ምዕራፍ ስድስት
ሙታን የት ናቸው?
ስንሞት ምን እንሆናለን?
የምንሞተው ለምንድን ነው?
ስለ ሞት ትክክለኛውን ነገር ማወቅ ያጽናናል?
1-3. ሰዎች ሞትን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ያነሳሉ? የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚሰጧቸው መልሶችስ ምንድን ናቸው?
እነዚህ ጥያቄዎች ሰዎችን ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲያሳስቡ የኖሩ ከመሆናቸውም በላይ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች ናቸው። ማንም እንሁን ማን ወይም የትም እንኑር የት ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች ሁላችንንም ይመለከቱናል።
2 ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን በር እንዴት እንደከፈተልን ተመልክተናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሞት የማይኖርበት’ ዘመን እንደሚመጣ የሚተነብይ መሆኑን ተምረናል። (ራእይ 21:4) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ማንኛችንም ብንሆን ከሞት ነፃ አይደለንም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉ” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 9:5) የተቻለንን ያህል ረጅም ዕድሜ ለመኖር እንጥራለን። ያም ሆኖ ስንሞት ምን እንሆን ይሆን ብለን ማሰባችን አይቀርም።
3 የምንወዳቸው ሰዎች ሲሞቱ በጣም እናዝናለን። እንዲያውም ‘ወዴት ነው የሄዱት? እየተሠቃዩ ይሆን? ከክፉ ሊጠብቁን ይችላሉ? ልንረዳቸው የምንችለው ነገር አለ? ዳግመኛ እናገኛቸው ይሆን?’ የሚሉ ጥያቄዎች እናነሳ ይሆናል። የዓለም ሃይማኖቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ጥሩ ሥነ ምግባር ካለህ ወደ ሰማይ ትሄዳለህ፣ መጥፎ ሥነ ምግባር ካለህ ግን በአንድ መሠቃያ ቦታ ትቃጠላለህ ብለው ያስተምራሉ። ሌሎች ሃይማኖቶች ደግሞ ሰዎች ሲሞቱ ወደ መንፈሳዊው ዓለም በመሸጋገር ከጥንት አባቶቻቸው ጋር ይኖራሉ ብለው ያስተምራሉ። ሙታን ወደ ታችኛው ዓለም ሄደው ከተፈረደባቸው በኋላ ሌላ አካል ለብሰው ዳግመኛ ይወለዳሉ ብለው የሚያስተምሩ ሃይማኖቶችም አሉ።
4. ሞትን በተመለከተ ብዙዎቹን ሃይማኖቶች የሚያመሳስላቸው ምን ነገር አለ?
4 እነዚህን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በሙሉ የሚያመሳስላቸው መሠረታዊ የሆነ አንድ የጋራ ነጥብ አለ። ሁሉም፣ ሥጋዊ አካላችን ሲሞት በሕይወት የምትቀጥል ነገር በውስጣችን አለች የሚለውን እምነት የሚያንጸባርቁ ናቸው። ጥንት የነበሩትም ሆኑ አሁን ያሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የማየት፣ የመስማትና የማሰብ ችሎታችንን ሳናጣ በሆነ መንገድ ለዘላለም እንኖራለን የሚል አመለካከት አላቸው። ግን ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? መስማት፣ ማየትና ማሰብ የምንችለው አንጎላችን እስከሠራ ድረስ ብቻ ነው። ስንሞት አንጎላችን መሥራቱን ያቆማል። አንጎላችን መሥራት ካቆመ ደግሞ ምንም ዓይነት ስሜት ሊሰማን የማይችል ከመሆኑም በላይ ማስታወስ፣ መስማትም ሆነ ማየት አንችልም።
ታዲያ ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?
5, 6. መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ምን ያስተምራል?
5 ስንሞት ምን እንሆናለን የሚለው ጥያቄ አእምሮን ለፈጠረው ለይሖዋ እንቆቅልሽ አይደለም። ትክክለኛውን መልስ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ገልጾልናል። ግልጽ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚከተለው ነው:- አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ከሕልውና ውጭ ይሆናል። ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። ሙታን ሊያዩ፣ ሊሰሙም ሆነ ሊያስቡ አይችሉም። ሥጋችን ሲሞት በሕይወት የምትቀጥል ረቂቅ አካል በውስጣችን የለችም። የማይሞት ነፍስ ወይም መንፈስ የለንም። *
6 ሰሎሞን፣ ሕያዋን እንደሚሞቱ የሚያውቁ መሆኑን ከገለጸ በኋላ “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ሲል ጽፏል። ከዚያም ሙታን መውደድም ሆነ መጥላት እንደማይችሉና በመቃብር “መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ” እንደሌለ በማመልከት መሠረታዊውን እውነት ይበልጥ ሰፋ አድርጎ ገልጿል። (መክብብ 9:5, 6, 10) በተመሳሳይም መዝሙር 146:4 ሰዎች ሲሞቱ “ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል” ይላል። ሟቾች በመሆናችን ሥጋችን ሲሞት በሕይወት የምንቀጥልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም። ሕይወታችን እንደ ሻማ ብርሃን ነው። የሻማው ብርሃን ሲጠፋ እንዳልነበር ይሆናል እንጂ የትም አይሄድም።
ኢየሱስ ሞትን አስመልክቶ ምን ተናግሯል?
7. ኢየሱስ ሞትን የገለጸው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ተናግሯል። በደንብ ያውቀው የነበረው አልዓዛር የተባለ ሰው በሞተ ጊዜ የተናገረው ቃል ይህን ይጠቁማል። ደቀ መዛሙርቱን “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ አልዓዛር ታሞ ተኝቷል ያላቸው መስሏቸው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደዚያ ማለቱ አልነበረም። በመሆኑም “አልዓዛር ሞቶአል” በማለት በግልጽ ነገራቸው። (ዮሐንስ 11:11-14) ኢየሱስ ሞትን ከእረፍትና ከእንቅልፍ ጋር እንዳመሳሰለው ልብ በል። አልዓዛር ሰማይም ሆነ እሳታማ ሲኦል ውስጥ አልነበረም። ከመላእክት ወይም ከጥንት አባቶቹ ጋር አልተገናኘም። በተጨማሪም አልዓዛር ሌላ ሰው ሆኖ ዳግመኛ የሚወለድበት ሂደት ውስጥ አልነበረም። ሕልም አልባ በሆነ ከባድ እንቅልፍ ውስጥ ያለ ያህል ሆኖ በሞት አንቀላፍቶ ነበር። ሌሎች ጥቅሶችም ሞትን ከእንቅልፍ ጋር ያመሳስሉታል። ለምሳሌ ያህል ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ በሞተ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “አንቀላፋ” ሲል ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 7:60) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ በእሱ ዘመን በሞት ‘ስላንቀላፉ’ አንዳንድ ሰዎች ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 15:6
8. የአምላክ ዓላማ ሰዎች እንዲሞቱ እንዳልነበር እንዴት እናውቃለን?
8 የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ሰዎች እንዲሞቱ ነበር? በፍጹም! ይሖዋ ሰውን የፈጠረው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በጣም አስደሳች በሆነች ገነት ውስጥ ያስቀመጣቸው ከመሆኑም በላይ ፍጹም የሆነ ጤንነት ሰጥቷቸው ነበር። ይሖዋ የተመኘላቸው ነገር ሁሉ መልካም ነበር። ልጆቹ በእርጅና ተሠቃይተው እንዲሞቱ የሚፈልግ አፍቃሪ ወላጅ ይኖራል? እንደማይኖር የታወቀ ነው! ይሖዋ ልጆቹን የሚወድ በመሆኑ በምድር ላይ ለዘላለም ተደስተው እንዲኖሩ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን በተመለከተ ሲናገር “[ይሖዋ] በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ” ይላል። (መክብብ 3:11) አምላክ የፈጠረን ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። ይህን ፍላጎታችንን ለማሟላትም ዝግጅት አድርጓል።
ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?
9. ይሖዋ በአዳም ላይ ምን እገዳ ጥሎበት ነበር? ይህ ትእዛዝ ከባድ አልነበረም የምንለውስ ለምንድን ነው?
9 ታዲያ ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በምድር ላይ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ብቻ በነበሩበት ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ መመልከት ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር አምላክም ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ” ሲል ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:9) ይሁን እንጂ አንድ እገዳ ተጥሎ ነበር። ይሖዋ አዳምን “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይህ ትእዛዝ ከባድ አልነበረም። አዳምና ሔዋን ሊበሏቸው የሚችሉ ሌሎች በርካታ ፍራፍሬዎች ነበሩ። ሆኖም ይህ ትእዛዝ ፍጹም ሕይወትን ጨምሮ ሁሉን ነገር ለሰጣቸው አምላክ አመስጋኞች መሆናቸውን መግለጽ የሚችሉበት ልዩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። በተጨማሪም ይህን መመሪያ መታዘዛቸው የሰማያዊ አባታቸውን ሥልጣን እንደሚያከብሩና ፍቅራዊ አመራሩን ማግኘት እንደሚፈልጉ ያሳያል።
10, 11. (ሀ) የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አምላክን ለመታዘዝ አሻፈረን ያሉት እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ መጣሳቸው በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ያልሆነው ለምንድን ነው?
10 የሚያሳዝነው የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ይሖዋን ለመታዘዝ አሻፈረን አሉ። ሰይጣን በእባብ አማካኝነት ሔዋንን በማነጋገር “በእርግጥ እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” ሲል ጠየቃት። ሔዋንም “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሎአል” ስትል መለሰችለት።—ዘፍጥረት 3:1-3
11 ሰይጣን “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” አላት። (ዘፍጥረት 3:4, 5) ሰይጣን፣ ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ መብላቷ ጥቅም እንደሚያስገኝላት ሆኖ እንዲሰማት ማድረግ ፈልጎ ነበር። እሱ እንዳለው ከሆነ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለራሷ መወሰን ትችላለች፤ እንዲሁም የፈለገችውን ማድረግ ትችላለች። በተጨማሪም ሰይጣን ፍሬውን መብላት የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ይሖዋ ዋሽቷል ሲል ወንጅሎታል። ሔዋን፣ ሰይጣን ያላትን አመነች። በመሆኑም ፍሬውን ወስዳ በላች። ከዚያም ለባልዋ ሰጠችውና እሱም በላ። ይህን ያደረጉት ባለማወቅ አይደለም። አምላክ እንዳያደርጉ ያዘዛቸውን ነገር እያደረጉ እንዳሉ ያውቁ ነበር። ፍሬውን በመብላት የተሰጣቸውን ቀላልና ምክንያታዊ የሆነ ትእዛዝ ሆን ብለው ጣሱ። በዚህ መንገድ ለሰማያዊ አባታቸውና ለሥልጣኑ ያላቸውን ንቀት አሳዩ። አፍቃሪ ለሆነው ፈጣሪያቸው ያሳዩት ንቀት በይቅርታ ሊታለፍ የሚችል አልነበረም!
12. ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን እሱን የሚጻረር እርምጃ ሲወስዱ ምን እንደተሰማው እንድንገነዘብ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
12 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ተንከባክበህ ያሳደግኸው ልጅ ለአንተ ምንም ዓይነት አክብሮትም ሆነ ፍቅር እንደሌለው በሚያሳይ መንገድ ትእዛዝህን ቢጥስ ምን ይሰማሃል? እጅግ እንደምታዝን ጥርጥር የለውም። እንግዲያው ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን እሱን የሚጻረር እርምጃ ሲወስዱ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ገምት።
13. ይሖዋ፣ አዳም በሚሞትበት ጊዜ ምን እንደሚሆን ተናግሯል? ይህስ ምን ማለት ነው?
13 ይሖዋ ለመታዘዝ አሻፈረን ያሉትን አዳምንና ሔዋንን ለዘላለም የሚያኖርበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም አዳምና ሔዋን፣ ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ሞቱ ወይም ከሕልውና ውጭ ሆኑ። ወደ መንፈሳዊ ዓለም አልተዘዋወሩም። ይሖዋ፣ አዳምን ለሠራው ጥፋት ተጠያቂ ካደረገው በኋላ የተናገረው ቃል ይህን እንድንገነዘብ ያደርገናል። አምላክ “ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት [ትመለሳለህ] . . . ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:19) አምላክ አዳምን የፈጠረው ከምድር አፈር ነው። (ዘፍጥረት 2:7) ከዚያ በፊት አዳም ከሕልውና ውጭ ነበር። ስለዚህ ይሖዋ፣ አዳም ወደ አፈር እንደሚመለስ ሲናገር ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ተመልሶ ከሕልውና ውጭ ይሆናል ማለቱ ነበር። አዳም ልክ እንደተሠራበት አፈር ሕይወት አልባ ይሆናል ማለት ነው።
14. የምንሞተው ለምንድን ነው?
14 አዳምና ሔዋን ዛሬም ሕያዋን መሆን በቻሉ ነበር፤ ሆኖም የአምላክን ትእዛዝ ለመጣስ በመምረጣቸውና ኃጢአት በመሥራታቸው ሊሞቱ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ እኛ የምንሞተው የአዳም ኃጢአትና ሞት ለዘሮቹ በሙሉ በመተላለፉ ነው። (ሮሜ 5:12) ይህ ኃጢአት ማንም ሊያመልጠው እንደማይችል በዘር የሚወረስ አስከፊ በሽታ ነው። የኃጢአት ውጤት የሆነው ሞት ደግሞ እርግማን ነው። ሞት ወዳጅ ሳይሆን ጠላት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ይሖዋ እኛን ከዚህ ክፉ ጠላት ለመታደግ ቤዛውን በማዘጋጀቱ በጣም ልናመሰግነው ይገባል!
ስለ ሞት ትክክለኛውን ነገር ማወቅ ጠቃሚ ነው
15. ስለ ሞት ትክክለኛውን ነገር ማወቁ የሚያጽናናው ለምንድን ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚሰጠው ትምህርት ያጽናናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሙታን ሥቃይም ሆነ ሐዘን አይደርስባቸውም። ሊጎዱን ስለማይችሉ ሙታንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። የእኛ እርዳታ አያስፈልጋቸውም፣ እነሱም ሊረዱን አይችሉም። ልናናግራቸውም ሆነ ሊያናግሩን አይችሉም። ብዙ የሃይማኖት መሪዎች ሙታንን መርዳት እንችላለን እያሉ ሰዎችን ያታልላሉ፤ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ ገንዘብ ይከፍሏቸዋል። ሆኖም ስለ ሞት ትክክለኛውን ነገር ማወቃችን እንዲህ ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን በሚያስተምሩ ሰዎች እንዳንታለል ይጠብቀናል።
16. ብዙዎቹ ሃይማኖቶች በሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ማን ነው? እንዴትስ?
16 ሃይማኖትህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ይስማማል? አብዛኞቹ ሃይማኖቶች አይስማሙም። ለምን? ሰይጣን በትምህርቶቻቸው ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳደረ በመሆኑ ነው። ሰዎች ሥጋችን ከሞተ በኋላ በመንፈሳዊው ዓለም እንኖራለን የሚል እምነት እንዲያድርባቸው ለማድረግ የሐሰት ሃይማኖትን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። ይህ ትምህርት ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ አምላክ ለማራቅ ከሚጠቀምባቸው የሐሰት ትምህርቶች አንዱ ነው። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?
17. ስለ ዘላለማዊ መሠቃያ ቦታ የሚሰጠው ትምህርት ይሖዋን የማያስከብረው ለምንድን ነው?
17 ቀደም ሲል እንደተገለጸው አንዳንዶቹ ሃይማኖቶች አንድ ሰው አኗኗሩ መጥፎ ከሆነ ከሞተ በኋላ እሳታማ ወደሆነ መሠቃያ ሥፍራ ገብቶ ለዘላለም ይሠቃያል ብለው ያስተምራሉ። ይህ ትምህርት የአምላክን ስም የሚያጠፋ ነው። ይሖዋ የፍቅር አምላክ በመሆኑ ሰዎችን ፈጽሞ በዚህ መንገድ አያሠቃይም። (1 ዮሐንስ 4:8) አንድ ሰው ልጁ አልታዘዝ በማለቱ እጆቹን ይዞ እሳት ውስጥ በመጨመር ቢቀጣው ምን ይሰማሃል? እንዲህ ያለውን ሰው ታከብረዋለህ? ማክበር ቀርቶ ልትተዋወቀውስ ትፈልጋለህ? እንደማትፈልግ የተረጋገጠ ነው! እንዴት ያለው ጨካኝ ነው ብለህ ማሰብህ አይቀርም። ይሁንና ሰይጣን፣ ይሖዋ ሰዎችን ለዝንተ ዓለም በእሳት ያሠቃያል ብለን እንድናምን ይፈልጋል!
18. የሙታን አምልኮ በየትኛው የሐሰት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው?
18 በተጨማሪም ሰይጣን አንዳንድ ሃይማኖቶችን በመጠቀም ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሕያዋን ሰዎች ሊያከብሯቸውና ሊፈሯቸው የሚገቡ መናፍስት ይሆናሉ ብሎ ያስተምራል። በዚህ ትምህርት መሠረት የሙታን መናፍስት ኃያላን ወዳጆች ወይም አስፈሪ ጠላቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ሰዎች በዚህ የሐሰት ትምህርት ያምናሉ። ሙታንን ስለሚፈሩ ያከብሯቸዋል እንዲሁም ያመልኳቸዋል። በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን እንዳንቀላፉና ማምለክ ያለብን ፈጣሪያችንና ተንከባካቢያችን የሆነውን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ብቻ እንደሆነ ያስተምረናል።—ራእይ 4:11
19. ስለ ሞት ትክክለኛውን ነገር ማወቃችን ምን ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንድንገነዘብ ይረዳናል?
19 ስለ ሙታን ትክክለኛውን ነገር ማወቅህ ሐሰት በሆኑ የሃይማኖት ትምህርቶች እንዳትታለል ይጠብቅሃል። በተጨማሪም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንድትገነዘብ ይረዳሃል። ለምሳሌ ያህል ሰዎች ሲሞቱ ወደ መንፈሳዊው ዓለም እንደማይሄዱ ስትረዳ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ትርጉም ያለው ይሆንልሃል።
20. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የትኛው ጥያቄ ይብራራል?
20 ከረጅም ጊዜ በፊት ጻድቁ ሰው ኢዮብ “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። (ኢዮብ 14:14) በሞት ያንቀላፋ በድን ሰው ዳግመኛ ሕያው ሊሆን ይችላል? የሚቀጥለው ምዕራፍ እንደሚያብራራው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ የሚሰጠው ትምህርት እጅግ የሚያጽናና ነው።
^ አን.5 “ነፍስ” እና “መንፈስ” የሚሉትን ቃላት በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 208-211 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።