በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ትዳር

ልጆች ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ

ልጆች ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ

ተፈታታኙ ነገር

አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስቶች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ቤት ውስጥ ብቻቸውን ሲቀሩ እርስ በርስ እንደማይተዋወቁ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። የቤተሰብ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ጋሪ ኒውማን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር እንደቀድሞው ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ያልቻሉ ብዙ ሰዎች ምክር ለማግኘት ይመጣሉ። አብዛኛውን ጊዜ ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ከወጡ በኋላ የሚወያዩበት የጋራ ጉዳይ አይኖርም።” *

እናንተስ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟችሁ ይሆን? ከሆነ በመካከላችሁ የነበረውን ወዳጅነት ማደስ የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ግን ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የነበራችሁ ግንኙነት እንዲላላ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን አንዳንድ ነገሮች እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

ባለትዳሮቹ ለበርካታ ዓመታት ቅድሚያ የሚሰጡት ለልጆቻቸው ነበር። ብዙ ወላጆች በቅን ልቦና ተነሳስተው ከትዳር ጓደኛቸው ፍላጎት ይልቅ ለልጆቻቸው ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጣሉ። ለበርካታ ዓመታት በአባትነትና በእናትነት ኃላፊነታቸው ተጠምደው ስለሚቆዩ የባልነትና የሚስትነት ድርሻቸውን ሊዘነጉት ይችላሉ፤ በተለይ ደግሞ ልጆች አድገው ከቤት ሲወጡ ይህ ሁኔታ ይበልጥ ጎልቶ ሊታይ ይችላል። አንዲት የ59 ዓመት ባለትዳር ሴት “ልጆቻችን ከእኛ ጋር በነበሩ ጊዜ ቢያንስ አንዳንድ ነገሮችን አብረን እንሠራ ነበር” ብላለች። ልጆቹ ከቤት ከወጡ በኋላ ግን “በየፊናችን መንቀሳቀስ ጀመርን” በማለት ተናግራለች። እንዲያውም በአንድ ወቅት ባሏን “እኔና አንተ ጨርሶ ባንደራረስ ይሻላል” እስከማለት ደርሳ ነበር።

አንዳንድ ባለትዳሮች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ይህን ለውጥ ማስተናገድ ይከብዳቸዋል። ኤምፕቲ ኔስቲንግ የተባለው መጽሐፍ “ብዙ ባለትዳሮች አዲስ ትዳር የመሠረቱ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል” ይላል። በርካታ ባሎችና ሚስቶች ልጆቻቸው ከቤት ከወጡ በኋላ የጋራ የሆነ ነገር እንደሌላቸው ሆኖ ስለሚሰማቸው የየራሳቸውን ጉዳይ በተናጠል ማከናወን ይጀምራሉ፤ በዚህ ጊዜ እንደ ትዳር ጓደኛሞች ሳይሆን እንደ ደባል መተያየት ሊጀምሩ ይችላሉ።

ደስ የሚለው ነገር፣ በዚህ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ማስወገድ እንዲያውም አጋጣሚውን በተሻለ መንገድ መጠቀም ትችላላችሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመልከት።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ከሁኔታው ጋር ተስማምታችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል” ይላል። (ዘፍጥረት 2:24) በመሆኑም ልጆች ካደጉ በኋላ ከወላጆቻቸው መለየታቸው አይቀርም። ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ለልጆቻችሁ ከወዲሁ ተገቢውን ሥልጠና መስጠታችሁ አስፈላጊ ነው፤ ራሳቸውን ችለው መኖር በሚጀምሩበት ጊዜ ሊጠቅሟቸው የሚችሉ ችሎታዎችን እንዲያዳብሩ መርዳት ይኖርባችኋል። በዚህ ረገድ የምታደርጉት ጥረት ተሳክቶ ልጆቻችሁ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ በማየታችሁ ልትኮሩ ይገባል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ማርቆስ 10:7

እርግጥ ነው፣ ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው መኖር ቢጀምሩም ምንጊዜም ለልጆቻችሁ ወላጅ መሆናችሁ አይቀርም። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ እንደቀድሞው ልጆቻችሁን ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ እንደ አስፈላጊነቱ ምክር መለገሳችሁ የተሻለ ነው። ይህም በአንድ በኩል ለትዳር ጓደኛችሁ ተገቢውን ትኩረት እንድትሰጡ በሌላ በኩል ደግሞ ከልጆቻችሁ ጋር ያላችሁን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቃችሁ እንድትኖሩ ያስችላችኋል። *የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ማቴዎስ 19:6

የሚያሳስቧችሁን ነገሮች በግልጽ ተነጋገሩ። ልጆቹ ከቤት መውጣታቸው ያስከተለባችሁን ስሜት ለትዳር ጓደኛችሁ በግልጽ ተናገሩ፤ የትዳር ጓደኛችሁ የተሰማውን ስሜት በሚገልጽበት ጊዜም በጥሞና አዳምጡ። ታጋሾችና የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ። የትዳር ዝምድናችሁን ማጠናከር ጊዜ ሊወስድባችሁ ይችላል፤ ይሁንና በዚህ ረገድ የምታደርጉት ጥረት የሚያስቆጭ አይሆንም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ቆሮንቶስ 13:4

የተለያዩ ነገሮችን በጋራ ለማከናወን ጥረት አድርጉ። የጋራ የሆነ ግብ አውጡ፤ እንዲሁም አብራችሁ ጊዜ ልታሳልፉ የምትችሉባቸውን ነገሮች ምረጡ። ልጆችን በማሳደግ ረገድ ጥሩ ተሞክሮ እንዳካበታችሁ የታወቀ ነው። ይህን ያገኛችሁትን ተሞክሮ ለምን ሌሎችን ለመርዳት አትጠቀሙበትም?—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኢዮብ 12:12

የቀድሞ ፍቅራችሁን አድሱ። ከመጋባታችሁ በፊት ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር እንድትዋደዱ ስላደረጓችሁ ባሕርያት አስቡ። በትዳር ሕይወታችሁ ያሳለፋችኋቸውን ትዝታዎችና ውጣ ውረዶች መለስ ብላችሁ አስታውሱ። እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው መኖር ከጀመሩም በኋላ ሕይወታችሁ አስደሳች ሊሆንላችሁ ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለታችሁም ጥረት ካደረጋችሁ ትዳራችሁ ይበልጥ ሊጠናከር እንዲሁም የቀድሞው ፍቅራችሁ ሊታደስ ይችላል።

^ አን.4 ኢሞሽናል ኢንፊደልቲ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

^ አን.12 ራሳቸውን ችለው መኖር ያልጀመሩ ልጆች ቢኖራችሁም እንኳ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር “አንድ ሥጋ” መሆናችሁን መዘንጋት የለባችሁም። (ማርቆስ 10:8) ልጆች ወላጆቻቸው ጥሩ ቅርርብ እንዳላቸው ሲመለከቱ ይበልጥ ደስተኞች ይሆናሉ።