በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በኢሳይያስ 60:1 ላይ የተጠቀሰችው “ሴት” ማን ነች? ‘የምትነሳው’ እና ‘ብርሃን የምታበራውስ’ እንዴት ነው?

ኢሳይያስ 60:1 እንዲህ ይላል፦ “አንቺ ሴት ሆይ፣ ተነሺ፣ ብርሃን አብሪ፤ ብርሃንሽ መጥቷልና። የይሖዋ ክብር በአንቺ ላይ ያበራል።” ከአውዱ እንደምንረዳው እዚህ ላይ የተጠቀሰችው “ሴት” ጽዮን ወይም በወቅቱ የይሁዳ ዋና ከተማ የነበረችው ኢየሩሳሌም ነች። a (ኢሳ. 60:14፤ 62:1, 2) ይህች ከተማ መላውን ብሔር ትወክላለች። ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ሁለት ጥያቄዎችን ያስነሳሉ፦ አንደኛ፣ ኢየሩሳሌም ‘የተነሳችው’ እና መንፈሳዊ ብርሃን ያበራችው መቼና እንዴት ነው? ሁለተኛ፣ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው?

ኢየሩሳሌም ‘የተነሳችው’ እና መንፈሳዊ ብርሃን ያበራችው መቼና እንዴት ነው? አይሁዳውያን በባቢሎን በግዞት በነበሩባቸው 70 ዓመታት ውስጥ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ፈራርሰው ቆይተዋል። ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ ከወደቀች በኋላ ግን በመላው የባቢሎን ግዛት የሚኖሩት እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ ዳግመኛ እንዲያቋቁሙ ተፈቀደላቸው። (ዕዝራ 1:1-4) ከ537 ዓ.ዓ. አንስቶ ከ12ቱም ነገዶች የተውጣጡ ታማኝ ቀሪዎች ይህን አድርገዋል። (ኢሳ. 60:4) ለይሖዋ መሥዋዕቶችን ማቅረብ፣ በዓላትን ማክበር እንዲሁም ቤተ መቅደሱን መልሰው መገንባት ጀመሩ። (ዕዝራ 3:1-4, 7-11፤ 6:16-22) የአምላክ ክብር በድጋሚ በኢየሩሳሌም ማለትም መልሰው በተቋቋሙት የአምላክ ሕዝቦች ላይ ማብራት ጀመረ። እነሱም በበኩላቸው፣ በመንፈሳዊ ጨለማ ላይ ለነበሩት ብሔራት የብርሃን ምንጭ ሆነዋል።

ይሁንና ኢሳይያስ የተናገራቸው የተሃድሶ ትንቢቶች በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸሙት በከፊል ብቻ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ፣ እስራኤላውያን አምላክን መታዘዛቸውን አልቀጠሉም። (ነህ. 13:27፤ ሚል. 1:6-8፤ 2:13, 14፤ ማቴ. 15:7-9) እንዲያውም ከጊዜ በኋላ መሲሑን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። (ማቴ. 27:1, 2) በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ለሁለተኛ ጊዜ ጠፉ።

ይሖዋ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል። (ዳን. 9:24-27) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ የሚገኙት የተሃድሶ ትንቢቶች በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸሙ ዓላማው አልነበረም።

ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው? አዎ፣ ሆኖም ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉት ከሌላ ምሳሌያዊት ሴት ማለትም ‘ከላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም’ ጋር በተያያዘ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህች ሴት ሲናገር “እሷም እናታችን ናት” ብሏል። (ገላ. 4:26) ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የአምላክ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ታመለክታለች። ልጆቿ ኢየሱስንና እንደ ጳውሎስ ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን በመንፈስ የተቀቡ 144,000 ክርስቲያኖች ያካትታሉ። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ቅዱስ ብሔር” ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤል’ ናቸው።—1 ጴጥ. 2:9፤ ገላ. 6:16

ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ‘የተነሳችው’ እና ‘ብርሃን ያበራችው’ እንዴት ነው? በምድር ላይ ባሉት ቅቡዓን ልጆቿ አማካኝነት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ያጋጠማቸውን ሁኔታ በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር ለማወዳደር እንሞክር።

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘መነሳት’ ያስፈለጋቸው ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ ኢየሱስ በትንቢቱ ላይ በጠቀሰው የክህደት እንክርዳድ ተውጠው በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው። (ማቴ. 13:37-43) በዚህ መንገድ፣ በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በምታመለክተው በታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ሥር ወደቁ። ቅቡዓኑ ‘እስከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ድረስ በግዞት ቆይተዋል፤ ይህ ጊዜ የጀመረው በ1914 ነው። (ማቴ. 13:39, 40) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በ1919 ነፃ ወጡ፤ ወዲያውኑም በስብከቱ ሥራ በመጠመድ መንፈሳዊ ብርሃን ማብራት ጀመሩ። b ባለፉት ዓመታት፣ በኢሳይያስ 60:3 ላይ የተጠቀሱትን “ነገሥታት” ማለትም የአምላክን እስራኤል ቀሪዎች ጨምሮ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ወደዚህ ብርሃን መጥተዋል።—ራእይ 5:9, 10

ወደፊት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የይሖዋን ብርሃን ከዚህም በላቀ ሁኔታ ያንጸባርቃሉ። በምን መንገድ? ምድራዊ ሕይወታቸውን ሲያጠናቅቁ የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችው ‘የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም’ ክፍል ይሆናሉ፤ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ከክርስቶስ ጋር አብረው ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑትን 144,000 ቅቡዓን ታመለክታለች።—ራእይ 14:1፤ 21:1, 2, 24፤ 22:3-5

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በኢሳይያስ 60:1 ፍጻሜ ረገድ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች። (ኢሳይያስ 60:1, 3, 5, 11, 19, 20⁠ን ከራእይ 21:2, 9-11, 22-26 ጋር አወዳድር።) ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም የጥንቷ እስራኤል መንግሥት መቀመጫ እንደነበረች ሁሉ አዲሱን ሥርዓት የሚያስተዳድረው መንግሥት ክርስቶስንና አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ያቀፈ ነው። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ የምትወርደው’ እንዴት ነው? ትኩረቷን ወደ ምድር በማዞር ነው። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች “በእሷ ብርሃን ይጓዛሉ።” እነዚህ ሰዎች ከኃጢአትና ከሞትም ጭምር ነፃ ይወጣሉ። (ራእይ 21:3, 4, 24) በውጤቱም ኢሳይያስና ሌሎቹ ነቢያት እንደተነበዩት ‘ሁሉም ነገሮች ሙሉ በሙሉ ይታደሳሉ።’ (ሥራ 3:21) ይህ ታላቅ ተሃድሶ የጀመረው ክርስቶስ ንጉሥ በሆነበት ወቅት ሲሆን የሚጠናቀቀው ደግሞ በሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ላይ ነው።

a የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም ኢሳይያስ 60:1 ላይ “ጽዮን” ወይም “ኢየሩሳሌም” ከማለት ይልቅ “ሴት” የሚለውን ቃል የተጠቀመው የዕብራይስጡ ጽሑፍ ላይ “ተነሺ” እና “ብርሃን አብሪ” የሚሉት ግሶች በአነስታይ ፆታ ስለተቀመጡ ነው። “አንቺ ሴት ሆይ” የሚለው አገላለጽ መግባቱ አንባቢው ይህ ጥቅስ እየተናገረ ያለው ስለ ምሳሌያዊት ሴት እንደሆነ እንዲገነዘብ ይረዳዋል።

b በ1919 የተከናወነው መንፈሳዊ ተሃድሶ በሕዝቅኤል 37:1-14 እና በራእይ 11:7-12 ላይም ተጠቅሷል። የሕዝቅኤል ትንቢት የሚናገረው ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጣም ረጅም ለሆነ ጊዜ በምርኮ ከቆዩ በኋላ በመንፈሳዊ መልሰው እንደሚቋቋሙ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ትንቢት ደግሞ የሚናገረው አመራር የሚሰጡት ጥቂት ቅቡዓን ወንድሞች ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመታሰራቸው የተነሳ ለአጭር ጊዜ ያህል ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነው ከቆዩ በኋላ በመንፈሳዊ ስለማንሰራራታቸው ነው። እነዚህን ቅቡዓን ወንድሞች ያቀፈው ቡድን በ1919 “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆኖ ተሾመ።—ማቴ. 24:45የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ! ገጽ 118⁠ን ተመልከት