በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጃችሁን ስለ ፆታ ማስተማር

ልጃችሁን ስለ ፆታ ማስተማር

ተፈታታኙ ነገር

ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ወላጆች፣ ልጆቻቸው ስለ ፆታ ግንኙነት ከሌላ ሰው ከመስማታቸው በፊት ቀድመው የማስተማር አጋጣሚያቸው ሰፊ ነበር። እንዲሁም የልጃቸውን ዕድሜና ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ጉዳዩን በጊዜ ሂደት ማብራራት ይችሉ ነበር።

አሁን ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። ዘ ሎሊታ ኢፌክት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች ከትንሽነታቸው ጀምሮ ከፆታ ግንኙነት ጋር ለተያያዙ መልእክቶች ተጋላጭ እየሆኑ ነው፤ እንዲሁም ለልጆች ተብለው በሚዘጋጁ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩት ስለ ፆታ የሚያወሱ ነገሮች እየጨመሩ መጥተዋል።” ይህ ታዲያ ለልጆች ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ከፆታ ጋር የተያያዙ ነገሮች በየቦታው ይገኛሉ። ዴብራ ሮፍማን ቶክ ቱ ሚ ፈርስት በተባለው መጽሐፏ ላይ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ጭውውቶች፣ ማስታወቂያዎች፣ ፊልሞች፣ መጻሕፍት፣ የዘፈን ግጥሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ መልእክቶች፣ ጌሞች፣ ፖስተሮች እንዲሁም የሞባይልና የኮምፒውተር ስክሪኖች በፆታዊ ምስሎች፣ ወሬዎችና በተዘዋዋሪ በሚነገሩ እንዲህ ያሉ ሐሳቦች የተሞሉ ናቸው፤ ይህም [በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ በርካታ ልጆችና ትናንሽ ልጆችም ጭምር] ሳይታወቃቸውም ቢሆን በሕይወት ውስጥ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር . . . የፆታ ግንኙነት እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።”

የንግዱ ዓለም በከፊል ተጠያቂ ነው። ምርቶችን የሚያስተዋውቁና የሚሸጡ ድርጅቶች ተቃራኒ ፆታን የሚማርኩ ልብሶችን ለልጆች በመሸጥ፣ ከትንሽነታቸው ጀምሮ ለመልካቸው ከተገቢው በላይ ትኩረት መስጠትን እንዲማሩ ያደርጓቸዋል። ሶ ሴክሲ ሶ ሱን የተባለው መጽሐፍ “የንግድ አስተዋዋቂዎች ትናንሽ ልጆች በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው ስለሚያውቁ ይህን ፍላጎታቸውን ያገናዘበ ምርት ያቀርባሉ” ይላል። አክሎም “ሰዎቹ ከፆታ ጋር የተያያዙ ምስሎችንና ምርቶችን የሚያዘጋጁበት ዓላማ ልጆቹ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ለማበረታታት ሳይሆን ሸቀጣቸውን ለመሸጥ ነው” ብሏል።

እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። አንድ ሰው መኪና እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ማወቁ ብቻ ኃላፊነት የሚሰማው አሽከርካሪ እንዲሆን አያደርገውም፤ በተመሳሳይም ልጆች ስለ ፆታ ግንኙነት እውቀት ስላላቸው ብቻ ይህን እውቀት ተጠቅመው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ያደርጋሉ ማለት አይደለም።

ዋናው ነጥብ፦ ልጆቻችሁ “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን” እንዲያሠለጥኑ መርዳታችሁ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን አስፈላጊ ነው።—ዕብራውያን 5:14

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

እናንተ ራሳችሁ ንገሯቸው። ስለ ፆታ ግንኙነት ከልጆቻችሁ ጋር ማውራት ሊከብዳችሁ ቢችልም ይህን ማድረግ የእናንተ ኃላፊነት ነው። ይህን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባችሁ አስታውሱ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 22:6

ቀስ በቀስ ንገሯቸው። በአንድ ጊዜ ረዘም ያለ ሰዓት ወስዳችሁ ስለ ፆታ ግንኙነት ከልጆቻችሁ ጋር ከማውራት ይልቅ ዘና የምትሉባቸውን የተለያዩ አጋጣሚዎች ተጠቀሙ፤ ምናልባትም አብራችሁ በመኪና ስትጓዙ ወይም ቤት ውስጥ ሥራ ስትሠሩ እንዲህ ማድረግ ትችላላችሁ። ልጃችሁ ሐሳቡን አውጥቶ እንዲነግራችሁ ለማበረታታት የአመለካከት ጥያቄዎችን ተጠቀሙ። ለምሳሌ “እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች ደስ ይሉሃል?” ከማለት ይልቅ “ማስታወቂያ የሚያዘጋጁ ሰዎች ምርቶቻቸውን ለመሸጥ እንዲህ ያሉ ምስሎችን የሚጠቀሙት ለምን ይመስልሃል?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ልጃችሁ መልስ ከሰጠ በኋላ “አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?” ልትሉት ትችላላችሁ። —የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ዘዳግም 6:6, 7

ዕድሜያቸውን ያገናዘበ መረጃ ስጧቸው። ትምህርት ቤት ላልገቡ ሕፃናት፣ የፆታ ብልቶችን ትክክለኛ ስሞች እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት ከሚያደርሱ ሰዎች ራሳቸውን መጠበቅ ስለሚችሉበት መንገድ ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ። እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ ልጆች ስለሚወለዱበት መንገድ አንዳንድ መሠረታዊ መረጃዎችን ልትነግሯቸው ትችላላችሁ። የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርሱ፣ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ይበልጥ የተሟላ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል።

የሥነ ምግባር እሴቶችን አስተምሯቸው። ልጃችሁን ከሕፃንነቱ አንስቶ ስለ ሐቀኝነት፣ ስለ ታማኝነት እንዲሁም አክብሮት ስለ ማሳየት አስተምሩት። ከዚያም ስለ ፆታ ግንኙነት ሲነሳ ቀደም ሲል በነገራችሁት ነገር ላይ ተመሥርታችሁ ልታስተምሩት ትችላላችሁ። በተጨማሪም ለልጆቻችሁ የምትመሩባቸውን የሥነ ምግባር እሴቶች በግልጽ ንገሯቸው። ለምሳሌ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ተገቢ እንዳልሆነ የምታምኑ ከሆነ ይህንን አሳውቋቸው። እንዲሁም ይህን ማድረግ ስህተት ብሎም ጎጂ የሆነው ለምን እንደሆነ አብራሩላቸው። ቢዮንድ ዘ ቢግ ቶክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች፣ የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው ተገቢ እንዳልሆነ ወላጆቻቸው የሚነግሯቸው ከሆነ በዚያ ዕድሜ የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም የመቆጠብ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።”

ምሳሌ ሁኑ። ለልጆቻችሁ በምታስተምሩት የሥነ ምግባር እሴት ተመሩ። እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስቡባቸው፦ የብልግና ቀልዶች ሲነገሩ ትስቃላችሁ? አለባበሳችሁ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነው? ታሽኮረምማላችሁ? እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁ ስለ ሥነ ምግባር እሴቶች የምታስተምሯቸውን ነገር አክብደው ላያዩት ይችላሉ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሮም 2:21

አዎንታዊ ሁኑ። የፆታ ግንኙነት የአምላክ ስጦታ ነው፤ እንዲሁም በትክክለኛው ሁኔታ ሥር ማለትም በጋብቻ ውስጥ ከተፈጸመ የደስታ ምንጭ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 5:18, 19) ልጃችሁም ትዳር እስኪመሠርት ድረስ ከታገሠ፣ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ከሚያስከትለው የስሜት ሥቃይና ጭንቀት ነፃ ሆኖ ይህንን ስጦታ ማጣጣም እንደሚችል ንገሩት።—1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19