው ሁሉ እጅግ አስደናቂ ትርዒት፣ አስደናቂ ውበት” በማለት አድናቆቱን ገልጿል።

ፀሐይዋ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ የቆየችው ለሦስት ደቂቃዎች ገደማ ነበር። ከዚያም ፀሐይዋ እንደገና መታየት ጀመረች። በዚህ ጊዜ የበርካታ ተመልካቾች የደስታ ጭብጨባ አስተጋባ። ሰማዩ እየጠራ ሲመጣ ከዋክብትም ከእይታ ተሰወሩ። ልክ እንደ ንጋት ጭጋግ እንግዳ የነበረው የአካባቢው ሁኔታ ተገፈፈ።

ጨረቃ “በሰማይ ታማኝ ምስክር” በመሆኗ ግርዶሽ የሚከሰትበትን ጊዜ በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ በስሌት ማወቅ ይቻላል። (መዝሙር 89:37) ምዕራብ አፍሪካ ይህን ሙሉ ግርዶሽ ለማየት 60 ለሚያህሉ ዓመታት ጠብቃለች። በሚቀጥለው ጊዜ በምዕራብ አፍሪካ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚታየው በ2081 ነው። ከዚያ በፊት አንተም ይህን የማይረሳ ክስተት በአካባቢህ የማየት አጋጣሚ ይኖርህ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ይህ መጠሪያ የተሰጣቸው በ1836 በታየው ግርዶሽ ወቅት ስለ እነዚህ የብርሃን ጨረሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በመዘገበው ፍራንሲስ ቤሊ የተባለ ብሪታንያዊ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ስም ነው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ኢየሱስ በሞተበት ዕለት የፀሐይ ግርዶሽ ታይቶ ነበር?

ማርቆስ 15:33 “ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ” ይላል። ከቀትር ጀምሮ እስከ 9:00 ሰዓት የዘለቀው ይህ የሦስት ሰዓት ጨለማ ተአምራዊ ክስተት ነበር። የፀሐይ ግርዶሽ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም መጀመሪያ ነገር፣ በምድር ላይ በአንድ ቦታ የሚታየው ማንኛውም ረጅም የፀሐይ ግርዶሽ ሊቆይ የሚችለው ለሰባት ተኩል ደቂቃ ገደማ ነው። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሞተው ኒሳን በሚባለው የጨረቃ ወር በ14ኛው ቀን ላይ ነበር። የወሩ መጀመሪያ ቀን የሚወሰነው አዲስ ጨረቃ ስትወጣ ሲሆን በዚህ ወቅት ጨረቃ በምድርና በፀሐይ መካከል ስለምትሆን ግርዶሽ ሊፈጠር ይችላል። ኒሳን 14 ላይ ጨረቃ በምድር ዙሪያ ከምታደርገው ዙረት ግማሹን ታጠናቅቃለች። በዚህ ጊዜ ምድር በፀሐይና በጨረቃ መካከል የምትገኝ ሲሆን ጨረቃ ከፀሐይ የሚመጣውን ብርሃን በመጋረድ ፈንታ ሙሉ በሙሉ ታንጸባርቀዋለች። በመሆኑም በዚህ ቀን የኢየሱስን ሞት ለማክበር አስደሳች ሁኔታ የምትፈጥረውን ሙሉ ጨረቃ እናያለን።

[ሥዕል]

ኒሳን 14 ምንጊዜም የሚውለው ሙሉ ጨረቃ በሚሆንበት ቀን ወይም በዚያ ጊዜ አካባቢ ነው

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ግርዶሹ ያለፈባቸው ቦታዎች

⇧ አፍሪካ

ቤኒን ●

ቶጎ ●

ጋና ●

[ምንጭ]

ካርታ:- Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጋቢት 29, 2006 የታየው ሙሉ ግርዶሽ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሕዝቡ ልዩ መከላከያ መነጽሮችን በማድረግ ግርዶሹን በቀጥታ መመልከት ችሏል