በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው ማን ነው?

ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው ማን ነው?

የሚደርስብንን መከራ የሚያመጣው አምላክ ካልሆነ በዓለም ላይ ለሚታየው ከባድ ረሃብ፣ የሚያቆራምድ ድህነት፣ አሰቃቂ ጦርነት፣ ሥር የሰደደ በሽታና አውዳሚ የተፈጥሮ አደጋ ተጠያቂው ማን ነው? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ዘር ላይ ለሚደርሰው መከራ ሦስት ዋና ዋና መንስኤዎችን ይጠቅሳል፦

  1. ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነትና ጥላቻ። “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9) ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለሥቃይ የሚዳረጉት ፍጽምና የሌላቸው፣ ራስ ወዳድ ወይም ጨካኝ የሆኑ ሰዎች በሚያደርሱባቸው በደል የተነሳ ነው።

  2. ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ስለሚያጋጥሟቸው ነው። (መክብብ 9:11) በመሆኑም ሰዎች በአጉል ሰዓት አጉል ቦታ ላይ በመገኘታቸው፣ ድንገተኛ አደጋ በመከሰቱ አሊያም ግድየለሾች በመሆናቸው ወይም ስህተት በመሥራታቸው ለችግር ሊዳረጉ ይችላሉ ማለት ነው።

  3. ክፉ የሆነው የዚህ ዓለም ገዢ። መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ዋነኛው መንስኤ ማን እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:19) “ክፉው” ተብሎ የተጠራው መጀመሪያ ላይ የአምላክ መልአክ የነበረው ሆኖም “በእውነት ውስጥ ጸንቶ [ያልቆመው]” ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ከጊዜ በኋላ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትም የራስ ወዳድነት ምኞታቸውን ለማሳደድ ሲሉ ከሰይጣን ጋር ተባብረው በአምላክ ላይ ያመፁ ሲሆን በዚህ መንገድ ራሳቸውን አጋንንት አድርገዋል። (ዘፍጥረት 6:1-5) ሰይጣንና አጋንንቱ በአምላክ ላይ ካመፁበት ጊዜ አንስቶ በዚህ ዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ከመሆኑም ሌላ ዓለም በጭካኔ የተሞላ እንዲሆን አድርገዋል። በተለይ በዘመናችን ይህ እውነት መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። በዛሬው ጊዜ ዲያብሎስ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ሲሆን ይህም በምድር ላይ ‘ወዮታ’ አስከትሏል። (ራእይ 12:9, 12) በእርግጥም ሰይጣን ጨካኝና አምባገነን ገዢ ነው። ሰዎችን በማሠቃየት ይደሰታል። ሰዎች እንዲሠቃዩ የሚያደርገው ሰይጣን እንጂ አምላክ አይደለም።

እስቲ አስበው፦ ንጹሐን ሰዎች እንዲሠቃዩ የሚያደርገው ጨካኝ የሆነና ርኅራኄ የሌለው አካል ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) ሁለንተናው ፍቅር የሆነው “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!”—ኢዮብ 34:10

ይሁን እንጂ ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ፣ ሰይጣን ጭካኔ በተሞላበት አገዛዙ እንዲቀጥል የሚፈቅድለት እስከ መቼ ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አምላክ ክፋትን የሚጠላ ሲሆን እኛ ስንሠቃይ አብሮን ይሠቃያል። በተጨማሪም የአምላክ ቃል “የሚያስጨንቃችሁን . . . ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 5:7) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደሚብራራው አምላክ የሚወደን ከመሆኑም ሌላ በእኛ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ዓይነት መከራና የፍትሕ መጓደል ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው። *

^ አን.7 መከራ የበዛው ለምን እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 26 ተመልከት። መጽሐፉን ከ​www.isa4310.com/am ላይ በነፃ ማውረድ ይቻላል።