በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሥርት

ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሥርት

እንዲህ አለማድረግ ምን ችግር አለው?

በአሉታዊ መንገድ ከምንመለከታቸው ሰዎች ራሳችንን የምናገል ከሆነ ጭፍን ጥላቻችን ይበልጥ ሥር እየሰደደ ሊሄድ ይችላል። በተጨማሪም ከእኛ ጋር ከሚመሳሰሉ ሰዎች ጋር ብቻ ጓደኝነት የምንመሠርት ከሆነ ተቀባይነት ያለው የእኛ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት ብቻ እንደሆነ አድርገን ማሰብ ልንጀምር እንችላለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ

“ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።”—2 ቆሮንቶስ 6:13

ከዚህ ጥቅስ ምን ትምህርት እናገኛለን? “ልብ” የሚለው አገላለጽ የአንድን ሰው ስሜት ያመለክታል። ከእኛ ጋር የሚመሳሰሉ ሰዎችን ብቻ የምንወድ ከሆነ ልባችን ዝግ ወይም ጠባብ ሊሆን ይችላል። ይህን ችግር ለማስወገድ ከእኛ ጋር ከማይመሳሰሉ ሰዎችም ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ፈቃደኞች መሆን አለብን።

ከተለያዩ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ስናውቃቸው አንዳንድ ነገሮችን ከእኛ በተለየ መንገድ የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ መረዳት እንጀምራለን። ደግሞም ይበልጥ እየቀረብናቸው ስንሄድ ከእኛ የተለዩ መሆናቸውን እንኳ ጨርሶ ልንረሳው እንችላለን። ለእነሱ ያለን አክብሮት የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ የደስታቸውም ሆነ የሐዘናቸው ተካፋዮች እንሆናለን።

የናዛሬን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ ወቅት ለስደተኞች ጭፍን ጥላቻ ነበራት። የነበረባትን ጭፍን ጥላቻ ለማስወገድ የረዳት ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍና አብሬ መሥራት ጀመርኩ። ይህም ሌሎች ከሚያስቧቸው ፈጽሞ የተለዩ ሰዎች እንደሆኑ እንዳስተውል ረድቶኛል። ከእናንተ የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ ሁሉንም በአንድ ከመፈረጅ እንድትርቁ ይረዳችኋል። ለእነሱ በግለሰብ ደረጃ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር ትጀምራላችሁ።”

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከሌላ አገር ከመጡ አሊያም ከአንተ የተለየ ዘር ወይም ቋንቋ ካላቸው ሰዎች ጋር የምትነጋገርበት አጋጣሚ ፈልግ። ለምሳሌ የሚከተሉትን ነገሮች ልታደርግ ትችላለህ፦

  • ስለ ራሳቸው አንዳንድ ነገሮችን እንዲነግሩህ ጠይቃቸው።

  • አብረውህ እንዲመገቡ ጋብዛቸው።

  • ስለ ራሳቸው ሲያወሩ በትኩረት በማዳመጥ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡት ነገር ለማወቅ ጥረት አድርግ።

ያሳለፉት ሕይወት ማንነታቸውን የቀረጸው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት መሞከርህ ለእነሱም ሆነ የዚያ ቡድን አባል ለሆኑ ሌሎች ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ይረዳሃል።