ለቲቶ የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-15

  • ተገቢ ታዛዥነት ማሳየት (1-3)

  • ለመልካም ሥራ ዝግጁ መሆን (4-8)

  • ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክርና ከኑፋቄ መራቅ (9-11)

  • ለቲቶ የተሰጠ መመሪያና ሰላምታ (12-15)

3  ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ+ እንዲሁም ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው፤  ደግሞም ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳይናገሩ፣ ጠበኞች እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንዲሆኑና+ ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።+  እኛም በአንድ ወቅት የማናመዛዝን፣ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ የምንገዛ፣ በክፋትና በቅናት የምንኖር፣ በሰዎች ዘንድ የምንጠላና እርስ በርስ የማንዋደድ ነበርን።  ይሁን እንጂ አዳኛችን የሆነው አምላክ ደግነትና+ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር በተገለጠ ጊዜ  (እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን+ በምሕረቱ)+ እኛን አጥቦ ሕያው በማድረግና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማደስ+ አዳነን።+  ይህን መንፈስ አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ* አፈሰሰው፤+  ይህን ያደረገው በእሱ ጸጋ አማካኝነት ከጸደቅን+ በኋላ ከተስፋችን ጋር በሚስማማ ሁኔታ የዘላለም ሕይወትን+ እንድንወርስ ነው።+  እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸው ናቸው፤ ደግሞም በአምላክ ያመኑ ሁሉ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዲያተኩሩ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ዘወትር አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። እነዚህ ነገሮች መልካምና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው።  ሆኖም ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር፣ ከትውልድ ሐረግ ቆጠራ፣ ከጭቅጭቅና ሕጉን በተመለከተ ከሚነሳ ጠብ ራቅ፤ እነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅሙና ከንቱ ናቸው።+ 10  ኑፋቄ+ የሚያስፋፋን ሰው ከአንዴም ሁለቴ አጥብቀህ ምከረው።*+ ካልሰማህ ግን ከእሱ ራቅ፤+ 11  እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከትክክለኛው መንገድ የወጣና ኃጢአት እየሠራ ያለ ከመሆኑም ሌላ በራሱ ላይ እንደፈረደ እወቅ። 12  አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን+ ወደ አንተ ስልክ፣ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጶሊስ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁና። 13  ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቀው ዜናስም ሆነ አጵሎስ ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።+ 14  ይሁን እንጂ አሳሳቢ ችግር ሲፈጠር መርዳት እንዲችሉና+ ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ የእኛም ሰዎች በመልካም ሥራ መጠመድን ይማሩ።+ 15  አብረውኝ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለሚወዱን የእምነት ባልንጀሮቻችን ሰላምታ አቅርብልኝ። የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በልግስና።”
ወይም “አስጠንቅቀው።”